ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ጦርነት ምክንያት ያዘገየውን የ680 ሚሊየን ዶላር የባለ ብዙ ዘርፍ ዓመታዊ ድጋፍ ለመልቀቅ የሚያስችል ስምምነት ከገንዘብ ሚኒስትር ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ በአውሮፓ ኅብረት የዓለም ዓቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን እና በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ መካከል የተደረገ ሲሆን፤ ድጋፉ የኹለቱን ወገኖች ስትራቴጂካዊ ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት እንደሚሆን ተመላክቷል።
ድጋፉ በኢትዮጵያ የልማት መርሃ ግብሮችን፣ በሰው ሃብት ልማት እና አስተዳደር እንዲሁም ሰላምን ማሻሻል ላይ ትኩረቱን ያደረገና የኹሉንም ኢትዮጵያውያን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያለመ መሆኑም ተነግሯል።
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ የህብረቱ የበጀት ድጋፍ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት የሚኖራት ትብብር “ስትራቴጂካዊ ፋይዳው” ከፍ ያለ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
የተደረገው የ650 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ቦታዎች ለመገንባትና የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን ለማናከናወን እንደሚጠቅም አመላክተዋል።
ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን በበኩላቸው፤ ድጋፉ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለመልሶ ግንባታና ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እንደሚውል ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን፣ የሽግግር ፍትህን ለማረጋገጥና የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ለማከናወን የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ በፈረንጆቹ 2024 እስከ 2027 ለአራት ዓመታት እንደሚቆይም ተመላክቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በጥር ወር 2021 ለኢትዮጵያ ሊያደርገው የነበረውን የበጀት ድጋፍ በትግራዩ ጦርነት ምክንያት አቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡



