ከኢሕአዴግ ወደ ኢብፓ/ብፓ ጉዞ …!!

0
871

የኢሕአዴግን ምሥረታ ቀደም ካለው ከሕወሓት አነሳስና ቀዳሚ ዓላማ በመጀመር የሚያወሱት ግዛቸው አበበ.፤ አሁንም ላይ በግንባሩ የሚገኙት ፓርቲዎች አጋር ሲሏቸው የቆዩትን ጨምረው ስለሚመሠርቱት ‹ብልጽግና ፓርቲ› አንስተዋል። ይህ በኢሕአዴግ ጀምሮ ወደ ብልጽግና ፓርቲ እየተደረገ ባለው ጉዞም፣ የሕወሓትን ሁኔታ ዳስሰዋል። አሁንም ኢሕአዴግ አስቀድሞም በሕዝብ ከላይ የተጫነ ቡድን እንደሆነው ሁሉ ብልጽግና ፓርቲስ በማንና በነማን ተፈጠረ ሲሉም ይጠይቃሉ።

ቢያንስ እስከ 1980 መገባደጃ ኢሕዴግ የሚባል ቡድን አልነበረም። ኢሕዴን ከሚባለው የሕወሓት ፍጥረት በስተቀር ኦሕዴድ እና ደኢሕዴንን የመሳሰሉ ቡድኖችማ ገና አልተጸነሱም ነበር። እነዚህ ቡድኖች ወደ ህልውና የመጡት ከ1981 ጀምሮ ነው። እስከ 1980 መገባደጃ የነበረው ሕወሓት በይፋ መገንጠልን የሚያቀነቅን ነበር። ይህ ደግሞ በማንም ሊካድ የማይችል ሃቅ ነው። ምክንያቱም ከመጋቢት 1980 ጀምሮ በነበሩት ኹለትና ሦስት ወራት ሕወሓት ይህንን አቋሙን በግልጽ በሰፊው ለሕዝብ የሚያሳውቅበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከመጋቢት 1980 አጋማሽ ጀምሮ በነበሩት ወራት፣ ሕወሓት በታሪኩ ታይቶ የማይታወቅና መደበኛ የሚባለውን ዓይነት ጦርነት ያካሔደበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት አግኝቶት በማያውቅ ደረጃ ከፍተኛ ወታደራዊ ድሎችን የተቀዳጀበት ጊዜም ነበረ። ይህ ጊዜ ሕወሓት በርካታ የትግራይ ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር ያስገባበት ነው። ከዚህ በፊት ሕወሐት ከባንክ ገንዘብ ለመውሰድ (ለመዝረፍ)፣ የታሰሩበት አባላቱን ነጻ ለማውጣት፣ ሊበቀላቸው ወይም ሊቀጣቸው በሚፈልግ ጠላቶቹ ላይ እርምጅ ለመውሰድና ለመሳሰሉት ተልዕኮዎች ጥቂት አባላቱን ለአጭር ጊዜ ወደ ከተሞች በተደጋጋሚ አስገብቶ ያስወጣ ቢሆንም፣ ከተሞችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጦር አሰልፎ ውጊያ ያካሔደው ከመጋቢት 1980 ጀምሮ ነው።

በዚህ አክሱም ከተማን በውጊያ በመቆጣጠር በጀመረው ዘመቻ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ አድዋን፣ ሽሬ-እንዳሥላሴን እና በዙሪያቸው ያሉ ትንንሽ ከተሞችን በቁጥጥር ስር ሲያውል፤ ዒዲግራት፣ ውቅሮ-ክልተ አውላሎ፣ ዓብይ ዓዲን የመሳሰሉ ትልልቅ የትግራይ ከተሞችንና በዙሪያቸው ያሉ ትንንሽ ከተሞችን ደግሞ ያለ ውጊያ ወይም በትንሽ የተኩስ ልውውጥ በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል።

የአክሱምን፣ ዓድዋንና ሽሬን የመሳሰሉ በከፍተኛ የጦር ክምችት ይጠበቁ የነበሩ ከተሞች በሕወሓት በቁጥጥር ስር መዋላቸው የወቅቱን መንግሥት (ደርግን) የጦር ኀይሉን በመቀሌና በዙሪያው ሲከማች መቀሌንና አዲስ አበባን የሚያገናኘው መስመር ጭራሽ እንዳይቋረጥ ደግሞ የተወሰነ ጦር በማይጨው ከተማና በዙሪያው አስቀምጦ ነበር። ስለዚህ ከመጋቢት 1980 ጀምሮ ሕወሓት የትግራይ ክፍለ ሐገርን 80 ከመቶ በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል ማለት ይቻላል።

ሕወሓት ትግራይን በሰፊው መቆጣጠሩን ተከትሎ በሁሉም በቁጥጥሩ ስር በገቡለት ከተሞች የሚኖረውን ሕብረትሰብ በትምህርት ደረጃ፣ በዕድሜና በጾታ ከፋፍሎ እየሰበሰበ ወደ ኹለት ወር የወሰደ ትምህርት ሰጥቷል። በዚህ ጊዜ ትኩረት ከተሰጣቸው ትምህርቶች ውስጥ የትግራይ ታሪክ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶታል። የዚህ ትምህርት መነሻ ‹‹……ትግራይ ራሷን ችላ ለሺሕ ዓመታት የኖረች አገር ነበረች…በምኒልክ ዘመን ነው በኢትዮጵያ የተወረረችውና ቅኝ የተገዛቸው…›› የሚል ሆኖ፣ ‹‹…ሕወሓት ትግራይን ከኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዛ ነጸ እያወጣ ነው…›› በሚል ሐሳብ የሚደመደም ነበር።

ይህ ትምህርት ኤርትራም ቅኝ በመገዛት ላይ ያለች አገር መሆኗን እየጠቀሰ ኤርትራን ነጻ ለማውጣት የሚደረገውን ትግል ሕወሓት እንደሚደግፍ ያሳውቃል። ከዚህ ትምህርት ጋር ተያይዞ በቪዲዮ (VCR) የሚታይ ካርታም ነበር። ካርታው ትግራይ በሰሜን ከኤርትራ፣ በምዕራብ ከሱዳን፣ በደቡብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትሰዋን አገር ናት የሚል የድምጽ መግለጫ ነበረው። በዚህ ወቅት በአዲሱ ትምህርት የተገረሙና ያዘኑ፣ ግራ የተጋቡና የተበሳጩ በጣም ብዙዎች ነበሩ። ከአጼ ምኒልክ በፊት የነበሩትንና ከአጼ ምኒልከ ጋር ጣሊያንን የተዋጉትን አጼ ዮሐንስን፣ ራስ አሉላ አባነጋን፣ ዘርዓይ ደረስን፣ ባሻይ አውአሎምን ወዘተ…. እያወሱ ከፍተኛ ክርክር ያደርጉም ነበረ። የሕወሐት ካድሬዎች ደግሞ እነ አጼ ዮሐንስ ለመሬት ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኤርትራ ምድር እየሔዱ ተዋጉ እንጂ ለኢትዮጵያ ብለው አልተዋጉም ብለው ድርቅ ያለ መልስ ይሰጣሉ።

ሰኔ እና ሐምሌ 1980 ላይ ግን ሁኔታዎች ተለዋወጡ። ደርግ ከምሥራቅና ከደቡብ ኢትዮጵያ አንስቶ ወደ ትግራይ በላከው ጦር፣ ሕወሓት ከተቆጣጠራቸው የትግራይ ሁሉም ከተሞች አፈገፈገ፤ ወደ በረሀ ምሽጉ ገሰገሰ። በእርግጥ አሯሯጡ አዲስ በመጣውና ከነ ሙሉ ሞራሉ በሚዋጋው ጦር የሚደርስበትን ከፍተኛ ሰብዓዊና የንብረት ኪሳራ ግምት ውስጥ ያስገባና ራስን የማዳን ስትራቴጂ የተከተለ ነበር።

በዚህ ጊዜ ሰምቶት የማያውቀውን የታሪክ ትምህርት ሲጋት እየተንገሸገሸ የቆየው በትግራይ ከተሞች የሚኖረው ሕዝብ የኢትዮጵያን ወታደሮች በፉከራና በሽለላ፣ በእልልታና በሆታ ነበረ የተቀበለው። ጦሩ ወደ እነዚያ ከተሞች ቢገባም የመንግሥት ተቋማት መልሰው ስላልተከፈቱና የተሰደዱት የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ቦታቸው ስላልተመለሱ ሕዝቡ በስጋት መዋጥ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ጦር አካባቢያቸውን ድጋሜ ለቅቆ እንዳይሔድ የሚማጸኑ የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው የጦር መሪዎችን አነጋግዋል። ሕወሐት አገሪቱን ሊያፈርስ የተነሳ ቡድን መሆኑን በምሬት በመናገር የኢትዮጵያ ጦር ከጎናቸው እንዲሆን ለምነዋል። ትግራይ ውስጥ ከሕብረተሰቡ መካከል የተመለመሉ የአካባቢ ሚሊሻዎች ነበሩ፤ ሚሊሻዎቹ የሕወሓትን በመሰለ አደረጃጀት የተደራጁና በየትም ቦታ እየደረሱ ሕወሓትን የሚያሳድዱ ናቸው። ሕዝቡ ይህ ሚሊሻ ተጠናክሮው ሕወሓት መቆሚያና መቀመጫ እንዲያጣ ማድረግ ካልተቻለ ኢትዮጵያ መፍረሷ አይቀሬ መሆኑን በይፋ አሳውቀው ነበር።
የትግራይ ሕዝብ የፈራው አልቀረም። የኢትዮጵያ ጦር ከሕወሓት ከነጠቃቸው ከሁሉም ከተሞች ነቅሎ በመውጣት ሽሬ ላይ ሰፈረ። ጦሩ ከሽሬና ከጎንደር ተነስቶ የሕወሓትን ዋና ምሽግ በመክበብ ሕወሓትን መደምስ አለበት በሚል ምክንያት ነበር ይህ የተደረገው። ነገር ግን ዘመቻው ሲጀመር ክርምቱ አይሎ የጦሩን ታንኮች፣ ብረት ለበሶች፣ ከባድ መሣሪያ የሚጎትቱና ከስንቅ እስከ ትጥቅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪወችን ወዘተ….. ጉዞ ስለገታ ጦርነቱ አስቸጋሪ ሆነ። ከዚህ ሌላ መረጃዎች በዚህና በዚያ ስለሚሾልኩ በኹለቱም አቅጣጫዎች የተንቀሳቀሰው ጦር ባልታሰቡ ቦታዎች አሰናካይ ግብግቦች ይገጥሙት ጀመር።

ከፍተኛ መስዋዕትነትም ለመክፈል ተገድዷል። ስለዚህ ዋናው ጦር ክረምቱ እስኪያልፍ ወደ ሸሬ ተመልሶ እንዲከርም ተወሰነ። ነገር ግን ሕወሓት ከሻእቢያ ባገኘችው የከባድ መሣሪያ ምድብተኞችና ተዋጊወች ታግዛ ሽሬ ላይ የተከማቸውን ጦር ደመሰሰችው፣ በታተነችው። ይህ ደግሞ ደርግ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ጥሎ እንዲወጣ አስገደደው።

ሕወሓት ልዩ ጨዋታውን የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው። በአንድ በኩል ትግራይ ነጻ ወጥታለች በሚል አዋጅ ለመናገር ባቆበቆቡና የኢትዮጵያ ጦር ከዚህ በኋላ ጸንቶ መዋጋት ስለማይችል ወደ አዲሰ አበባ መገስገስ አለብን በሚሉ አባላቱ መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ተነክሮ እያለ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ከጥቂት ጓዶቻቸው ጋር ኢሕአዴግን ፈጠሩ። ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተጫነ። የኢትዮጵያን ዕጣ ወሳኝ ሆኖ ብቅ አለ። የትግራይ ሕዝብም ኢትዮጵያ ባልታሰበ መንገድ ከብተና የምትድንበት፣ ትግራይም የኢትዮጵያ አካል ሆና የምትቀጥልበት አጋጣሚ መጣ ብሎ ስላሰበ ልጆቹን ወደ ሕወሐት ካምፕ መርቆ መላኩን ቀጠለበት።

የእነ አቶ መለስ ፈጠራ ቀጥሎ ኦሕዴድ ከዚያም ደኢሕዴን ተፈጠሩ። ኢሕዴንም ብአዴን ተብሎ ዳግም ተፈጠረ። ከዚያም እስከ አሁን ያልወከሉትንና ያልተቀበላቸውን ሕዝብ ወክለዋል ተብለው በሥልጣን ላይ ቆዩ።

የ2010ን ለውጥ ተከትሎ ኦሕዴድ ወደ ኦዴፓ፣ ብአዴን ወደ አዴፓ ስማቸውን በመቀየር የሕወሐት አሻንጉሊት መሆናቸው ያከተመ፣ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው እንዳበቃ ለማሳየት ሞከሩ። አሁን ደግሞ በሕወሓት ላይ የማመጹ ተራ የኢሕአዴግ ሆነና ስለ ‘ኢብፓ’ (የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ) መነገር ጀመረ። አዲሱ ፓርቲ ወሬ ከመጀመሩ ‘ኢብፓ’ ስሙን ቀይሮ ‘ብፓ’ (ብልጽግና ፓርቲ) በሚል መጠራት ጀመረና ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የተወገደው ‘ማንን ደስ ይበለው ተብሎ ነው?’ በሚል ማነጋገር ጀመረ።

በዚህ ጉዳይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የሚባሉት አመራሮች በጥበብ ሳይሆን በእልህ በመፎካከር ላይ ያሉ ይመስላሉ። ሕወሓት በውህደቱ ውስጥ የለሁበትም ብሎ ራሱን ከማግለል ይልቅ ሕገ-መንግሥቱ እና ሕግጋት ተጣሱ፣ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ሊናጋ ነው፣ የቀድሞው የአፈና ስርዓት ሊጀመር ነው፣ አገር ሊፈረስ ነው…ወዘተ በተዘዋዋሪ በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እየሞከረ ነው። እንገነጠላን ወይም የትግራይ ዲፋክቶ መንግሥት መመሥረት አለበት የሚሉ ወገኖችን አሰማርቶ አቅሉና መቆጣጠር የተሳነው መውረግረግ ውስጥ ገብቶ ይታያል።

ዕድሜ ጠገብ የሕወሓት ልሳን የሆነው ‹ወይን መጽሔት›ና በሕወሓት እንደተፈጠረ የሚነገርለት ‹ባይቶና› የተባለው የትግራይ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ወዘተ… ስለ ዲፋክቶ መንግሥትነት ሰፊ ጉዳይ በማሰራጨት ላይ ቢሆኑም፣ የሕወሓት ባለሥልጣናት በድርጅቱ ልሳን ላይ ለንባብ ስለበቃው ጉዳይ ምንም እንደማያውቁትና የድርጅቱ (የሕወሓት) ሐሳብ እንዳልሆነ አስመስለው ሲናገሩ ተሰምተዋል።

የሕወሐት ይሁን በትግራይ የሚሠሩ ሌሎች መገናኛ ብዙኀን፣ ከሕወሓት ያፈነገጠ አካሔድ አልለመዱምና ሕወሓትና አውራዎቹ ለዲፋክቶ መንግሥት ሐሳብ ባይተዋር መምሰል ድራማ ከመሆን አያልፍም። ሕወሓት በተከፋፈለችበት አጋጣሚ ወይን ጋዜጣ ክፍፍሉን በሚመለከት ሚዛናዊ ለመሆን ሞክራ ወደ አንባቢ እጅ ከመግባቷ በፊት፣ ተከምራ እሳት እንደ ወደመች ይታወቃልና፤ ወይን መጽሔት እነ ደብረጽዮን የማያውቁትን ነገር ለንባብ አብቅታለች መባሉ የሚዋጥ ወሬ አይደለም።

እርግጥ ነው፣ ከወራት በፊት ሕወሓት ፌዴራላዊ (ፌዴራሊስት) ጓዶቼ ናቸው ያለቻቸውን፣ ከ60 በላይ መሆናቸው የተነገረላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች መቀሌ ላይ ሰብስባ አብሮ ስለመሥራት፣ ፌዴራሊዝምንና ሕገ-መንግሥቱን ለማስቀጠል ሲባል በመጭው ምርጫ ተደጋግፎና ተባብሮ በመወዳደር ምክር ቤቱን ስለ መቆጣጠር ጭውውት ማድረጓ የሚታወስ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች አበክረው ስለተቃወሙት ‘ጊዜው አሁን አይደለም!’ ተብሎ ተተወ እንጅ የቬንዙዌላውን ወይም የአዲሰ አበባውን “ባለ አደራ መንግሥት” ስለ ማቋቋምም ተወርቶ ነበረ።

በአጭሩ ሕወሓት የቀድሞ አገልጋዮቿን እንደ አሻንጉሊት አድርጋ የምትጫትበትን ቀዳዳ እያነፈነፈች ብዙ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኗ የሚታበል ሃቅ አይደለም። የአሁኑን ውህደት በሚመለከት የምትሠራው ድራማም የዚህ ጨዋታ አካል ነው። በእርግጥ ‹ወጣ-ገባ ነበረ› እየተባለ ውህደቱ ሕወሓትን ሰንጥቋታል ወይስ ትቷታል የሚለው ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል።

በሌላ በኩል የቀድሞ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆነ ውህደቱን ተቀብለነዋል የሚሉት የታዳጊ ክልሎች መሪ ድርጅቶች አዲሱን ውህደት ተአምር ሰሪ እንደሆነ አድርገው በመስበክ ላይ ተጠምደው እየታዩ ነው።

እዚህ ላይ የመጀመሪያውና ትልቁ አሳሳቢ ነገር ከቀድሞው የኢሕአዴግና ከአሁኑ የብልጽግና ፓርቲ አመሠራረት ምን ልዩነት አለ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ኢሕአዴግ በአቶ መለስ ዜናዊ ፈጣሪነትና በጥቂት የሕወሓት አውራዎች ቡራኬ ተጠፍጥፎ፣ በሕዝብ ከላይ የተጫነ ቡድን እንደሆነው ሁሉ የአሁኑ የኢሕዴግ ውህድ ልጅ ነው የተባለው የብልጽግና ፓርቲስ የአንድ ወይም የጥቂት ሰዎች የፈጠራ ውጤት ነውን?

ለመሆኑ ፓርቲው ሳይወለድ እንዴት እና በማን ስም ወጣለት? የአብዮታዊ ዴሞከራሲ ምትክ ነው የሚባለውን መደመርስ እንዴት በፓርቲው ሳይወለድ መመሪያ ሆነ? ብልጽግና ፓርቲ እንደ ኢሕአዴግ ተቀበል በሚል ትዕዛዝ ነገር ግን በአስመሳይ ጭብጨባ በማንም ላይ እየተጫነ ነውን? አጨብጫቢነት መቼም ቢሆን ለሕዝብና ለአገር ሊጠቅሙ ያሰቡ አለቆችና ጭፍሮች ባህሪ ሊሆን አይችልምና በማስተዋል መራመድ ተገቢ ነው!!

ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here