ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ እና ሰደን ሶዶ ወረዳዎች ከኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የወረዳዎቹ አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከአመራሮች የቅርብ ሰዎች ሰምታለች።
በዚህም ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 05/2016 የበቾ ወረዳ አስተዳዳሪ እና የወረዳው የፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መታሰራቸው ነው መረዳት የተቻለው።
በተጨማሪም ባለፈው አርብ መስከረም 04/2016 የሰዴን ሶዶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች የተወሰኑ የወረዳው አመራሮች መታሰራቸውም ተነግሯል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን ባለፈው መስከረም 01/2016 ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ በተመሳሳይ ሰዓት በዞኑ በሚገኙት በቾ፣ ሰዴን ሶዶ እና ቶሌ ወረዳዎች በዋና ከተሞቻቸው ተኩስ በመክፈት የታጣቂ ቡድኑን አባላት ለማስለቀቅ ሙከራ ማድረጋቸው እና በተለይ ቶሌ ወረዳ ላይ የተወሰኑ እስረኞች ማምለጣቸውን እና የፖሊስ አባላት መገደላቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወቃል፡፡
ጥቃቱ ከተሰነዘረ ጀምሮም በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት ማደሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ጥቃት ሊደርስብን ይችላል በሚል ፍራቻ ንብረታቸውን እየሸጡ እና እያከራዩ አካባቢውን ለቀው የሚወጡ ግለሰቦች መኖራቸውም ተጠቁሟል።
ወቅቱ የተማሪዎች መመዝገቢያ እና ትምህርት የሚጀመርበት ቢሆንም ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው በሚያደርገው እንቅስቃሴ በተለይ በወረዳዎች በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ አለመጀመራቸው ተነግሯል።
ከዚህም ጎን ለጎን “ከእስር ቤት አምልጠዋል” የተባሉትን የታጣቂ ቡድኑ አባላት አሰሳ በሚል በመንግሥት የጸጥታ አካላት ቤት ለቤት በሚደረግ ፍተሻ ወጣቶች ያለአግባብ እየታሰሩ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አስምተዋል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ነዋሪዎችን በማገት “ይህን ያህል ብር ካልከፈላችሁ እንገላችኋላን” በማለት የሚፈጽመው ውንብድና የከፋ ነውም ተብሏል።
የቡድኑ ታጣቂዎች “በበቾ ወረዳ ታስረውብናል” የሚሏቸው አባላቶቻቸውን ለማስፈታት ከወራት በፊትም መሰል ጥቃት መፈጸማቻው ተወስቷል። .
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስረዳዳሪ ታዬ ጉዲሳን ለማነጋጋር ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም፤ ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለጊዜው ማካተት አልተቻለም፡፡



