ዘጠኝ የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ሠራተኞች “በፓርኩ የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን አጋልጣችኋል” በሚል ከፓርኩ እንድንወጣ ተደርገናል አሉ

"ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ የተደረጉት ዘጠኝ ሠራተኞች በፓርኩ ላይ ከፍተኛ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ናቸው" የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን

0
282

አርብ መስከረም 11 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች መካከል በሚገኘው ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ሕገወጥ የሰዎች ሰፈራን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ብልሹ አሰራሮች እየተፈጸሙ መሆኑን ተከትሎ፤ “ለምን?” ብለን በመጠየቃችን፣ ረጅም ዓመት ስንሰራበት ከነበረበት ፓርክ እንድንለቅ ተደርገን ሌሎች ፓርኮች ላይ ተመድበናል ሲሉ ዘጠኝ የፓርኩ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሠራተኞቹ “በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ለበርካታ ዓመታት ስናገለግል ቆይተን፣ ትዳር መስርተን፣ ልጆች ወልደንና ቤት ሰርተን በሰላም በተቀመጥንበት “በፓርኩ የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን ለምን አጋለጣችሁ?” በሚል ከፓርኩ ያለፈቃዳችን አስወጥተው፤ ወደ ሌሎች ፓርኮች መድበውናል” ነው ያሉት።

“ኑሯችንን በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ አካባቢ አድርገን በመንግሥት በኩል የተጣለብንን ሃላፊነት በአግባቡ እየተወጣን የነበረ ቢሆንም፤ ያለፈቃዳችን ከፓርኩ እንድንወጣ መደረጉ ቤተሰቦቻችን እንዲፈናቀሉና ልጆቻችን ትምህርታቸው እንዲያቋርጡ አድርጓል።” ብለዋል።

“ከፓርኩ ውስጥ 25 ኪሎ ሜትር ያክል ሕገወጥ ሰፋሪዎች ገብተው መኖሪያ ቤት እንዲሁም ትምህርት ቤት ገንብተው ለእርሻ ሥራ ኹሉ እየተጠቀሙበት መሆኑ እየታወቀ “ለምን ይሄን ጉዳይ ማስቆም አልተቻለም?” ብለን በጠየቅን፤ ጉዳዩ ወደ ብሄርተኝነት ዙሮ 7 የአማሮ ኬሬ ዞን ብሄር ተወላጆችንና ኹለት የጋሞ ዞን ብሄር ተወላጅ የሆኑ፣ በድምሩ ዘጠኝ የፓርኩ ሠራተኞች ወደ አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ፣ ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ እና ወደ ሌሎች ፓርኮች ሄደን እንድንሰራ አድርገውናል።” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን መኮንን፤ የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ በኦሮሚያ ክልል እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መካከል የሚገኝ በመሆኑ በአካባቢው በተደጋጋሚ የጎሳ ግጭት ይነሳ እንደነበር አውስተው፤ “ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ የተደረጉ ዘጠኝ ሠራተኞች ፓርኩ የጎሳ ግጭት እንዲካሄድበት እያደረጉ ያሉ እና የተለያዩ የፓርኩን ሚስጥሮች ከመዝገብ ቤት አውጥተው ለሌላ አካል ይሰጡ የነበሩ ናቸው።” ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በፓርኩ ውስጥ ከሰል እንዲወጣ ሲያደርጉ የነበሩ፣ በሕገወጥ መንገድ የፓርኩን እንጨት ሲቆርጡ የነበሩ ሰዎችን ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ፤ እንጨቱን ተረክበው ለሌላ ሰው ይሸጡ የነበሩ እና በአጠቃላይ ፓርኩ እንዳይረጋጋ ከፍተኛ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ናቸው” ሲሉ ነው የገለጹት።

በመሆኑም፤ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ሲነገራቸው የቆየ ቢሆንም፤ ሊያሰተካክሉ ባለመቻላቸው ፓርኩን ለቀው ሌላ ፓርክ ተመድበው እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም፤ “በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ሕገወጥ ሰፋሪዎች አሉ።” ስለመባሉ ትክክል መሆኑን በማመን፤ ለፓርኩ ችግር ፈጣሪ የሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት ለመፍታት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ የተመሰረተዉ በ1967 ሲሆን፤ ስፋቱም 514 ሰኩየር ኪሎሜትር ነው፡፡ ከዚህም 87 ስኩየር ኪ.ሜ (15 በመቶ) የሚሆነው ከአባያና ከጫሞ ሃይቆች የተከለለ የፓርኩ ክፍል ዉሃማ ሲሆን፤ ቀሪዉ የየብስ አካል ነዉ፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here