በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ኹለት ባለስልጣናት ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

0
1271

በምዕራብ ሸዋ ዞን የጀልዱ ወረዳ ኹለት ባለስልጣናት ማክሰኞ ኅዳር 16/2012 ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። ከኹለቱ የወረዳ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ ፖሊስ የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ገላና ኑረሳ መናገራቸውን ዶይቸ ቬለ ዘግቧል። በግድያ ሕይወታቸውን ያጡት የጀልዱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት ረጋኔ ከበደ እና በወረዳው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የከተማ ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ የነበሩት ተስፋዬ ገረመው መሆናቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ባለሞያ ቢቂላ አበበ አስታውቀዋል። ከኹለቱ የጀልዱ ወረዳ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 11 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ቢቂላ ገልጸዋል። ሕገ ወጥ የቤት ግንባታን ከማፍረስ ጋር በተያያዘ ጥቅማቸው የተነካባቸው ያሏቸው ሰዎች ግድያውን በተደራጀ መንገድ ሳይፈጽሙ እንዳልቀረ ጥርጣሬ እንዳላቸው ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ፖሊስ የምርመራ እያከናወነ ሲሆን ምርመራው ሲጠናቀቅ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም ታውቋል። በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ግድያ በሳምንት ውስጥ ይህ ለኹለተኛ ጊዜ ሲሆን ኅዳር 10/2012 በምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ ውስጥ የኦሮሚያ የመንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ኃላፊ የነበሩት ቶላ ገዳ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የምዕራብ ሸዋውን ግድያ ጨምሮ ባለፉት ኹለት ወራት በምዕራብ ኦሮሚያ ሦስት ዞኖች ብቻ ስ የመንግስት ባለስልጣናት መገደላቸውን ግድያዎቹ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች የመንግስት ኃላፊዎች ማስታወቃቸው ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here