የኦሮሚያ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች ስለኢህአዴግ ውህደት ለመወያያት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ እና ነገ ሊያደርጉ ነው

0
715

የኦሮሚያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በቅርቡ ተግባራዊ ሊደረግ ጫፍ ስለደረሰው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ጥምር እና አጋር ፓርቲዎች ውህደት በተመለከተ ለመወያየት አስቸኳይ ጉባኤ መጥራታቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።

ኦዴፓ ዛሬ ኅዳር 16/2012 አስቸኳይ ጉባዔ የጠራ ሲሆን ኦዴፓ ወህደቱን በተመለከተ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ አዴፓ በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ጉባዔ የጠራ ሲሆን በተመሳሳይ ርዕስ ላይ ለኹለት ቀናት እንደሚወያይ ምንጮች ገልፀዋል።

ባለፉት ሳምንት የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋ.ህ.አ.ዴ.ን) እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባኤ ኢህአዴግ ወደ ብልፅግና ፓርቲ የሚያደረገውን ውህደት በመደገፍ በሙሉ ድምፅ አፅድቀው ነበረ።

ባለፈው ሳምንት የኢህአዴግ ምክር ቤት የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የመራለትን የፖርቲውን ውህደት ማፅደቁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያልተገኘው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕውሓት) ውህደቱን ሙሉ ለሙሉ መቃወሙ ይታወሳል።

በተጨማሪ የህውሓት ስራ አስፈፃሚ የትግራይ ምክትል ርእሰ መስተዳድር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ትናንት ኅዳር 15/2012 በሰጡት መግለጫ በቅርቡ ውህደቱን በተመለከተ ለመወያየት ፓርቲያቸው ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራል ብለዋል። ይሁን እንጂ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ሆነ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ውህደቱን መቃወማቸውን ከወዲሁ ይፋ አድርገዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here