ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 17/2012

0
676

1-የእንስሳት መድኃኒት ለማምረት በመቶ ሚሊዮን ብር የተገነባው ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ለአራት ወራት ያለሥራ መቆሙን የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወል አብዱልጀባል እንደተናገሩት የፋብሪካው ግንባታ በ2009 ተጀምሮ ከአራት ወራት በፊት ሙሉ ለሙሉ ቢጠናቀቅም በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ወደ ሥራ መግባት አለመቻሉን ገልጸዋል።(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
………………………………………………………………
2- በኦሮሚያ ክልል የተሽከርካሪን ፍጥነት የሚቆጣጠር መሣሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚገጠም የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ገልጸዋል።ባሳለፍነው ሳምንትም በሶስት ቀናት ብቻ 36 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ ያስታወሱ ሲሆን ለዚህ የትራፊክ አደጋም የአሽከርካሪዎች በፍጥነት ማሽክርከር እና የአገሪቱ መንገድ ሁኔታ እንዲሁም የአሽከርካሪዎች ስነ ምግባር ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።(አዲስ ማለዳ)
………………………………………………………………
3-በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የህፃናት ማቆያ ለመክፈት የዲዛይን ስራ ተሰርቶ ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ጀማል አባሶ አስታውቀዋል።የህጻናት የፊደል መቁጠሪያ እና ማቆያ ቦታ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ 123 ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባለመገኘቱ ከወላጆቻቸው ጋር ማረሚያ ቤት የሚኖሩ ሕጻናት ሕይወት አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ ስነ ልቦናዊ ጫና ውስጥም ይከታቸዋል።የህጻናት ማቆያ ማዕከል ጉዳይ በመንግስት ደረጃም ትኩረት ያልተሰጠው ሲሆን አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ልጅ የያዙ እናቶችን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ከሌላው ታራሚ በመለየት ለብቻቸው እንዲቆዩ የማድረግ ጊዜያዊ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
………………………………………………………………
4-የጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ህዳር 1/2012 በተካሄደ ድንገተኛ አካላዊ ፍተሻ በአንድ አስመጭ በተፈፀመ የንግድ ማጭበርበር ከ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በልዩነት መገኘቱን ታውቋል።አስመጭው ይህን የፈፀመው ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በኩል ድክሌር አድርጎ ያስገባው ዕቃ ላይ በአገላለፅ ልዩነት ምክንያት የአይነት ልዩነት በመገኘቱ ሲሆን ይህም የመኪና ዕቃ መለዋወጫን ፓርት ቁጥር (part number) በመደበቅና በላዩ ላይ ሌላ ሐሰተኛ የፓርት ቁጥር በመለጠፍ አነስተኛ ዋጋ በመስጠት ለመንግስት መከፈል የሚገባው አራት ሚሊየን ሶስት መቶ ሰማኒያ ኹለት ሽሕ ኹለት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ብር ከአስር ሳንቲም ብር ልዩነት በመገኘቱ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።(አዲስ ማለዳ)
………………………………………………………………
5- በደቡብ ክልል በተቋማት የቅንጅት ጉድለት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የአፈር ማዳበሪያ ውዝፍ ዕዳ ተመላሽ ማድረግ እንዳልተቻለ የክልሉ ሕብረት ስራ ኤጀንሲ የግብዓት እና ምርት ግብይት ዳይሬክተር ደስታ ደንሳ ተናግረዋል።ማዳበሪያው ለአርሶ አደሩ ሲሰራጭ የነበረው በብድር ሲሆን በአሁኑ ወቅት ገንዘቡን ማስመለስ ባለመቻሉ በቀን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር እየወለደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
………………………………………………………………
6-ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት ከ674 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በእርዳታ እና በብድር መገኘቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታዉቋል።ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ አንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ በተጠቀሱት ወራት ወስጥ ከውጪ እርዳታ ሰጪዎች እና አበዳሪዎች 373 ነጥብ 66 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት አቅዶ ከእቅድ በላይ 674 ነጥብ 06 ሚሊየን ዶላር ማግኘቱን ገልጿል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)
………………………………………………………………
7-ኢትዮጵያ በስራ ላይ ደህንነት አለመጠበቅ እና ተያያዥ የጤና ችግሮች በየዓመቱ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚታጣ ዓለም ባንክ እና በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ሚኒስቴር ጥምረት የተሠራ ጥናት ይፋ በሆነበት ወቅትተገልጿል።በጥናቱ ላይ በግብርና 53 በመቶ፣ በኮንስትራክሽን 28 በመቶ እና በመንገድ ትራንስፖርት 19 በመቶ አገሪቱ በሥራ ላይ አደጋ ከፍተኛ ገንዘብ እንደምታጣ ተረጋግጧል።ጥናቱ ኮንስትራክሽን፣ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ ትምህርት እና ግብርና ዘርፎች ከፍተኛ የሠራተኛ ቁጥር እና የአደጋ ተጋላጭነት ያለባቸው መሆኑን መለየቱን አስታውቋል።(ኢቢሲ)
………………………………………………………………
8- የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን ተማሪዎችን ለይቶ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚታየውን ወቅታዊው የሰላም መደፍረስ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲከሰት ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን ተማሪዎች የከፋ ጥፋት ሳይፈጸም ቀድሞ በመለየት እርምጃ መውሰዱን ዩኒቨርሲቲው አሳውቋል።ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም በተመሳሳይ ድርጊት የተጠረጠሩትን ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሰራተኞች ለይቶ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ(ዶ/ር)ገልጸዋል።(አዲስ ማለዳ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here