ጩኸት አልባ ድምጾች – ከሕጻናት መንደር

0
982

ዘንድሮ 12 ዓመቷን ትደፍናለች። የተወለደችው ከአዲስ አበባ ወጣ ባለች ገጠራማ አካባቢ ነው። የት ነው ብትባል እንኳ እዚህ ነው ብላ ለመናገር በማታስታውስብት ጨቅላ እድሜ ነው ከትውልድ ስፍራዋ ወጥታ አዲስ አበባ የመጣችው። ‹‹አክስት›› ናቸው የተባሉ ሴት ሊያስተምሯት ብለው እንዳመጧት በተለያየ አጋጣሚ ይናገራሉ። ‹‹ቤተሰቦቿን ላግዝ ከሰማይ ዋጋውና አገኛለሁ ብዬ እንጂ…›› በሚል ሐረግ የሚጀምሩት ጨዋታ ብዙ ነው። ታድያ ግን ትምህርቱን ለደንቡ ያህል እንድትማር ያድርጉ እንጂ በለጋ እድሜዋ የቤቱን ሥራ ሁሉ እንድትሠራ ያስገድዷታል፤ አብዝተውም ይመቷት ነበር።

በዚህ አላበቃም፤ ወደ ትምህርት ቤት አቋርጣ በምትሔደው መንገድ ላይ ከአንዴም ኹለት ጊዜ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባታል። ይህም አንድ ጊዜ በጓዳ በዝምታ የታለፈ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ጋንዲ ሆስፒታል የተመዘገበ ሲሆን፤ ጉዳዩን የተከታተለ ሰው አልነበረም። ነገሩ ሁሉ ግልጽ የወጣው ይህቺው ትንሽ ልጅ ከኹለት ዓመት በፊት በቤት ውስጥ ከተከራይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባት አምልጣ ጮኻ የሰፈሩን ሰው ድረሱልኝ ያለች ጊዜ ነው። በዚህ ቀን አሳዳሪዋ ለቅሶ በሚል ከከተማ ውጪ ስለነበሩ ታሪኩ ሁሉ ለአካባቢው ሰው ግልጽ ሆኖ ታየ። አሁንም ጉዳይዋ በፍርድ ቤት ሒደት ላይ ሲሆን ይህም ኹለት ዓመት የተጠጋው ጉዳይ ነው።
ይህ አዲስ ማለዳ በቅርበት ከአካባቢው ሰው የተረዳችውና የታዘበችው ታሪክ የብዙ ትንንሽ ልጆችና ሕጻናት ሕይወት ነው። ለእነዚህ ሕጻናት መማር አይደለም በደኅና የመኖር መብት እንዲከበርላቸው የሚያደርግ አዋቂ ጥቂት ነው። በየጎዳናውና መንገዱ የምናያቸው ልጆችም በተመሳሳይ የተዘነጉ፣ ‹የእኔ ናቸው› ባይ ያጡ ናቸው። የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ይሄ ነው ብሎ ባይገልጽም፤ በየቀኑ ቢያንስ ኹለት ቢበዛ ስድስት ሕጻናት ተጥለው ከጎዳና እንደሚገኙ ይነገራል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው አገር ተተኪ ትውልድ እየጠበቀች የምትገኘው።

ለመብታቸው ድምጽ አውጥተውና ጩኸት አሰምተው መከራከር የማይችሉ ሕጻናት በጉልህ በሚታይ መልኩ መብታቸውን እየተጣሰ፣ ለተለያየ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ይታያል። ይህም አካላዊ ብቻ ሳይሆን የማይሽር የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥርባቸዋል።

የሕጻናት ቀን
የሕጻናት ቀን መከበር የጀመረው የሕጻናት መብቶች ድንጋጌ መጽደቁን መነሻ አድርጎ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የሕጻናት መብቶች ድንጋጌን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1989 ያፀደቀ ሲሆን፣ የሕጻናት ቀንም ይህን ተከትሎ ከዛን ጊዜ ጀምሮ መከበር ቀጥሏል። ኢትዮጵያም ይህ ድንጋጌ በፀደቀ በኹለት ዓመቱ ተቀብላ ነገሩን ጉዳይዋ አድርጋዋለች። ይሁንና የሕጻናት ቀንን አስባ ማክበር የጀመረችው ከ14 ዓመት በፊት ነው።

ዘንድሮ ዓለም ዐቀፍ የሕጻናት ቀን በዓለም ደረጃ ለ30ኛ በአገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ ይከበራል ማለት ነው። ‹‹መጪዎቹን ዘመናት በዛሬዎቹ ሕጻናት እንመልከት!›› የሚል መሪ ሐሳብ የያዘው የዘንድዎ በዓል በዛሬው እለት (ቅዳሜ ኅዳር 13) በኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደር በተለያዩ ክዋኔዎች ተከብሯል/እየተከበረም ይገኛል። ይህንንም የሕጻናትን ጉዳይ በተጠሪነት የሚመለከተው የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፤ ዘንድሮ የወላጆችን ድጋፍ ያጡ ሕጻትን በዘላቂነት ለመደገፍ በሚያስችሉ ዝግጅቶች ላይ ትኩረት አድርጓል። በሰመሞኑም የተለያዩ የሕጻናት ማሳደጊያዎች ጉብኝት ሲደረግ ነበር።

የሕጻናት ድምጾች
በተለያየ ምክንያትና አጋጣሚ ለሕጻናት የተነፈጉ ብዙ መብቶችና ያልተሰጡ ቦታዎች አሉ። ለዚህ አንዱ ማሳያ በ2018 የወጣ ዘገባ ሲሆን በዚህ መሠረት አዲስ አበባ ላይ ብቻ 55 ሺሕ የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ ተብሏል። ከዛ ውስጥ አብዛኞቹ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችና ሕጻናት ናቸው።
ይህን ያነሱት በስለ እናት የበጎ አድራጎት ድርጅት የገቢ ማሰባሰብና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ልዑልሰናይ ደመና፤ ይህ ክስተት ሕጻናት ያሉበትን ሁኔታ በቀላል ያስረዳናል ይላሉ። ምንም እንኳን አሁን ላይ የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብር እውን ቢሆንም፤ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በምግብ አለማግኘት ምክንያት የሚወድቁ ልጆች መኖራቸውም የማይዘነጋ ሃቅ ነው።

ልዑልሰናይ እንደሚሉት፤ መገናኛ ብዙኀን እና መዝናኛው ዘርፍ ላይ የሕጻናት ነገር ተዘንግቷል። ለዚህም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሚታየው ‹‹የልጆች ጊዜ›› እና በኢትዮጵያ ራድዮን ከሚቀርቡ ሳምንታዊ ዝግጅቶች ውጪ ብዙ የሚጠቀሱ አልነበሩም። ስለ ባህል ወረራ፣ ልጆች ታሪካቸውን ስላለማወቃቸውና አካሔዳቸውም ወደዛው እንደሆነ ከመናገር ባሻገር፤ ስለ ባህልና ታሪካቸው መሠረት ይዘው እንዲያድጉ የሚያስችሉ ሥራዎች ጎድለዋል። ለዚህም ነው ልጆች በእንግሊዘኛና በባህር ማዶ ቋንቋ የተሠሩ የልጆች ፊልሞችንና ጨዋታዎችን እንዲያዩ የተገደዱት፤ አማራጭ ባለመኖሩ።

ይህ ነጥብ ትኩረት እንደሚያሻው የሚናገሩት ልዑልሰናይ፣ አሁን ላይ ያሉትን ለውጦች ያዘገሙ ቢሆኑና የጥበብ ባለሙያዎችን ማስወቀሳቸው ባይቀርም፣ እንዳልዘገዩና ለልጆች የሚሆኑ ጥበባዊ ሥራዎችን በትጋት እየሠሩ ያሉ ባለሞያዎች ስለመኖራቸውም ይጠቅሳሉ።

የሕጻናት ድሮና ዘንድሮ
ሰብለ አዳም (ስሟ የተቀየረ) ወላጆቿ ነፍስ ባላወቀችበት እድሜ ነው በሞት የተለይዋት። አሁን ላይ የ27 ዓመት ወጣት የሆነችው ሰብለ ታድያ፤ መለስ ብለው ታሪኩን እንዳጫወቷት ከሆነ በጉዲፈቻ ወደ ውጪ አገር ልትላክ እንደነበር ትገልጻለች። ነገር ግን በየመካከሉ በሚፈጠሩ ክፍተቶች ምክንያት የውጪ ጉዞው መጨረሻው ሳይታይ የወላጆቿ የቅርብ ዘመዶች ሊያሳድጉ ወስደዋታል፤ ምንም እንኳ የስጋ ሳይሆን የ‹መወለድ ቋንቋ ነው› ዝምድና ያስተዋወቃቸው ቢሆንም።
በአሳዳጊዎቿ ሳይሆን በወላጅ አባቷ ስም መጠራቷ እንጂ ያደገችበት ቤተሰብ በስጋ የማይዛመዳት እንደሆነ አስታውሳ እንደማታውቅ አንስታለች። በትውልድ አገሯ፣ በአካልም ሆነ በመንፈስ ምንም ሳይጎድልባት በማደጓም የሚሰማትን ደስታም ትገልጻለች። እንደ ሰብለ ያለ እድል የገጠማቸው ሰዎች ብዙ ናቸው ለማለት ግን አይደፈርም።

ስለእናት የበጎ አድራት ድርጅት ከልጆች ጋር በተያያዘ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ልጆችን ከአደራ ቤተሰብ እንዲሁም ከአሳዳጊ ጋር ማገናኘት አንዱ ነው። ‹‹የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ የተሻለ እንደሆነ ይታመናል።›› ያሉት ልዑልሰናይ፤ አሁን ላይ ልጆች በብዛት መንገድ ላይ እየተጣሉ የሚገኙበት ምክንያት የማህበራዊ ግንኙነትና ትስስሩ መላላት ነው ይላሉ።

በተለይ በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ከተሞች ያለው የኑሮ ሩጫ ማህበራዊ ትስስሩን ስለጋረደ፣ አንድ ቤት ውስጥ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች በሞት ሲሰናበቱ፣ ‹የቀሩት ልጆች እንዴት ይሆናሉ?› ብሎ መጠያየቅ በሚያስችል ደረጃ ትውውቅ የለም።

በልዑልሰናይ ገለጻ ይህ ብቻ ሳይሆን የኑሮ ውድነትም ተዘዋዋሪ ጫና አሳድሯል። ልጅ ለማሳደግ ወጪው ከፍተኛ መሆኑና ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ጨምረው ለማሳደግ ቢፈልጉ እንኳ አስፈላጊውን መሠረታዊ ነገር ለማሟላት የገንዘብ አቅም ሊያጥራቸው እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

ሕጻናት በክትትልና በጥበቃ ባለማደጋቸው ምክንያት ታድያ የተለያዩ ቀውሶች ደርሰዋል። ልዑልሰናይ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ አሁን የሚታዩ ግጭቶችና በጠቅላላው የሚስተዋሉ ችግሮች አመጣጥ አስቀድሞ የሰዎች የልጅነት ጊዜ ላይ አለመሥራት ነው። ‹‹አሁን ላይ ችግር ፈጣሪ የሚባሉ የህብረተሰብ አካላት በልጅነት ምን ዓይነት ኑሮ ይኖሩ ነበር? ቤተሰብስ አይቷቸዋል ወይ?›› ሲሉ ይጠይቃሉ።

በሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከሕጻናት የድጋፍ አገልግሎትና ኢንስፔክሽን ክፍል በለጠ ዳኜ፤ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ መንግሥት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ለሕጻናት ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ሠርቷል። ይሁንና የሕጻናት ስብእና ቀረጻ ላይ የነበረው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። እርሳቸውም በበኩላቸው አሁን በአገራችን የሚታየው ችግር ሕጻናት ላይ የቤት ሥራው በሚገባ ስላልተሠራ ነው ባይ ናቸው።

መሠረታዊ ፍላጎትን በማሟላት በኩል ግን መንግሥት የአቅሙን እያደረገ ስለመሆኑ ነው በለጠ የገለጹት። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በተለያየ አጋጣሚ፣ ሕጻናት ያሏቸውን ሰብአዊ መብቶች ከሚጥሱ፤ በጤና፣ በሥነ ልቦና እና በማህበራዊ ኑሮ ረገድም ተጽእኖ ከሚያደርሱ፤ ደኅንነታቸውን ስጋት ላይ ከሚጥሉ ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ ችግሮች እንዲጠበቁ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ይገልጻል።

በለጠ እንደሚሉት የተለያዩ አማራጭ የድጋፍ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፤ በመንግሥት እንዲሁም በግል ድርጅቶች። ከእነዚህም መካከል የልጆች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ረገድ፣ ወላጅ ያጡ ሕጻናትን ለመደገፍ እንዲያስችል ከ2010 ጀምሮ ከሠራተኛው ደሞዝ አንድ በመቶ በመሰብሰብ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። ከዛም ውጪ በተቋማት የልጆች መዋያ ማዘጋጀት፣ ማሳደጊያዎችን መጠበቅና መከታተል እንዲሁም ልጆችን ከጎዳና ማንሳትና ወደ ቤተሰብ የመመለስ ሥራም እንዳሉ ይጠቅሳሉ። በዚህም በድምሩ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው አያይዘው የጠቆሙት።

‹‹ማሳደጊያ የመጨረሻው አማራጭ ነው፤ በቤተሰብ ፍቅር ማደግ አለባቸው።›› የሚሉት በለጠ፤ እነዚህን ማሳደጊያዎች መተላለፊያ በማድረግ ልጆች ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉ ጊዜ በሥነ ልቦና የተዘጋጁ እንዲሆኑም በየማሳደጊያ ተቋማቱ ባለሙያዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ‹‹በሚገባ እየሠሩ ስለመሆኑ ጥያቄ ይኖራል፤ የሚታዩ ክፍተቶች በመኖራቸው።›› ሲሉ የገለጹት በለጠ፤ እንደ ፕሮግራም ምን መሟላት አለበት የሚለውን በአግባቡ መተግበር ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የስለ እናት በጎ አድራት ድርጅት ሕዝብ ግንኙነት ልዑልሰናይ፣ በአንጻሩ ከ2010 ወዲህ በመጣው ለውጥ የሕጻናት ነገር እምብዛም ሲነሳ የሚሰማ ጉዳይ እንዳልሆነ ግን አንስተዋል። ፖሊሲ ተኮር የሆኑ ሥራዎችም መሠራት እንደሚገባቸውና ለሕጻናት ሥነ ልቦናም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።

የተሻለ የልጅነት ጊዜ እንዴት?
ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ኅዳር 7/2012፣ በስለ እናት የበጎ አድርጎት ድርጅት ጊቢ የሕጻናት ቀን ተከብሮ ውሏል። በዚህም ለሕጻናት የተሻለ የልጅነት ጊዜ መስጠትን በሚመለከት ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ ነበር። ልዑልሰናይ እንደሚሉት፤ ‹የተሻለ› የሚለው አንጻራዊ ገለጻ ነው። እንደ ድርጅቱ ይህን የተሻለ የልጅነት ጊዜ ለልጆች ለመስጠት መሟላት አለባቸው ተብሎ የታሰቡ መሠረታዊ ነገሮች አሉ። ሕጻናት ካሉበት ችግር ወጥተው በተሻለ አካባቢ ውስጥ፣ ከጎዳና ውጪ፣ የእናት ፍቅር አግኝቶ መኖር ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።

ልጆችና ሕጻናት ለማህበረሰቡና ለአገራቸው ፍቅር እንዲኖራቸው አስቀድሞ ለእነርሱ ፍቅር መስጠትና ማሳየት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ለዚህም ሁሉም ተቋም ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here