የፍትህ ዘርፉ ማሻሻያዎች ከየት ወዴት?

0
1250

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ህገ መንግስት ከተተገበረ በኋላ ዜጎች የተጎናፀፏቸውን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባግባቡ እንዲተገበሩ ለመጠየቅ ብዙ አመት አልፈጀባቸውም። ታዲያ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ሲል የቆው የመብቶች ጥያቄ በተለይ በ1997 ከተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ እና እሱን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያ በሰፊው ገንፍሎ ከወጣው ተቃውሞ በኋላ ወደ ሌላ ምእራፍ ተሻግሯል። መንግስት በሃይል ያዳከመው ጥያቄ በድጋሚ ከአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ትግበራ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ብሎም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ቁጣን በመቀስቀሱ የፍትህ ጥያቄ ተፋፍሞ ቀጠለ።

ይህ የህዝብ የፍትህ ጥያቄ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ባመጣው ለውጥ ወደ ፊት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና አስተዳደራቸው ህዝቡ ላይ ለደረሰው በደል በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በፖለቲካ ምክኒያት ለታሰሩ ከ 10ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ምህረት ተደርጎ የፍትህ ስርአቱን ለማሻሻል ተሞክሯል።

አፋኝ ህጎችን በማሻሻል የገባሁትን ቃል ፈጽማለሁ ያለው የመንግሰት ቃል ከምን ደረሰ? የፍትህ ተቋማቱ አካላት የሆኑት የፍርድ ቤት እና የዓቃቤ ህግ ባለሞያዎች ምን ይላሉ? ባጠቃላይ ብዙ የተባለለት የፍትህ ስርአት ለውጥ የት ደረሰ በሚለው ሃሳብ ላይ የአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ሐተታ ዘማለዳን አሰናድታለች።

በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቃሊቲ ምድብ ችሎት በያዙት መዝገብ ላይ ለሶስተኛ ግዜ ዳኛ በመቀየሩ ምክንያት ለወራት ደንበኞቻቸው ላይ እንግልት እና ያለአግባብ ወጪ ውስጥ መድረሱን መልካሙ (ስማቸው የተቀየረ) ይናገራሉ። በጥብቅና ሞያ ውስጥ ለረጅም አመታት የቆዩት መልካሙ በጣም በቀላሉ አልቆ መወሰን በሚገባው መዝገብ ዳኛ በተቀየረ ቁጥር ክርክር የተደረገበትን ጭብጥ እንዳዲስ በመያዝ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን በመስጠታቸው መቸገራቸውንም ይናገራሉ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዳኞች እና ጠበቆች እንደሚሉት ከወራት በፊት በፌደራል ፍርድ ቤቶች በተካሄደው የዳኞች ሹመት ምክንያት ብዙ ልምድ ያላቸው ዳኞች እድገት አግኝተዋል። ይህም በተለይ ከፍ ያለ እውቀት፣ ልምድ እና አቅም የሚጠይቁ መዝገቦች ላይ የሰው ኃይል ለመጨመር የሚረዳ ቢሆንም በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ክፍተት የፈጠረ ሆኗል። በያዝነው አመት በቁጥር ብዛት ያላቸው አዳዲስ ዳኞች እና ረዳት ዳኞች ቢመጡም ከችሎት አመራር ጀምሮ ከፍተኛ የአቅም ማነስ እንደታይባቸው በተለይ ከጠበቆች ዘንድ የሚነሳ አስተያየት ነው።

‹‹አዳዲስ ዳኞች ገና የፍርድ ቤቶቹን ሰንሰለት ስላለመዱት በተለይ በሙስና ረገድ ብዙም አያስቸግሩንም፣ ነገር ግን ከአቅም ጋር በተያያዘ የሚታየው ክፍተት ከበፊቱ የባሰ ነው›› ሲሉ በማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ የሆኑት ግለሰብ ይናገራሉ። ‹‹ዳኞች በትምህርትም ሆነ በልምድ ብቁ የሆኑበት ችሎት ሌላ ቢሆንም በፍላጎታቸው መሰረት በሚል ምንም ወደማያውቁት ችሎት ተዘዋውረው እንዳዲስ ጀማሪ ሲሆኑ እየተመለከትን ነው›› ሲሉም ይናገራሉ።

ከመዝገብ ውስጥ ማስረጃዎች ተለይተው ይጠፋሉ የሚሉት መልካሙ አንዳንዴ ባስ ሲልም ሙሉ መዝገብ የሚሰወርበት አጋጣሚም እንዳለ ይናገራሉ። የፍርድ ቤቶች መዝገብ ቤት መዝገቦቹ የያዙትን እውነት የማይመጥን የብዙዎችን ሕይወት በቸልተኝነት እና በማይገባ አያያዝ አደጋ ላይ የሚጥል አንደሆነም ይናገራሉ። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ህገወጦች ከዳኞች ወይም ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር የሚያደርጉት የማስረጃ የማጥፋት መንገድ እንደሆነም ይናገራሉ።

‹‹አብዛኛው ዳኛ ለህሊናው ያደረ ነው ብዬ አምናለሁ፣ ነገር ግን እነዚህን ዳኞች ሳይቀር ተስፋ የሚያስቆርጡ በአንድ ጉዳይ ላይ በመቶ ሺዎች ገንዘብ የሚቀበሉ ዳኞች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ነው›› ሲሉ ይኮንናሉ። ‹‹አንድ ዳኛ የፈለገውን ያህል ሃቀኛ ሆኖ ፍርድ ቢሰጥ ይገባኝ ላይ ጉቦ የሚቀበሉ ዳኞች ውሳኔውን ስለሚሽሩበት ከግዜ ወደ ግዜ እተሰላቸ ወይ ተስፋ እየቆረጠ ሄዶ አንዳንዴም ሙስና ተቀባይ ይሆናል፡፡››

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሚሉት አንዳንድ ዳኞች የሙስና እና የማን አለብኝ ባይነታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያውቁት ይግባኝ የተባለበት መዝገብ ላይ ከሁለቱም ወገኖች ገንዘብ ተቀብለው መዝገቡን ወደ ለሁለቱም ውሳኔ በመከልከል መዝገቡን ወደ ስር ችሎት ይመልሱታል፡፡ ይህም የህጉን ክፍተት በመጠቀም የሚደረግ ድርጊት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቀጥታ ጉቦ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ከዳኝነት ወጥተው የጥብቅና ፈቃድ የሚያወጡ ሰዎች የፍርድ ቤት ትውውቃቸውን ያላግባብ በመጠቀም መዝገቦቻቸው ላይ ውለታ እንደሚያሰሩ በዳኞች መካከል የሚታወቅ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ይሄ ማለት ግን አብዛኛው ዳኛ በዚህ ውስጥ ያለ ነው ማለት አይደለም፣ ዳኞች ማህበራዊ ህይወታቸው ብዙ ጫና ያለበት ነው›› ይላሉ፡፡ ‹‹ከፈረድንበት ሰው ጋር በታክሲ ተጋፍተን ነው የምንሄደው፣ የዳኛ ደመወዝ የሚሰራውን መዝገብ ልክ የሚያስተናግደውን መዝገብ ልክ ያላማከለ ሆኖ የቢሊዮን ብር መዝገብ ያያሉ›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ‹‹የዳኝነት ስራ ጫና ከወንዶች ባላነሰ በተለይ ወልደው በተመለሱ እና በነፍሰጡር ዳኞች ላይ የበረታ ነው፣ እርስ በእርስ ካልተጋገዝን አንድ አካውንታንት ሴት ያላትን ረፍት ያህል ነው ጫና የበዛበትን ስራ የምትስራ ዳኛ የሚኖራት›› ሲሉ ለአዲስ ባለዳ ተናግረዋል፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ 104ቱ ሴቶች ሲሆኑ ቀሪ 246ቱ ወንዶች ናቸው፡፡ በፍርድ ቤቶቹ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት በመሆን መአዛ አሸናፊ የተሾሙ ሲሆን ከሹመታቸው በኋላም በመጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሴት ምክትል ፕሬዘዳንቶች እንዲሾመ ተደርጓል፡፡
በፍርድ ቤቶች ስላለው የሙስና ድርጊት እንደማንኛውም ሰው የፍርድ ቤቱ አስተዳደር ይሰማል የሚሉት በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ የሆኑት ተስፋዬ ነዋይ ናቸው። በግል ከሚወሩ ሃሜቶች ባሻገር ማስረጃ ይዘው ወደ አስተዳደር ኃላፊዎች በመምጣት ክስ አይመሰርቱም ሲሉም ይሞግታሉ። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ አዲስ የኢንስፔክሽን ክፍል በማዋቀር እና በማጠናከር የመዝገቦችን ሂደት በመመርመር ለብልሹ አሠራር በር የከፈቱ ውሳኔዎችን መከታተል የሚያስችል ስርአት በመዘርጋት መፍትሄ እንደሚሰጥ ይናገራሉ።

መዝገብ ወይም ማስረጃ መጥፋት መኖሩን የሚያምኑት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ይህንን ለመፍታትም መዝገቦችን በዲጂታል ምልክ ቀይሮ የማስቀመጥ ሥራ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጀምሮ መቋረጡን ያስታውሳሉ። የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ላይ ለሦስት አመት የተዘረጋ እቅድ መተግበር መጀመሩን እና ከዋና ዋና ስራዎች መካከልም የአይቲ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ መሆኑንም ገልፀዋል።

‹‹አንድ መዝገብ በዳኛ፣ በችሎት በፀሃፊ ወይም በሬጅስትራር መሃል ሲለዋወጡ ፎርም ማስሞላት የቱ መዝገብ ማን ጋር አለ የሚለውን በማረጋጋጥ መዝገብ ሲሰወር ወይ ማስረጃ ሲወጣ ተጠያቂነት ለማምጣት ያስችላል›› እንደ ተስፋዬ ገለጻ። ‹‹በቅርቡም የወሰድናቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች አሉ፣ በማስጠንቀቂያ ያለፍናቸውም እንዳሉ ሆነው እስከ ወንጀል ድረስ የምንጠይቃቸው ይሆናል›› ብለዋል።

የፍርድ ቤቶች የሶስት አመት መሪ እቅድም በቀዳሚነት የዳኝነት ነፃነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ይህም ዳኞች ከውጪም ከውስጥም ከጫናዎች ነፃ እንዲሆኑ ይሠራል ብለዋል። ‹‹አንድ ዳኛ ከውጫዊ ጫና ነጻ እንዲሆን እንደሚያስፈልገው ሁሉ ከግሉ ጨናም ነፃ መሆን ይገባዋል›› ብለው ‹‹ይህ በቤተሰብ፣ በጓደኝነት፣ በትውውቅ ወይም በግል አመለካከት ምክኒያት ህጎችን ያለአግባብ መተርጎምን ይጨምራል›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡

በ2012 የበጀት አመት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመታዊ በጀት በፕሬዘዳንቷ መአዛ አሸናፊ ለመጀመሪ ግዜ ለተወካዮች ምከርቤት ቀርቦ መጽደቁ የዚህ አካል እንደሆነም ሲገለፅ ቆይቷል። የዳኝነት አገልገሎትን ተደራሽነት እና ውጤታማነት ማሳደግ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በጥቅምት አንድ ወደ ሥራ በገባው አዲስ የዳኞች ምደባ መሰረትም 176 ዳኞች በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የተደለደሉ ሲሆን አንዳንድ ችሎቶች እንዲታጠፉ፤ እንዲሁም ከፍተኛ የመዝገብ ፍሰት ያለባቸው ችሎቶች ደግሞ ቁጥራቸው እንዲጨመር መደረጉን ተስፋዬ ይናገራሉ። በተጨማሪም አዳዲስ ዳኞችን እና ረዳት ዳኞችን ለመቅጠር ሂደት መጀመሩን እና በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ፈተና እንደሚገቡም ይናገራሉ። በዚህ ሂደት በሕግ ትምህርት ቤቶቸ ላይ ያለውን የጥራት ማነስ ተመልክተናል ስለዚህም ተባብረን እንሠራል ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በልደታ ፍርድ ቤት ዙሪያ ከ 15 አመት በላይ በራፖር ፀሃፊነት እየሰሩ ያሉት ግለሰብ እንደሚሉት ራፖር ጸሃፊ እንደሚጠቅም ስለሚያውቁ ፍርድ ቤቶች አይከለክሉም። ነገር ግን ፍርድ ቤት ውስጥ እንኳን ለመግባት እንከለከላን። ስለዚህ በየአጥር ጥጉ ጥላ ይዘን እንሰራለን ሲሉ ይናገራሉ። በቀን እስከ ሶስት መቶ ብር በአማካኝ እንደሚሰሩ የሚናገሩት አዛውንት በተለይ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ጠበቆች ከፍተኛ ዋጋ ስለሚጠሩ ክስ፣ መልስ እና ሌሎች ሰነዶችን በርካሽ ዋጋ እንሰራለን ይላሉ። በአንድ ወቅት ልደታ ግቢ ውስጥ እንድንሰራ ቢፈቀድም መልሰው አስወጥተውናል ሲሉ ይናገራሉ። ከሚያገኙት ገቢም የልጅ ልጃቻውን ጨምሮ አራት ቤተሰብ ያስተዳድራሉ፡፡

‹‹ለኛ ደህና የሚባለው ገቢ ደንበኛን ከጠበቃ ጋር ማገናኘት ሲሆን ጠበቆቹም አንዴ ደንበኛ ከሰጠናቸው ቀሪ የኮሚሽን ክፍያ ለመስጠት አይፈልጉም፤ በአንድ ጉዳይ በትንሹ ሁለት ሺህ ብር እናገኛለን›› ይላሉ።

ተስፋዬ እንደሚሉት የጠበቆችን ፈቃድ እና ተግባር ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በበላይነት የሚከታተለው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ስለሆነ የራፖር ፀሃፊዎች ጉዳይ ከግምት ቢወስደው መልካም ነው። ምንም አይነት የሕግ ተጠያቂነት ወይም የትምህርት ዝግጅት ሳይኖራቸው የሕግ ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችም ካሉ፤ በተለይም በችሎት ያለፈቃድ የሚገኙት ላይ ዳኞች ስልጣን ቢኖራቸውም ዓቃቤ ሕግ የራሱ ሚና ይኖረዋል።

ራፖር ፀሃፊው እንደሚሉት ግን በደሃ ደንብ ጉዳያቸው እንዲታይላቸው የሚፈቀድላቸው ተከራካሪዎች እንኳን ክስ፣ መልስ እና ሌሎች አቤቱታዎችን ከ ሁለት መቶ ብር በላይ ነው የሚያጽፉት፣ ይህም በየቀጠሮው የሚሆን ስለሆነ ወጪው ከአቅም በላይ ነው።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባዩ ተስፋዬ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዳኝነት ክፍያ ከሃምሳ አመት በፊት የተዘጋጀ እና በገፅ በጣም ዝቅተኛ ክፍ የሚከፈልበት ነው፤ ይህም በአለም ላይ ዝቅተኛ ከሚባሉት ይከመደባል ይላሉ። አቅማቸው ለማይፈቅድ ተከራካሪዎች ሕጉ በደሃ ደንብ ከእነዚህ ወጪዎች ነጻ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም ጠበቆች በአመት በትንሹ 50 ሰአት ነጻ የህግ አገልግሎት እንዲሰጡ በሕግ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች ለወንጀል ጉዳዮች በህጉ መሰረት እየታየ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ተከላካለይ ጠበቃ ያቆማሉ፡፡

በተደጋጋሚ በችሎቶች ላይ የተከላካይ ጠበቆች የብቃት ማነስ ይታያል የሚሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዳኛ ናቸው፡፡ ተከላካይ ጠበቆች ከሚታይባቸው ከፍተኛ እውቀት ማነስ ባሻገር ባግባቡ ግዜ እና ሰአት አክብሮ ለሚከራከሩላቸው ሰዎች ያለመምጣት እንዲሁም ቀደም ብለው ሳይዘጋጁ በችሎት ለመታየት ብቻ ብቅ ብለው የሚጠፉ ሲሆኑ እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡

‹‹አገሪቱ ውስጥ ያሉት ጠበቆች እና የሚሰጡት የነጻ የሕግ ድጋፍ እና ጥብቅና አገልገሎት ይመጣጠናል ለማለት ያስቸግራል፣ ስለዚህም ይህንን ሂደት በበላይነት የሚመራው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል›› ሲሉ ተስፋዬ ይናገራሉወ። ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ሌላው ለወጪ የሚዳርግ መሰረታዊ ምክንያት ነው፤ የጉዳዮች ፍሰትና አመራር ሰነድ ተዘጋጅቶ ዋና ዋና የፍርድ ሂደቶች ላይ ዳኞች ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠማቸው በቀር በግዜ እንዲያስተናገዱ ይደረጋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኞች አስተዳደር አዋጅ በመሻሻል ላይ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ አስታወቋል።

በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታየው ችግር የብቃት ችግር ነው ማለት ከዚህ ቀደምም ሲባል የነበረ ነገር ግን ከእውነታው የራቀ ነው ሲሉ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ የሆኑት ሔኖክ አክሊሉ ይናገራሉ። በተለይም በቅርቡ በሽብር ተጠርጥረው ለታሰሩ ግለሰቦች በጥብቅና ሲቆሙ የነበሩት ሔኖክ ፍርድ ቤቶች ውስጥ አሁንም በቀድሞው ስርአት ታማኝነታቸው ታይተው የተሾሙ ዳኞች ያሉበት ነው፤ ይህም መሰረታዊውን የነጻነት እና ገለልተኝነት ሚናቸውን ያጡ ፍርድ ቤቶች እንዲኖሩን ያደረገ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

‹‹ከዚህ ቀደምም ቢ ፒ አር በሚል ፍርድ ቤቶች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ያልተሳካው ፍርድ ቤቶች ውሰጥ ያለው በሽታ ሌላ መንግሥት መርፌ ካልወጋሁ የሚለው ቦታ ሌላ ስለሆነ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ፍርድ ቤቶች አሁንም ለሕግ አስፈፃሚው ታዛዥ በሆኑ ሰዎች የተሞሉ ናቸው›› ያሉት ጠበቃው ‹‹የፍትህ ሪፎርም ቃሉ ራሱ ፍትህን የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ያስረዳል፤ ነገር ግን ያንን አላየንም፤ ይህንን ለማምጣትም ዋናው የሚያስፈልገው የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው እንዲዋቀሩ ማድረግ ነው›› ሲሉም ያስረዳሉ።

ዓቃቤ ህግ
ኢትዮጵያ ለላፉት 11 አመታት በሥራ ላይ አውላ ስትጠቀምበት የቆየችው የፀረ ሽብር አዋጅ በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲደርስበት ከነበረው ትችት ባሻገር ዜጎች የዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲጣሱ ምክንያት ሆኗል በሚል የተለያዩ ወቀሳዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። አሁንም ድረስ በሥራ ላይ ያለውን ይህንን አዋጅ በመጠቀም ለደረሱ ጉዳቶች ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይቅርታ እንዲጠይቁ ምክንያት ሆኗል።
የሽብር አዋጁን በመጠቀም በተለይ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄዎችን ለማንሳት ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ እየተጠቀመበት ነው በሚል የተለያዩ ወቀሳዎችን ለማስተናገድ ግን አጭር ጊዜ ነበር የወሰደው። በማርቀቅ ሂደት ውስጥ ካሉ ሕጎች ውስጥ በአንገብጋቢነት ከተያዙት መካከል ነው የተባለው ይህ አዋጅ ለአንድ አመት ያክል በዚህ ሂደት ውስጥ ቆይቶ በቅርቡ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ውይይት የሕዝብ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

አዋጁ የሽብር ድርጊት ምንድን ነው የሚለውን ከመተርጎም ጀምሮ ብዙ ለትርጉም ክፍት የተደረጉ እንዲሁም ሳይተረጎሙ በግርድፉ ያለፉ እና የዜጎችን መብት ለመጣስ የሚመች እንደነበር ሕጉን ለማሻሻል የተሠራው ጥናት ያመላክታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፍቃዱ በበኩላቸው ከአራት የማይበልጡ መዝገቦች ብቻ በስራ ላይ ባለው ሽብር አዋጅ ክስ የተመሠረተባቸው፤ በዚህ ህግ ስር መውደቅ የሚችሉ ወንጀሎችን ሆን ብለን በወንጀል ሕጎች እንዲዳኙ ለማድረግ እየሞከርን ነው ይላሉ። በተለይ ከአልሸባብ በኩል የሚፈጸሙ ወንጀሎች በዚህ አዋጅ ክስ እንዲመሰረት አድርገናል ሲሉ ይሞግታሉ።

‹‹በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ በሰኔ 15/2011 በተፈፀመው ወንጀል በአዲስ አበባ 146 ከሚሆኑ ከተያዙ ሰዎች ብዙዎቹ ላይ በሽብር ሕጉ ለመክሰስ የሚያስችል ማስረጃ ነበረን›› ሲሉ ይናገራሉ። ‹‹ሪፎርም ላይ በመሆናችን እንጂ በተለይ በየክልሉ በብሄረሰቦች መካከል እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎች ይህንን አዋጅ ለመጠቀም የሚያስችሉን ቢሆንም ይህንን ላለማድረግ እየሞከርን ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ደንበኞቻቸው በሽብር ሕጉ ቀጠሮ ሲጠየቅባቸው እንደነበሩ የሚናገሩት ሔኖክ በመርህ ደረጃ ሕጉ አፋኝ ነበር ከተባለ ከተጣለበት ማንሳቱ ተገቢ አልነበረም፤ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እና ከሕዝቡ ሲቀርብበት የነበረው ጫና አስጨንቆት እንጂ ሕጉን ከተጠቀመው በላይ የመጠቀም ፍላጎትም ነበረው፣ አሁንም አለው ብለው እንደሚምኑ ይናገራሉ።

‹‹አንድ ሕግ አፋኝ ነበር ከተባለ ይህን በመርህ ደረጃ ተግባባንበት ማለት ነው፣ አንድም ሰው ቢሆን በዚህ ስንቶች ሊቀይሩት ዋጋ በከፈሉበት እና በታገሉት አዋጅ መሰረት በድጋሚ መከሰስ አልነበረባቸውም፣ መንግሥትም ቢሆን የጠየቀው ይቅርታ ከልብ ሳይሆን ሕዝቡን በጊዜአዊነት ለማስደሰት ብሎ ያደረገው እንደሆነ ያሳያል›› ይላሉ። ‹‹እኔ እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ይህ ሕግ ተመልሶ ሥራ ላይ ሲውል መመልከቴ፣ ከዛም ዓቃቤ ሕግ የሰጠው ምክንያት አግባብ ነው ብዬ እንዳምን በፍፁም አያደርገኝም።››

የአዋጁ በጊዜው ያለመፅደቅ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ለመጠቀም አላስገደደንም ክፍተትም አልፈጠረም የሚሉት ፈቃዱ በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር አዋጅ በሕዝብ ላይ የፈጠረው አእምሯዊ ጫና ስላለ እና ሁሉንም ሰው ሊያስማማ የሚያስችል አዋጅ ቢፀድቅ የራሱ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ፍትሓ ብሄር
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲቋቋም ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል በፍትሓ ብሔር ጉዳዮች መንግሥትን የመወከል እንዲሁም አገርን በሕግ ጉዳዮች ወክሎ ግንኙነት የማድረግ ሥልጣን ቢካተትም ይህንን ሥራ የወንጀል ሥራዎች ሸፍነውታል ሲሉ አንድ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዓቃቤ ሕግ ይናገራሉ።

‹‹ለአንድ ዓለም አቀፍ ክርክር ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ ከሚደረግ በዳይሬክቶሬታችን ውስጥ ያሉ ዓቃቤያን ሕግ ብቃት እንዲኖቸው ቢደረግ አግባብ ነበር›› ሲሉ ይናገራሉ።

ለምሳሌነት የተነሳው የጤፍ ጉዳይ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኃላፊነቱ ከተሰጠ ሁለት አመት ሊሞላ ቢሆንም እስከ አሁን የሄደበት ሁኔታ ያን ያህል አመርቂ አለመሆኑን ያነሳሉ። የውጪ ተከራካሪ ሚሊዮኖችን ወጪ በማድረግ ከመቅጠር የራሱን ዓቃቤያን ሕግ ማብቃት ያስፈልጋል ብለዋል። በተጨማሪም የአሳልፎ መስጠት ስምምነቶች ዝቅተኛ በመሆናቸው ከአገር የሸሹ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ማምጣት ከባድ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል። በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው አሳልፎ የመስጠት ሰምምነት ዝቅተኛ ነው ይላሉ።

የሸሸ ሃብት ለማስመለስ የተሄደው ርቀት በጣም ትንሽ ነው የሚሉት ዓቃቤ ሕጉ የሕዝብ ሃብት በውጪ አገራት ያስቀመጡ ሰዎችን ማስመለስ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት አለበት ይላሉ። ምንም እንኳን ይህ እስከአሁን ያልዳበረ ሥራ ቢሆንም አጠንከሮ ካልተሠራ በፍትህ ዘርፍ ለሚታሰበው ለውጥ ውጤት የራሱ ጉዳት አለው ይላሉ።

ዓቃቤያን ሕጉ ምን ይላሉ?
በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሰራው እና አዲስ ማለዳ እጅ የገባው ጥናት እንደሚያሳየው በተለይ በምድብ ጽህፈት ቤቶች ያሉ ዓቃቤያን ሕግ ላይ ከፍተኛ መሰላቸት ይታያል። የማስረጃ ምዘና፣ የችሎት ክርክር ክህሎት፣ በማህደር አያያዝና ሌሎች መሰረታዊ ሂደቶች ላይ ዓቃቤያን ሕግ ዝቅተኛ አቅም አላቸው ሲል ጥናቱ ያመላክታል።
ቢ ኤስ ኤስ ተብሎ የሚጠራው የምዘና ስርአት ላይ ዓቃቤያን ሕጉ እምነት የሌላቸው ሲሆን የመመዘኛ መንገዶቹም አድካሚ እንዲሁም የተሰለቹ ናቸው ሲል ይሄው ጥናት ያሳያል። ‹‹አንድ ለአምስት በሚል የሚደረገው ውይይትም ከሪፖርት የዘለለ ውጤት ያላመጣ እና ድግግሞሽ ነው›› ሲሉ ዓቃቤያን ሕጉ አስተያየታቸውን አንጸባርቀዋል።

‹‹ካሉብን ክፍተቶች መካከል የዓቃቤያን ሕጎቻችን የብቃት ጉዳይ በመሆኑ ለአንድ መቶ ዓቃቤ ህጎች ከውጪ ሃገር የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እድል አግኝተው እንዲማሩ አመቻችተናል›› የሚሉት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የለውጥ ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት በረከት ማሞ ናቸው። ‹‹በተጨማሪም የምርመራ ሥራ አጋዥ ተቋማትን በሚያግባባ እና በቴክኖሎጂ ላይ በተመሠረተ መልኩ እንዲከናውኑ የፎረንሲክ እና የመሳሰሉ ሥራዎችን የሚያከናወኑ ዘመናዊ መሳሪዎች እንዲሟሉላቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ እንደሰማቸውም 40 ሚሊዮን ብር የምርመራ ስራዎችን ለማዘመን ከለጋሽ አካላት ተገኝቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

አንድ መዝገብ ከፖሊስ ተልኮ ዓቃቤ ሕግ ክስ እስኪመሰርት በአማካኝ ሁለት ወር ይወስዳል ያሉት በረከት ይህንን ለማሻሻል አዲስ ጥናት እየተሰራ ነው ብለዋል። የሥራ ቦታዎችን ምቹ ለማድረግ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የስድስት ህንጻ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን ሶስቱ ወደ መገባደድ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።

አዳዲስ ሕጎች
የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከአንድ አመት ተኩል በፊት ያቋቋመው የአማካሪ ጉባኤ ለሶስት አመት ያክል የፍትህ ዘርፉ ላይ ያሉ ለውጦችን የማማከር ተግባር ያከናውናል። በተለይም አዳዲስ የሚወጡ ሕጎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኘው 13 አባላት ያሉት ጉባኤ በስሩ ባሉት የተለያዩ የሥራ ቡድኖች አማካኝነት የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ አንድ ሕግ መሻሻል፣ መለወጥ፣ መሻር ወይም አዲስ ሕግ መውጣት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ሲደረስ ወደ ተግባር ይገባል።
አማካሪ ጉባኤው ከተቋቋመ ወዲህ 12 ሕጎችን የማሻሻል ሥራዎችን ያካሄደ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም አንዱ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እጅ ላይ ሲሆን ሶስቱ በአማካሪ ጉባኤው እጅ ላይ የሚገኙ ሆነው ቀሪ ስምንት ሕጎች ግን የመረቀቅ ሂደቶችን አልፈው በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በተወካዮች ምክር ቤት እና ፀድቀው ወደ ሥራ የገቡ መሆናቸውን ከአማካሪ ጉባኤው ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የአማካሪ ጉባኤው ገለልተኛ እንዲሁም ሞያዊ ብቃት ያለው ጉባኤ ነው የሚሉት የአማካሪ ጽህፈት ቤቱ አላፊ አባድር ኢብራሂም (ዶ/ር) ጉባኤውን መንግሥት ቢያቋቁመውም አብዛኛውን ፋይናንስ ከመንግስት አለማግኘቱ መሰረታዊ የነጻነት ምንጩ ነው ይላሉ። ጉባኤው ሲዋቀር ጀምሮ የራሱን በጀት የማፈላለግ ሥልጣን ኖሮት እና ዋና ሃብቱም በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉት አባላቶቹ በመሆናቸው ምክንያት ለጫና የማይበገር መዋቅር አለው ብለው እንደሚያምኑም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ከ 20 በላይ የልማት አጋሮች በሕግ ማርቀቅ ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

በተለይም ለጋሽ ተቋማት በሕግ ማርቀቅ ሂደቶቹ ውስጥ የአጀንዳ ጫና የሚያደርጉበት እድል የለም የሚሉት አባድር አንድ ተቋም በፋናንስም ሆነ በቴክኒክ ድጋፍ ከማድረጉ ቀደም ብሎ ማንኛውም የድጋፍ ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠ ተቀባይነት እንደማይኖረው ይገልጻሉ። እስካሁን እያገዙን ያሉ ተቋማት በተለይም የሕጉ ይዘት ላይ የሚያስቀምጡትን ማንኛውም አይነት ቅድመ ሁኔታ ተቀብለን አናውቅም፣ በተጨማሪ በአጋጣሚ አንድ ለጋሽ ተቋም የሚቆምለት ጉዳይ እና የሚሻሻሉ ሕጎች ይዘት ቢገጣጠም ግን ለሚያደርጉት ድጋፎች ተቃውሞ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

አዋጆች ከአማካሪ ጉባኤው እጅ ከወጡ በኋላ እስኪጸድቁ ባለው ሂደት ውስጥ የተለያዩ ለውጦች መደረጋቸው የመንግሥት አካላት ጣልቃ ገብነትን ያሳያል በሚል የሚነሳው ሃሳብ ላይም አስተያየታቸውን የሰጡት አባድር የጉባኤው ሥልጣን ዓቃቤ ሕግን የማማከር በመሆኑ ምክሩን የመቀበል ወይም ያለመቀበል ጉዳይ ግን የመንግሥት ሥራ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

መፍትሄ
በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተቋቋመው የአማካሪ ጉባኤ በሁለተኛ አመት እቅድ እንደሚያሳየው ባለፈው አንድ አመት በፍትህ ዘርፉ ላይ በተለይም በሕግ ማርቀቅ ዙሪያ ለውጥ መደረጉን ይገልፃል። አማካሪ ጉባኤው እንደ መፍትሄ ያቀረባቸው የፍትህ ስርአት ማሻሻያ ጥቅሎች መሬት ላይ እንዲወርዱ ማስቻል ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠራ የሁለተኛ አመት የሥራ መግለጫው ያሳያል።

በተለይም በዴሞክራሲ፣ በሕግ የበላይነት እና በሰብአዊ መብቶች ላይ አተኩሮ መሰራት አለበት የሚል እምነት አማካሪ ጉባኤው በተያዘው አመት የተሸሻሉ ሕጎች እንዲተገበሩ የሚተገብሩ ተቋማትን ማጠናከር አማራጭ የለውም ሲል ይደመድማል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here