ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ቀጣይነት ባለው ምርመራ ማረጋገጥ እና በግጭት ለተጎዱ ሰዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ አለበት ሲል አለም ዓቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ያለው ባለፈው ረቡዕ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የመጨረሻ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ሲሆን፤ በሪፖርቱም “በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ለኹለት ዓመታት በዘለቀው አሰቃቂ ጦርነት ተፈጽመዋል” ስላላቸው የመብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች ሰፊ ማብራሪያ አቅርቧል።
የኮሚሽኑ ባለሙያዎች “በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሕዳር ወር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም በተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ቀጥለዋል” ያሉ ሲሆን፤ በመንግሥት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሂደት ውስጥም ከባድ ጉድለቶች መኖራቸውን አመላክተዋል። ወደፊትም በአገሪቱ ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስጠንቀዋል።
“በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጣም ጨለማ የሆኑ ምዕራፎችን ተመልክተናል። በግጭቱ ውስጥ ያሉ ኹሉም አካላት የፈጸሙትን የጭካኔ መጠን እና ክብደት መግለጽ አንችልም” ሲሉ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር መሀመድ ቻንዴ ኦትማን በጉባዔው ተናግረዋል።
“በጦር ወንጀሎች እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰት ወንጀሎችን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አግኝተናል።” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በትግራይ ክልል በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማጣራት፤ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ እናምናለን።” ሲሉ ለጉባዔው አስረድተዋል፡፡
በያዝነው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት 54 ኛ ስብሰባ ላይ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመኑ እንዲራዘም የጠየቀ አገር ባለመኖሩ፤ የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ እንዲያበቃ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ የምርመራው ጊዜ በዚህ ወር ሲያልቅ እንደሚበተን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
በረቡዕ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ “የኮሚሽኑ ሥራ ማቋረጥ በአገሪቱ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ የመብት ጥሰቶችን ያባብሳል” ያሉት ኮሚሽነሮቹ፤ የኮሚሽኑ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎችን በዝርዝር ከማስቀመጥ ባለፈ፣ ቀጣይነት ያላቸው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ስጋቶችን አጉልቶ በማሳየት፣ ወደፊት ሊደርስ ስለሚችል አደጋ የሚያስጠነቅቁ በመሆናቸው ምርመራው ሊቀጥል ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽነሮቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ የአገር ውስጥ ስልቶችን እና አሰራሮችን በመዘርጋት የዓለም አቀፍ ትኩረትን ለማፈን እና አለም ዓቀፋዊ ምርመራዎችን ለማደናቀፍ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ተጠቅሟል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም የብዙ ተጎጂዎች እውነትን፣ ፍትህን እና ማካካሻን የማግኘት ዋስትና ላይ ኪሳራ ያስከትላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽኑን የምርመራ ሥራ እንዲቆም በመወሰኑ የተጎዱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ባለሙያዎቹ፤ “ብዙዎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደተተዉ ይሰማቸዋል።” ሲሉ ባለሙያዎቹ ለጉባዔው አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት እና አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በህይወት የተረፉት የአገሪቱ ዜጎች ፍትህን፣ እውነትን፣ እርቅን እና ዘላቂ መረጋጋትን እንዲያገኙ በሚደረገው ጥረት ላይ ቁርጠኛ አቋም እንዲያሳዩ አሳስበዋል፡፡
አክለውም አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት እና ግጭት መከላከልን የሚመለከቱ አካላት እንዲሁም አባል አገራት፤ በኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ ከአለም ዓቀፍ አጀንዳነት እንዳያነሱ ያሳሰቡ ሲሆን፤ ይልቁንም “በአገሪቱ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ክትትል፣ ሪፖርት፣ ግምገማ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋችነትን ሊረጋገጥ ያገባል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ታኅሳስ 8/2014 ባጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት የተቋቋመ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ መስከረም 27/2015 የኮሚሽኑን የሥራ ዘመን እስከ ጥቅምት 2016 አራዝሞ ነበር።
ኮሚሽኑ “በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያስችል ከፍተኛ ስጋት አለ።” በማለት በመስከረም ወር ማብቂያ ላይ ያወጣው ሪፖርት ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሪፖርቱ “ሃላፊነት የጎደለው እና በመረጃ ያልተደገፈ ግጭት ቀስቃሽ ውንጀላ ነው።” ሲል ውንጀላውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡



