አብነት ገብረመስቀል የያዟቸውን ኹለት ይዞታዎች ለቦሌ ታወርስ እንዲመልሱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላለፈ

አብነት ከባንክ ከተበደሩት 425 ሚሊየን ብር ውስጥ፤ 304 ሚሊየን ብር ለማህበሩ እንዲመለስ ታዟል

0
179

ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ባለኃብቱ አብነት ገብረመስቀል በሕገወጥመንገድ ካርታ ያወጡባቸው ኹለት ይዞታዎች ለቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ እንዲመለሱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ስፋታቸው 3 ሺሕ 383 እና 1 ሺሕ 971 ካሬ ሜትር የሆኑ እና ስያሜያቸው C እና D የተባሉ የካርታ ይዞታዎች ለቦሌ ታወርስ ማስፋፊያነት የተሰጡ ሆነው ሳለ፤ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አብነት ገ/መስቀል የቦሌ ታወርስ ኃ.የተ.የግ.ማ. ሥምን ከካርታዎቹ ላይ እንዲወጣ በማስደረግና “የግል ንብረቴ ነው” በማለታቸው፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሃ ብሔር ችሎት ክስ ተመስርቶ ክርክር ላይ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በዚሁ መሰረት የማህበሩ የቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ 60 በመቶ ባለድርሻ የሆኑት ሼይኽ መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በአብነት ገብረመስቀል ላይ ያቀረቡትን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤት፤ ትናንት ጥቅምት 5/2016 ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በዚሁ ፍርድ መሰረት ፍ/ቤቱ ሼይኽ መሀመድ ያቀረቡትን ክስ ሙሉ በሙሉ በመቀበል ተከሳሽ አብነት ገ/መስቀል ከሕግ ውጪ “የግሌ ነው” በማለት በሕገወጥ መንገድ ካርታ ያወጡባቸውን የኩባንያውን ከላይ የተጠቀሱ 2 ይዞታዎች ለማህበሩ ተመላሽ እንዲያደርጉ ውሳኔ አሳላፏል፡፡

እንዲሁም የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አብነት ገ/መስቀል የኩባንያውን ሕንጻ ግንባታ ለማሰራት በሚል በማህበሩ ሥም ከባንክ የተበደሩትን 425 ሚሊየን ብር ለኩባንያው ሕንጻ ግንባታ ማዋል ሲገባቸው፤ ብድሩ ከተፈቀደለት ዓላማ ውጪ ለተለያዩ ግለሰቦች እንዲተላለፉ በማድረግ በማህበሩ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውም በችሎቱ ተነግሯል፡፡

በዚህም አብነት ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ የኩባንያው 60 በመቶ ባለድርሻ የሆኑት ሼይኽ መሀመድ ክስ አቅርበዋል፡፡

ክሱን ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤቱ የብድሩ ገንዘብ ለኩባንያው ሕንጻ ግንባታ መዋል አለመዋሉን የሚያጣሩ ኦዲተሮች ሾሞ ኦዲተሮቹ ያጣሩት ሪፖርት ለፍ/ቤት ቀርቦለታል፡፡

ፍ/ቤቱም ኦዲተሮቹ ያቀረቡለትን ሪፖርት ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ፤ አብነት ገ/መስቀል 304 ሚሊየን ብር ከባንክ ወለድ ጋር ለኩባንያው እንዲከፍሉ በማለት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም አብነት ገ/መስቀል “ከቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ ሥራ አስኪያጅነት እንድነሳ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የተወሰነብኝ ውሳኔ ተገቢ አይደለም፡፤” በማለት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም ዛሬ ጥቅምት 6/2016 በዋለው የሰበር ሰሚ ችሎት “አብነት ገ/መስቀል ከሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ የተወሰነው በበቂ ምክንያት ነው፡፡” በማለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ ማጥናቱን የፍርድ ሂደቱን አስመልክቶ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አብነት ገ/መስቀል ከሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ ከተፈረደባቸው በኋላ፤ በምትካቸው አምባሳደር አሊ ሱለይማን የቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ ሥራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here