መንግሥት የማያውቀው ስብሰባ በመቀሌ ከተማ መጠራቱን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ

0
151

ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) “መንግሥት በማያውቀው፣ የሕዝብ ሃብት በማባከን ከረቡዕ ጥቅምት 14/2016 እኩለ ሌሊት ጀምሮ፤ ከጣቢያ፣ ከወረዳ እና ከዞን የተሰባሰበ ኃይል ወደ መቀሌ ለስብሰባ የተጠራበት ምክንያት ግልጽ አይደለም” ሲል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት በፅህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ፤ “የተሰው ታጋዮች መርዶ በተነገረበት ማግስት ያሉ የመንግሥት ሥራዎችን ወደ ጎን በመተው፤ መንግሥት የማያውቀውን የሕዝብ ሃብት በማባከን ከጥቅምት 14/2016 ጀምሮ ከቀበሌ እስከ ዞን ስብሰባ መጥራት ምክንያቱ ግልፅ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ባለሥልጣናት መቀለ ውስጥ ስብሰባ ለማድረግ ከረቡዕ ሌሊት ጀምሮ እየተነቀሳሱ እንደሚገኙ ገልዋል።

በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የማያውቀው በህወሓት የተጠራ ስብሰባ እንዲካሄድ ጥሪ ሲያደርጉ በነበሩ የክልሉ መስተዳደር ባለሥልጣናት ላይ፤ “እርምጃ” መወሰዱንም ጌታቸው ጨምረው ተናግረዋል።

ክልሉ የገጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ለስብሰባ ወደ መቀለ በመምጣት የክልሉ መስተዳደር የማያውቀውን ስብሰባ ማካሄድ ዓላማው ግልፅ አይደለም ያሉት ጌታቸው፤ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በማለት የመንግሥትን አሰራር በጣሱት ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

አክለውም የሰብሰባው ዋና ተሳታፊዎች በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊዎች መሆናቸውን ያስረዱ ሲሆን፤ በሕዝብ እና በመንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያልተወጡት ላይ የተወሰደው እርምጃ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

በህወሓት ለተጠራው ስብሰባ ከአንዳንድ አካባቢዎች ለሚመጡት ሰዎች “ስንቃቸውን ጭምር ይዘው እንዲመጡ” እንደተነገራቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ኃላፊዎች “ሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት አለባቸው፤ ይህንን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ላይ ጠንካራ ሕግን የማስከበር እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።

ህወሓት በበኩሉ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በኩል ባሰራጨው መልዕክት፤ ቅዳሜ እና እሁድ በመቀለ ከተማ ስብሰባ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ህወሓት “የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈጻሚ እና የተለያዩ ኮሚቴዎች በወሰኑት መሠረት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ካድሬዎች ስብሰባ እንደሚያካሂዱ” በመግለጽ፤ ሕዝቡ ስብሰባውን በሚመለከት የሚነዙትን  አሉባልታዎች እንዳይሰማ አሳስቧል።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ስብሰባውን በማዘጋጀት ተሳትፈዋል የተባሉ 6 የዞን ከፍተኛ አመራሮችን ከስልጣናቸው ማንሳታቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

በዚህም ከስልጣን የተነሱት አመራሮች የምስራቅ፣ የደቡብ፣ የማእከላይ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ የሰሜናዊ ምእራብ እና የምእራብ ዞን የሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ኃላፊዎች ሲሆኑ፤ ኃላፊዎቹ ከፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ጥቅምት 14/2016 በተፃፈ ደብዳቤ በይፋ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተገልጿል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሥራቸው በለቀቁ ባለሥልጣናት ምትክ “በቅርቡ” ሌሎች ሃላፊዎችን እንደሚመድብ ጌታቸው አስታውቀዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here