አርብ ጥቅምት 16 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ ፍትሕን የማግኘት ነፃነት፣ ሙስናን እና ጠቅላይ አምባገነንነት በዓለም ዙርያ ፈትሾ ዓመታዊ ልኬትን የያዘ ሪፖርት የሚያወጣው ዎርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት፤ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከዓለም 142 አገራት ውስጥ የ129ኛ ደረጃን መያዟን አስታውቋል።
ዎርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት ጥቅምት 14/2016 ባወጣው ሪፖርት፤ የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ምዘና ውጤት ከአምናው ዝቅ በማለት 129ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ያስታወቀ ሲሆን፤ ከሰሐራ በታች ካሉ 34 የአፍሪካ አገራት ደግሞ አራት አገራትን ብቻ በመቅደም 30ኛ ደረጃ ላይ መቀመዘጡን ገልጿል።
በሪፖርቱ ርዋንዳ በአፍሪካ ካሉ 42 አገራት የተሻለ አፈጻጸመ በማስመዝገብ 1ኛ መሆኗ የተገለጸ ሲሆን፤ ናሚቢያ እና ሞሪሺየስ 2ኛና 3ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በተጨማሪም ሪፖርቱ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው18 አገራት ውስጥ ኢትዮጵያን 15ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች በሪፖርቱ ከተካተቱ አገራት አንፃር ዝቅ ያለ ውጤት ካስመዘገበችባቸው መስፈርቶች መካከል፤ የመንግሥት ግልፅነት፣ የመሠረታዊ መብቶች መከበር፣ የህግ እና ስርዓት መኖር እንዲሁም የመንግስትን ስልጣን የሚቆጣጠር ልጓም መበጀት የሚሉት ይገኙባቸዋል።
በሪፖርቱ ዴንማርክ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፤ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድንና ጀርመን እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ቬንዘዌላ፣ ካምቦዲያ፣ አፍጋኒስታን፣ ሃይቲና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊከ ኮንጎ ዝቀተኛ ደረጃን መያዛቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ጥናቱ በተከናወነባቸው አገራት የሕግ የበላይነት በ59 በመቶ መቀነሱን ዎርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከአለማችን 140 አገራት 123ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም፤ ከሰሃራ በታች ካሉ 34 አገራት ደግሞ 27ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ይታወሳል፡፡



