ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኀዳር 15/2012

0
630

1-በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ኅዳር 14/2012 ከለሊቱ 7 ሰዓት በተማሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት ምክንያት አምስት ተማሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር አስታወቀ።በግጭቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን የግጭቱን መነሻ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።(አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………….
2-የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን)ኅዳር 14/2012 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ወደ ብልፅግና ፓርቲ የሚደረገውን ውህደት በመደገፍ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።ውህደቱ የሞግዚት አስተዳደርን በማስቀረት ክልሎች ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ስርዓትን እንዲተገብሩ የሚያስችል መሆኑን የጋህአዴን ሊቀመንበር ኡሞድ ኡጁሉ ገልፀዋል።(ዋልታ)
…………………………………………………….
3-በኦማን እስር ቤት የሚገኙ 3 ኢትዮጵያውያን ታራሚዎች 49ኛውን የኦማን ብሔራዊ ቀን ምክንያት በማድረግ ይቅርታ ተደረገላቸው።የኦማን መንግስት በየዓመቱ ህዳር 8 የሚከበረዉን የኦማን ብሔራዊ ቀን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች ይቅርታ ያደርጋል። 49ኛው የኦማን ብሔራዊ ቀን ሲከበር በተለያየ ወንጀል ተፈረዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሶስት ኢትዮጵያውያን ይቅርታ መደረጉን በኦማን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።(ኤዜአ)
…………………………………………………….
4-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ ምሁራን ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።የግድቡ ግንባታ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ምሁራን ባላቸው ሙያ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በአዲስ መልክ ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን የጽሕፈት ቤት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ኃይሉ አብርሃም ገልፀዋል።በዘርፉ ብቁ የሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙያቸው አስተዋፅኦ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቀሴ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።በእንግሊዝ አገር የሚገኙ ምሁራን በመሰባሰብ ‹‹ኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ሳይንስ›› (ኢፕሳ) በሚል ስያሜ ድርጅት በማቋቋም ወደ ስራ መግባታቸው ተገልጿል።(ኢቢሲ)
…………………………………………………….
5-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አየር መንገዶች የበረራ አገልግሎት ድርሻቸውን ከፍ ለማድረግ ደቡብ አፍሪካ አየር መንገድን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም “የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ እኛንም እንዲደግፈን እንፈልጋለን፤ይህም የአፍሪካ አየር መንገዶችን በአፍሪካውያን ለአፍሪካውያን ለማድረግ እንዲቻል ነው። ነገር ግን ዘርፉን ለሌሎች አየር መንገዶች ዝግ እናደርጋለን ማለት አይደለም፤ ዓላማው በዘርፉ ያለንን የገበያ ድርሻ ይዘን ለማስጠበቅ ነው። በዘርፉ ውስጥ 50-50 መልካም የገበያ ድርሻ ቢሆንም፣ አሁን ያለን 20 በመቶ ድርሻ ብቻ ነው። በዚህም የተነሣ ሌሎች እህት አፍሪካውያን አገራት አየር መንገዶቻቸውን እንዲያሳድጉ ለመርዳት ዝግጁ ነን። አቅማችንን አንድ ላይ በማስተባበር ከተቀረው ዓለም ጋር መወዳደር እንችላለን” ብለዋል።
…………………………………………………….
6-በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ 189 ሽጉጦችን ሲያጓጉዝ የነበረ ግለሰብ መያዙን የወረዳ አስተዳደር ጸጥታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንተነህ ታደሰ ተናግረዋል። ግለሰቡ በሕገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውር በሳንጃ ከተማ በሚገኘው የፍተሻ ኬላ ላይ መያዙን አስታውቀዋል።(ኤዜአ)
…………………………………………………….
7-በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣውን የጥጥ ልማት ለማሻሻል እና የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን በተገቢው መንገድ እንዲያግዝ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።ስትራቴጂው ምርታማነትን በመጨመር፣ ጥራትን በማሻሻል፣ በአቅም ግንባታ እና ተቋማትን በማጠናከር የኢንዱስትሪውን አፈፃፀም፣ ተወዳዳሪነት እና ዘላቂነት ማሳደግ ላይ እየተሰራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ ገልጸዋል።(ኢቢሲ)
…………………………………………………….
8- በነገው ዕለት ማለትም ኅዳር 16/2021 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጥላቻ ንግግርና አነስተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል።(አዲስ ማለዳ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here