በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከሰልፉ ጋር በተያያዘ እስርና ድብደባ የተፈጸመባቸው አካላት ካሳ እንዲያገኙ ክስ ለመመስረት ዝግጅት እያደረግን ነው አሉ

0
377

ሐሙስ መስከረም 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ባለፈው በጳጉሜ ወር በመቀሌ ሊደረግ ከነበረው ሰልፍ ጋር በተገናኘ እስር እና ድብደባ የደረሰባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ሕክምና እንዲያገኙ እንዲሁም ተገቢው ካሳ እንዲሰጣቸው ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የውናት፣ ሳልሳይ ወያነ እና ባያቶና ትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕብረት የሚዲያ ማስተባበሪያ ክፍል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ውናት፣ ሳልሳይ ወያነ እና ባያቶና ትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ “የክሱ ሌላኛው ዓላማ ወንጀል የፈጸሙ አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ ነው፡፡” ሲሉ ገልጸው፣ “የጠየቅነው ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላል፡፡” ብለዋል።

የሦስቱ ፓርቲዎች ኅብረት የሚዲያ ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ አብለሎም ገብረ ሚካኤል፤ “ከጳጉሜ 2/2015 ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በመቀሌ ሮማናት አደባባይ ሕዝባችን ያለበትን ሰቆቃ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ልናደርግ የነበረው ሰልፍ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተስተጓጉሏል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

“ሆኖም ግን በሰልፉ ለማድረግ ያቀድነውን አሳክተናል፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ “ይህም በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ እና በደል ማሳወቅ ነበር፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ሌላው አላማችን በክልሉ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል ብለን እንደማመናችን ይህን የሚደግፍ እና ከአላማችን ጎን የሚቆም አባላትን መፍጠር ነበር፡፡ እሱንም ካቀድነው በላይ አሳክተናል፡፡” ሲሉ አውስተዋል፡፡

“የመቀሌ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወልዳይ መውጫ ከሰልፉ ጋር ተያይዞ በሰጡት መግለጫ፤ “በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት” የለም ማለታቸውን ውሸት ነው፡፡” ሲሉም አጣጥለውታል፡፡

ሰልፉን ለማድረግ ወደ አደባባይ በወጣንበት ዕለት የክልሉ መንግሥት ያሰማራቸው በርካታ ኃይሎች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የፓርቲ አባላትን ጨምሮ በርካታ የሰልፉ እድምተኞች ላይ ድብደባ እና ወከባ አድርሰዋል ነው ያሉት።

የፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ከተያዙበት ሰዓት ጀምሮ ሥነምግባር በጎደለው መልኩ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው አውስተው፤ እሳቸውን ጨምሮ ከስድስት ቀናት እስር በኋላ መፈታታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከሰልፍ ጋር በተገናኘ እስር እና ድብደባ የደረሰባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ሕክምና እንዲያገኙ እንዲሁም፤ ተገቢው ካሳ እንዲሰጣቸው ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሦስቱ ፓርቲዎች ጠርተውት የነብረውን ሰልፍ ለማድረግ “አስቻይ የጸጥታ ኹኔታ የለም” በሚል ፈቃድ መንሳቱ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here