“ኢትዮጵያ ጦር የምታዘጋጀው በዋናነት ሕዝቦቿን ለመጠበቅ ነው፡፡” ጀኔራል አበባው ታደሰ

116ኛው የሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ የሚጸና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሐሙስ ይከበራል

0
205

ማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ጦር የምታዘጋጀው በዋናነት ሕዝቦቿን ለመጠበቅ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፤ 116ኛ የሠራዊት ቀን አከባበርን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ከዚህ ቀደም በነበረው ስርዓት ሠራዊት እንደ አዲስ የተደራጀበት በሚል ምክንያት የሠራዊት ቀን ይከበር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በተደረገው ሪፎርም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ሚኒስትር በሠየመችበት ቀን ላይ ቀኑን ለማክበር መቻሉን አስረድተዋል።

በዚህ መሠረትም ሰራዊቱ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ኹኔታ ኹሉ በፈተና እየተሻገረ የመጣ ሀይል ስለሆነ፤ የሠራዊቱ ቀን በዛ ቀን ሊከበር እንደቻለም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሰራዊት የነበራት ጠላቶቿ በተነሱባት ጊዜ ኹሉ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ተልዕኮውን፣ አገሩን እና ህዝቡን እየጠበቀ የመጣና ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ሰራዊት ያላት ሀገር መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ገልጸዋል።

ጄኔራል አበባው የበዓሉ ዋና አላማ ለዘመናት አገራቸውን ከጠላት ለመፋለም መስዋዕት የሆኑ ጀግኖችን የምናከብርበትና ቃላቸውን በመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ቃለ መሀላ የምንፈፅምበት፣ ባሳለፍነው ዓመት የነበሩ ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን በማየት ለቀጣይ ግዳጆቻችን ዝግጁ የምንሆንበት፣ እንደ ተቋም የተሠጠንን አገርን እና ሕዝብ የመጠበቅ ሀላፊነት አጠናክረን የምንቀጥልበት እንዲሁም በአገራችን በምንም አይነት መልኩ ትንኮሳ ሊቃጡ የሚችሉ ሀይሎች ካሉ አይቻልም የምንልበት በዓል ነው” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ጦር የምታዘጋጀው በዋናነት ሕዝቦቿን ለመጠበቅ ነው፡፡” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ “በዓሉ ሕዝባችን አገራችንን በመጠበቁ በኩል ከጎናችን በመሆን ሚናውን እንዲጫወት መልዕክት የምናስተላልፍበት ዕለትም ነው፡፡” ሲሉ አክለዋል።

116ኛው የሠራዊት ቀን “በተፈተነ ጊዜ የሚጸና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በተቋም ደረጃ እየተከበረ እንደሚገኝ የገለጹት ጄኔራል አበባው፤ የፊታችን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ከህዝቡ ጋር በጋራ በማክበር የበዓሉ ፍፃሜ እንደሚሆን ማስታወቃቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገነነው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘ ይህን የአገር መከላከያ ሰራዊት ቀንን ለመታደም የተለያዩ አገራት የጦር አዛዦች አዲስ አበባ በመግባት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የደቡብ አፍሪካ እና ታንዛኒያ የጦር መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

የጦር አዛዦቹ አዲስ አበባ ሲደርሱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here