ጎጎት ፓርቲ  የፓርቲው አመራር በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ገለጸ

0
175

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) የፓርቲው የጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ መላኩ ሳህሌ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን አስታውቋል።

ፓርቲው መላኩ “ትላንት ጥቅምት 14/2016 ከሥራ ወጥተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ላይ እያሉ፤ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ መታፈናቸውን ከቤተሰቦቻቸው ተረድቻለሁ” ሲል ገልጿል፡፡

አመራሩ በአሁን ሰዓት ሰሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኘው 3ተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የገለጸው ፓርቲው፤ ፖሊስ የፓርቲውን አመራር ለምን እንዳሰራቸው አለመግለጹንም አስታውቋል፡፡

ፓርቲው በ 2015 ምሥረታውን ለማካሄድ ፔቲሽን (ፊርማ) ከማሰባሰብ ጊዜ ጀምሮ መሥራች ጠቅላላ ጉባዔ ሲያካሂድ በመንግሥት አካላት መዋከብና እስራት እየገጠመው መሆኑን የተናገረ ሲሆን፤ መሥራች ጠቅላላ ጉባዔውን በስኬት ሲያካሂድም፣ ከ12 ያላነሱ አባላቱ ከእነ ጠቅላላ ጉባዔ ሰነዶቹ በፖሊስ መታሰራቸውን አስታውቆ ነበር።

በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ፓርቲው፤ ይህ ደግሞ የጉራጌ ዞን ሕዝብን ድምፅ አልባ ለማድረግ የተወጠነ ነው ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

በወቅቱም የፓርቲው የጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ መላኩ ሳህሌ “ፓርቲያችን ፍፁም አንድነትና ፍፁም መለያየት ከሚያቀነቅኑ ሁለት አፍራሽ የፅንፈኝነት ኃይሎች ጋር አይተባበርም” ሲሉ ተናግረዋል።

ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ ሐምሌ 18/2015 ሕጋዊ አገር ዓቀፍ ፖለቲካ ፓርቲነት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማግኘት በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here