የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሕዝብ እምነትና ተስፋ አምክኗል ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

0
447
አርብ መስከረም 11 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በዘመነ ኢሕአዴግ ለተፈጠሩ ስህተቶች ኹሉ ይቅርታ ጠይቆ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው የብልጽግና ፓርቲ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እምነትና ተስፋ አምክኗል ሲሉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ እናት ፓርቲ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ትናንት ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።
“በአሁናዊ የአገራችን ኹኔታ የእልህ፣ የፉክክር እና የአሻጥር ፖለቲካ ብቸኛ የእውቀት መገለጫ፣ የሕዝብ ሰቆቃ፣ ስቃይ፣ እልቂት እና ሥር የሰደደ ድህነት ደግሞ ብቸኛ የስልጣን ማስጠበቂያ መንገዶች ሆነዋል፡፡” ሲሉም አክለዋል።
“ከሰሜኑ ጦርነት በቂ ትምህርት መውሰድ ያልቻለው የብልጽግና መንግሥት፤ ዛሬም የአገር ዳር ድንበርን ከወራሪ ጠላት ለመከላከል የተቋቋመን የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ሕዝብ ላይ በማሰማራት ታሪክ ይቅር የማይለው የወንድማማች ጦርነት በማካሄድ ላይ ነው፡፡” ብለዋል።
በጦርነቱ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያን በአሰቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፣ ሃብት ንብረታቸውም እየተዘረፈ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ “ሕዝባችን ሥር በሰደደ የኑሮ ውድነት እና በማያባራ ጦርነት ተጠምዶ በቀቢፀ-ተስፋ እያነባ ነው፡፡” በማለት አስገንዝበዋል።
“ኢትዮጵያ አገራችን ጥንታዊ የመንግሥት ሥርዓት እንዳላት አገር፤ መንግሥትና የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡ ግለሰቦች በሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት ሊመሯት ይገባል፡፤” ሲሉም አሳስበዋል።
“ከዚህ ውጭ ቀጣዮን ትውልድ አገር አልባ አድርጎ ለማስረከብ መሞከር ከመቶ ሚሊየን የሚልቀውን ሕዝብ መናቅ፤ በቀጣይ እጣ ፈንታችንም ላይ መሣለቅ ነው፡፡” ብለዋል።
በአገሪቷ የሚስተዋለውን ዘርፈ ብዙ ችግር የዳሰሰው መግለጫው፤ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ከተጋረጠባቸው አደጋ ለመታደግ ከተፈለገ ሊተገበሩ ሰባት ነጥቦች መተግበር አለባቸው ሲል አስፍሯል።
የመጀመሪያውም መንግሥት ለለሚመለከታቸው አካላት ኹሉን አቀፍ የአገር አድን ድርድር እንዲደረግ ፍቃደኝነቱን በመግለጽ ይፋዊ ጥሪ እንዲያቀርብ የሚል ሲሆን፤ ቀጣዩ በንጹህን ዜጎች ላይ የሚፈጸም የጅምላ ግድያና የድሮን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ ነው ብሏል።
እንዲሁም የመንግሥት ኃይሎች ከሰፈሩባቸዉ የመደበኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአስቸኳይ በመልቀቅ ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛ ተግባራቸው እንዲሰማሩ መድረግ እንዳለበት ያሳሰበው የፓርቲዎቹ የጋራ መግለጫ፣ ባልታወቁ ሥፍራዎች በጅምላ ታጉረው የሚገኙ ዜጎቻችን የጅምላ ማጎሪያዎቹ ይፋ ተደርገዉ በአስቸኳይ እንዲፈቱና ተዋጊ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ሕጎችንና የጄነቫ ስምምነት እንዲጠብቁ ጠይቋል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አገር ከገባችበት ችግር በአሰቸኳይ እንድትወጣ ድርድር እንዲደረግ ጫና እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
መንግሥት እነዚህን የመፍትሄ ሃሳቦች ቸል በማለት ችግሮችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት በሚያደርገው ሙከራ በአገር ላይ ለሚደርሰው የከፋ ጉዳት በታሪክ፣ በሞራልም ሆነ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆንም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አስፍረዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here