ትንንሽ ድሎችን ለማስቀጠል

0
681

ባለፈው ሳምንት በመገናኛ ብዙኀንና ማኅበራዊ ገጾ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የተሰማውን ዜና መዝዘው ያወጡት ቤተልሔም ነጋሽ፤ የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህከምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ የመካተቱን ነገር አውስተዋል። እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስም የብዙዎች ድምጽና ቅስቀሳ እንደነበር በማንሳት ማኅበራዊ ገጾችን ለለውጥና ለበጎ ነገር መጠቀም እንደሚቻል ማሳያ ነው ይላሉ። እነዚህ ትናንሽ የሚመስሉ ድሎችም በሴቶች ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያመጣ ውጤት እንዳላቸው በጽሑፋቸው ይጠቅሳሉ።

 

ያሳለፍነው ሳምንት መደበኛ የመገናኛ ብዙኀንን የአየር ሰዓት፣ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችንም ትኩረት የሳቡ ዋና ዋና ክስተቶችን ያስተናገደ ሆኖ አልፏል። ከእነኚህ ክስተቶች መካከል የአገራችንን ዕጣ ፈንታ በቀጥታ የሚመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዮች አሉበት። የመጀመሪያው ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቱን በገዢ ፓርቲነት የመራው ኢሕአዴግ፣ አራት ራሳቸውን የቻሉ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ግንባር መሆኑ ቀርቶ አንድ ውሁድ ፓርቲ የመሆኑን ሐሳብ እውን ወደ ማድረግ የተቃረበበት ውሳኔ ነው።

ኹለተኛው ኅዳር 10 ቀን የተካኅየደው የሲዳማ ዞንን በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል ውስጥ እንዳለ መቀጠል ወይም ራሱን ችሎ አስረኛ ክልል ሆኖ መመሥረቱን የሚወስነው ሕዝበ ውሳኔ ወይንም ሪፈረንደም ነው። ቀጣዩ ደግሞ አሁንም አላልፍ ያለ ዩኒቨርሲቲዎችን የጥቃትና የሰላም እጦት ማዕከል ያደረገ ብሔርን መሠረት አድርጓል የሚባል ጠብ ወይንም ተማሪዎች አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት ነው።

ሁሉም ሁነቶች በየፊናቸው የተለያየ የሕዝብ አስተያየት፣ የፓርቲ አባላት አቋም (በተለይ ውህደቱን አልቀበልም ወይም ውህደቱን ለመወሰን ሥልጣን የለንም ባሉት የሕወሃት ተወካዮች መግለጫ) ያስተናገዱ ነበሩ። መደበኛውም ሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ እነኚህን ዜናዎች እያስተጋባ ባለበት ግን፣ አንድ ዜና ጣልቃ እንደመግባት ብሏል። ይኸውም በዋነኛነት ኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን በቴሌቪዥን አስተላልፎት በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራው የጤና ሚኒስቴር የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫን ተመርኩዞ የወጣው ዜና ነው። የዜናው ሙሉ ቃል እነሆ፡-

“የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህከምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ መካተቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህክምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የክትትል ዝርዝር ውስጥ መካተቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቀደም ሲል የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ የሚመረተዉም ሆነ ወደ አገር ዉስጥ የሚገባዉ በብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ መስፈርት ብቻ እንደነበር ሚኒስቴሩ አስታውሷል።

አሁን ላይ ግን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሱ ወደ ምዝገባ ስርአት ዉስጥ ገብቶ ምርቱ ላይ በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል የደኅንነትና የጥራት ቁጥጥር ይካሔድበታል ተብሏል።

በትምህርት ቤት፣ ክሊኒኮችና በጤና ተቋማት የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሱን በማቅረብም የአፍላ ልጃገረዶችን የጤና ተደራሽነት ለማሰደግ አዲስ መርሃ ግብር እየተተገበረ መሆኑን በሚኒስቴሩ የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተሯ ዶክተር መሰረት ዘላለም ተናገረዋል።

በገጠር ከሚኖሩ አፍላ ወጣቶች መካካል የሚገኙ ልጃገረዶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ መረጃና እዉቀት እንዲሁም የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ባለማግኘታቸዉ፣ ከትምህርት ገበታቸዉ መቅረትና እንዲሁም ለሥነ ልቦና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸዉ ከፍተኛ ነዉ።

ይህንን ችግር ከግምት ዉስጥ በማስገባት የጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸዉ ሴክተር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እነዚህን ተጋላጭ ልጃገረዶች በትምህርት ቤት መቆየት እንዲችሉ ለማድረግ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶች አዉጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።”

ይህንን ዜና በርካቶች በበጎ ሲቀበሉት በተለይ ይህንን በሚመለከት የቅስቀሳ ሥራ ሲያከናውኑ በነበሩት የፆታ እኩልነት ንቅናቄ አራማጆች ዘንድ ‹ልፋታችን ፍሬ አፈራ› የሚያሰኝ የምስራች ነበር። እንደዚህ ዓይነት ትናንሽ ድሎች በተለይ በሴቶች መብቶች ዙሪያና ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል፣ እኩል ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ለማስቻል ዘመቻ ለሚያደርጉ “ለካስ የሚሰማን አለ” የሚያሰኙ ተስፋ ሰጪ ክስተቶች ናቸው።

ከዚህም ሌላ እነኝህን መሰል ጥያቄዎች ሲቀርቡ ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸው አካላት “ይሄ የቅንጦት ጉዳይ ነው፤ ያኛውን ጠይቁ” በሚልም ይሆን በአጠቃላይ ሴቶች ድምፃቸውን ማሰማታቸውን በመቃወም ዕለት ዕለት የሚያደርጉትን ተቃውሞና አላስፈላጊ ትችት አልፎ ከሔዱ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ትናንሽ የሚመስሉ ነገር ግን በሴቶች ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያመጡ ውጤቶችንና እርምጃዎችን ማየት ይቻላል የሚል እምነት የሚሳድር ነው።

በዚህ በኩል የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቢያንስ ታክሱ ቢነሳለት፣ እንደ ቅንጦት ዕቃ መታየቱ ቢቆም፣ ለአገር ውስጥ አምራቾች ማበረታቻ ቢደረግ ቢቻል እንደ ኬንያ ጉዳዩ የፖሊሲ ትኩረት የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ ትኩረት ቢሰጠው በሚል የሚደረገውን ዘመቻ ያዩት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን፣ በትዊተር ገጻቸው ጉዳዩን እንደሚከታተሉት ቃል ከገቡ ወዲህ የመጣ ነው፤ ከላይ ያያችሁት ዜናና ውጤት።

በዚህ ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ እና ባልደረቦቻቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ቀጥሎ ውጤት እንደሚያመጣ ተስፋ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የምንከታተለውና የት ደረሰ ብለን የምንጠይቀውም ይሆናል።

በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ መምጣትና ይህንንም በመጠቀም ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት፣ የተበላሹና አቅጣጫቸውን የሳቱ ክስተቶችን ለይቶ በመናገር ፈጣን ማስተካከያ እንዲደረግ በማድረግ በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴና ውጤት ታይቷል። በቅርቡ እንኳን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሴት ተማሪዎችን መብት የሚጥስ “የእርግዝና ምርመራ ውጤት ካላመጣችሁ ትምህርት ምዝገባ ማድረግ አትችሉም” የሚል ማስታውቂያ አውጥቶ በዚሁ በማኅበራዊ ሚዲያ በተደረገበት ዘመቻ ይህንን ማስታወቂያ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ይቅርታ መጠየቁ የማኅበራዊ ሚዲያ ውጤት ምን ያህል ለበጎ መዋል እንደሚችል አመላካች ነው።

ይህን ካልን በኋላ፣ በተለይ በአገራችን ባለፉት ሳምንታት በተከሰተው አለመረጋጋት ለተፈጠረ ሞትና ስደት ሴቶች ሰለባ እንደነበሩ የሚታወስ ነው። አሁንም በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ባለው መፈናቀል ሴቶች ከወንድ ተማሪዎች በተለየ የመደፈር አደጋና ስጋት ውስጥ ናቸው። ማኅበረሰቡ በጠቅላላው ባንልም፣ ሴቶች የተለየ ድጋፍና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ የተለየ ተጋላጭነት ያለባቸው እንደሆኑ አይረዳም።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለምሳሌ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሰለባ ስለመሆናቸው ሲወራ “ሰው እየሞተ ስለ መደፈር ታወራላችሁ” የሚል አለ። ከዚህም በላይ በተለይ በሴቶች ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ድርጅቶች ለእነኚሁ በየእምነት ተቋማት ለተጠለሉት ሴት ተማሪዎች እንደ ንጽህና መጠበቂያና አልባሳት ያሉ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ “ለምን ሴቶች ላይ ብቻ አተኮራችሁ፤ ከረዳችሁ ሁሉንም እርዱ” የሚሉ አሉ።

አስተያየት ለምን ተሰጠ ወይም ትችት ለምን ተሰነዘረ ለማለት ሳይሆን፣ ሴቶች በማይመች ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርገውና ለሚደርሱባቸው ጥቃቶችና እኩል ዕድል ተጠቃሚ ያለመሆን እውነታዎች ምክንያት ማኅበረሰቡ ለሴቶች የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት ለመለወጥ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ለማመላከት ነው።
ከላይ እንደተቀመጠው ያሉ ትናንሽ ድሎች በሁሉም የሴቶችን ሕይወት በሚመለከቱ ዘርፎችና አካባቢዎች ተደግመው በድምሩ በሴቶች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ፣ ድሎቹን ለማስቀጠል የሚያስችል የተቀናጀ ተከታታይነት ያለው ዘመቻ ቅስቀሳና የማሳወቅ ሥራ ሊሠራ ይገባል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here