የስዕል ጥበብ በወጣቷ ሰዓሊ ብሩሽ

0
1598

በጣልያን የባህል ማዕከል አዘጋጅነት ከማክሰኞ ኅዳር 2/2012 እስከ ኅዳር 6 የዘለቀ የሰዓሊ ሚሊዮን ብርሃኔ የስዕል ሥራዎች የቀረቡበት ‹‹ስእላዊ ቅኔ›› የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ለተመልካች ክፍት ሆኖ ቆይቷል። ለስዕልና ፎቶ አውደ ርዕዮች የሚሰጠው ትኩረት ከጥቂት ቅርብ ተመልካችና ሰሚ ውጪ ብዙም ሆነ በቂ ነው በማይባልበት ደረጃ፤ ሴቶች ደግሞ በተሳትፎም እጅግ ጥቂት ሆነው እንመለከታለን። በስዕል አውደ ርዕዮች ላይ በግላቸውና በነጠላ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡትም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

ታድያ ከእነዚህ ጥቂት መድረኮች መካከል የሚሊዮን ስዕሎች በቀረቡበት የስዕል አውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ መታደም የቻለችው አዲስ ማለዳ፤ ከወጣቷ ሰዓሊ ሚሊዮን ብርሃኔ ጋር በአውደ ርዕዩ እና በሕይወቷ ዙሪያ አጭር ቆይታ ማድረግ ተሳክቶላታል።

ሚሊዮን በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከአቢሲንያ የሥነ ጥበብ ማዕከል በቅርጻ ቅርጽ እና ስዕል ጥበብ ተመርቃለች። ከዚያም ወደ እንጦጦ ቴክኒክ እና ሙያ፤ በቀድሞ አጠራሩ ተፈሪ መኮንን በቅርጻ ቅርጽ እና ቀለም ቅብ ጥናት ተመርቃለች። እንደ ወዳጆቿና የሙያ አጋሮቿ አስተያየት፣ ከሰዓሊነቷ ይልቅ ቀራጺነትዋ ይገዝፋል። በስዕሉ ላይ ከመጠበብ እንደማትቦዝንም ይመሰክራሉ። በእርግጥ እንደነ ከበደች ተክለአብ አይነት እንስት የሥነ ጥበብ ሰዎች በኹለቱም ገጽ መገለጣቸዉ እንግዳ ጉዳይ አይደለም። ሰዓሊዋ ሚሊዮንም በዛ መንገድ የምትሔድ እንደምትሆን መገመት አያዳግትም።

ሚሊዮን ከሌሎች ሰዓልያን ጋር በጥምረት በመሆን በአገር ውስጥ እንዲሁም ባህር ማዶ የተለያዩ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ ተሳትፎ ነበራት። በዚህ ዓመት ግን በግሏ የመጀመሪያዋ የሆነዉን የስዕል አዉደ ርዕይ ለተመልካች ማቅረብ ችላለች።

ስለ አሳሳል ዜይቤ (style) ምርጫዋ የምትናገረው ሰዓሊዋ፤ (semi-realistic) ወደ እዉነታ እንደሚቀርብ ታስረዳለች። ‹‹ሰዓልያን የራሳቸውን የአሳሳል ዘይቤ በብዙ ፍለጋ ዉስጥ አልፈዉ፤ መንገዳቸዉን ለይተዉ እንዳገኙ ሲሰማቸዉ፤ ያኔ በድፍረት ‹እዚህ ምድብ ዉስጥ ነዉ እኔ ራሴን ያገኘሁት› ብለው ሊነግሩህ ይችላሉ›› ትላለች።

ከዚህም ባሻገር አንዳንድ ጊዜ ሰዓልያን አስበዉበት የራሳቸዉን ዓይነት መንገድ መርጠዉ ሥራቸዉን የሚጀምሩም እንዳሉ ሰዓሊዋ ትጠቅሳለች። ብዙ የስዕል ሥራዎቿ ግማሽ ምድራዊነት እና ከፊል ሰማያዊነትን ሲያንፀባርቁ፣ ለአውደ ርዕዩ ያቀረበቻቸው ሥራዎችም በዚሁ አውድ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

በኢትዮጵያ ታሪክን ተገን አድርገዉ የተጻፉ ድርሳናት እንደሚገልጡት፣ በ4ተኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ክርስትና የአክሱም ሃይማኖት ሊሆን ከበቃ በኋላ ምስሎችን፣ ቅርጻ ቅርጾችንና ግዙፍ ሃዉልቶችን በአንድ በኩል ከእምነቱ አስተምህሮ ጋራ የሚጻረር ሆኖ ይታይ ነበር። ከዛ በተጨማሪም የአረመኔያዊ ልማድ ተደርጎ በመቆጠሩ የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ እየከሰመ ሲመጣ በፋንታዉ ክርስትያናዊ ሥነ ስዕል አብቧል። ይህን የምታብራራው ሚሊዮን፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ የአሳሳል ዘዴ በጉልህ ተጽእኖ እንዳሳረፈባት ትናገራለች።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሥነ ጥበባዊ ትዉፊት የራሱ ፍልስፍናን የተከተለ የእዉቀት ይትባህል አለው። ሆኖም ደፍሮ ለመጥቀስ ያህል በመረጃ የተደገፈ እና እንዲህ ነዉ ሊያስብል የሚችል በዛ ፈለግ የተሠራ የራስ ፈጠራ የታከለበት የስዕል ሥራ በብዛት አይታይም። በሚሊዮን ስዕሎች ውስጥ የክብ ዐይን ቅርጽ፤ ነጻ የጀርባ ቦታዎችን እና የ ‹ቶ› መስቀል ክርስትናዊ ምስሎችን እንዲሁም የግዕዝ ቁጥሮችን ማስተዋል ይቻላል። ጥንታዊዉ ሥነ ጥበብ እንዴት ሊዋሃዳት እንደቻለ ስታስረዳ፤ አስቀድማ የጠቀሰችው ምን ያህል ከራሳችን እንደሸሸን ነው።

ሰዓሊዋ ዛሬ በዓለማችን የሚታየው ሳይንስና ጥበብ ሁሉ መነሻው የአፍሪካ ምድር ይልቁንም ኢትዮጵያ እንደሆነች ታምናለች። ነገር ግን እንደጠልሰም ያሉ በምዕራባዉያኑ አገራት ለህክምና ተግባር በሰፊዉ የዋሉ ጥበቦች፣ በዘመን ዉስጥ አስቸጋሪዉን ሰዉ ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ተቋቁመዉ በአብያተ ክርስትያናት እና ገዳማት ዉስጥ እንደሚገኙት ሁሉ፣ ዛሬ ላይ መለስ ብሎ ታሪክን ማጥናት ቢቻል ወደ ቀድሞ ከፍታ መመለስ የማይቻልበት ከልካይ ምክንያት የለም ስትል ሚሊዮን ትገልጻለች።

የስዕል ጥበብ በኢትዮጵያ
በእርግጥ አጥኚዎች በተለያየ ጊዜ እንደመሰከሩት የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ከእድሜዋ እኩል ነው። ለዚህም ጥሩ ማጣቀሻ የሚሆነው አሁን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር በሆኑት በታሪክ መምህር ረደት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የኢትዮጵያን የሦስት ሺሕ ዘመን የሥነ ጥበብ ታሪክ ያስቃኙበት የጽሑፍ ሥራ ነው። በዚሁ ላይ በሦስተኛው እና አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለይ ከክርስትና ጋር የተያያዘው ሥነ ጥበብ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር። በአንጻሩ ከክርስትና መምጣት ቀደም ብሎ ሐውልቶችን ማቆም ነበር በልምድ የቆየው።

የሚገርመው ከዚህም በላይ ጥበቡ በፍልስፍና የሚመራ ነበር ማለት የሚያስችሉ ምልክቶች ነበሩት። ጥንታዊና ቀዳሚ በሆነው የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ፣ ተመልካቹ ስዕሉን የሚያየውን ያህል ስዕሉም ተመልካቹን እንደሚያይ ይታመናል። በዚህ ላይ ቢቢሲ አማርኛ ባነበበው ሥነ ጥበብን ይልቁንም ስዕልን የተመለከተ ጽሑፍ፣ ይህ ሁኔታ ስእሎች ዐይን እንዳላቸው እንዲታሰብ አስችሏል ይላል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ታድያ አስገራሚና በምስጢር የተመሉ ስዕላትን ያቀረቡ ሰዎች በብዛት የሚታወቁ አይደሉም። ይህም የሆነው ሥራው ሃይማኖታዊ ተግባር ተደርጎ ስለሚቆጠር እንደሆነ ይነገራል።

እንደ ታዋቂው ፖላንዳዊ የሥነ ጥበባዊ ታሪክ እና የሥነ ሰብእ ተመራማሪ ስታኒስላቭ ኮይናትስኪም ግምት፣ ኢትዮጵያውያን ቅርጽን ሳይሆን ሐሳብ ነዉ የሚስሉት። ይህንን ‹Major Themes in Ethiopia> በተባለዉ መጽሐፋቸዉ የጠቀሱት ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ እና በከፊልም በእርሱ ላይ ተመሥርቶ ለዓመታት ያህል ከቅርብ የአፍሪካ አገራት እንኳ ተነጥላ መቆየቷ፣ በመሠረታዊነት የራሷ የሆነ ልዩ የአሳሳል ጥበብ እንድታዳብር አስችሏታልም ይላሉ።

የኢትዮጵያን ጥንታዊና የራሷ የሆነውን የስዕል ጥበብ ከዘመናዊ ጋር አጋምዶ በመሔድ የተሳካላቸው ናቸው ከሚባሉ ጥቂት ሰዓልያን መካከል አንዱ ናቸው፤ ልዑልሰገድ ረታ። እርሳቸው ደግሞ ከራሳቸው ባሻገር በተለይ በዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ ጋር አብሮ ስማቸው ይነሳል ሲሉ፤ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ጌታሁን አሰፋ እንዲሁም እሸቱ ጥሩነህን ይጠቅሳሉ። ልዑልሰገድ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሲናገሩ፤ አቅምና ጊዜ ሲኖር አልፎም ኢትዮጵያዊነት የገባን ቀን ስለ ኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ እድገት መነሻና ያለበት ሁናቴ በጥልቅ መጻፍ ይቻላል ይላሉ።

ጥቂት ከሚባሉ ሴት ሰዓልያን መካከል አንዷ የሆነችው የእናትፋንታ አባተ፣ በአውሮፓውያን አቆጣጠር 1996 ነበር ‹‹ነጻ ጥበብን ፍለጋ›› የተሰኘ መርሃ ግብር የጀመረችው። የእናትፋንታ ከዶቼቬሌ ጋተረ ባደረገችው ቆይታ ስትናገር፤ እንደ ቀደሙት ሁሉ ኢትዮጵያ የጥበብ መፍለቂያ ናት ስትል ገልጻለች። የኢትዮጵያ ሰዓልያንም ወደ ማህበረሰቡ በመጠጋትና መገናኛ ንገድ በማግኘት ራሳቸውን በማስተዋወቅ ውስጥ ዘርፉ ይበልጥ ተወዳጅ እንዲሆን ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ታሳስባለች። ታድያ በበኩሏም ዘርፉ ትኩረት እንዲያገኝ ለማስቻል፣ ለማሳደግና በሰፊው ለማስተዋወቅ የተሻለ ጥረት እንደምታደርግ ገልጻለች፤ ሥራዋም ምስክር ነው።
እንዲህ ያሉ የስዕል ጥበብን ወድደውና ፈቅደው እየኖሩት አልፎም ለአገር ትርፍ የሚያስገኝ እያደረጉ ያሉ ሰዓልያን፣ እንዲሁም የቀደሙት አንጋፎቹ በስዕል ልኅቀት ላይ የደረሱት፤ ለሚሊዮን ዓይነት ሰዓልያን አረአያነታቸው ቀላል የሚባል አይሆንም።

ሚሊዮን እና ‹ቀለሟ›
ሚሊዮንም ለኢትዮጵያዉን ሰዓልያን እና የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ ትልቅ አክብሮት እንዳላት ገልጻለች። ይልቁንም ደግሞ ሰዓሊ ደስታ ሀጎስን እንደምታከብርና እንደምታደንቅ ሳትሸሽግ ትናገራለች።

ይህቺ ወጣት ሰዓሊ በስእሎቿ መርከቦችን በድግግሞሽ ትጠቀማለች። በዚህ ውስጥ ያላት የተለየ እይታና መግለጽ የምትሻው ነገር ያለ ከሆነ ስትል አዲስ ማለዳ ጥያቄዋን አቅርባለች። እርሷም ነገሩን ከመጽሐፈ ኄኖክ የጥንት ታሪክ ጋር በማያያዝ ታነሳለች። በዚህም መሠረት ጥንት የሰዉ ልጆች አሰፋፈር የዉሃ አካላትንና ዉሃን የተከተለ በመሆኑ፣ ከዉሃ ጥፋት በኋላ ኖህ ይዞት ያቆየዉን መጽሐፈ ኄኖክን ልጆቹ እርስ በእርስ በመጣላታቸዉ ካም የተባለዉ ልጁ ወደ ግዮን ወንዝ ፈለግ ወደ ሆነዉ አባይ ይዞት ይመጣል።

በዛም ምክንያት ኢትዮጵያ ሊደረስ እንደቻለ ከንባቧ ጠቅሳ ታስረዳለች። መርከቢቱም የ‹ድኅነት› ውክልና እንደሆችና መርከቢቱ ባትኖር ከጥፋት ዉሃ ማን ሊተረፍ አንደሚችል ትጠይቃለች። ይህም የላቀ ትኩረቷን የሳበና በስዕል ሥራዎቿም ላይ እንደ አሻራ ታትሞ እየቀረ የሚታይ ነው።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here