ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከባለፉት ቀናት ጀምሮ በደቡብ ትግራይ ራያ አዘቦ፣ መኾኒ ከተማ፣ በራያ አላማጣ እና ኦፍላ አካባቢዎችን ጨምሮ በትግራይ ክልል የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ መታየቱን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በወረርሽኙ ምክንያት የዜጎች ሕመምና ሞት ሊያጋጥም እንደሚችል መረጋገጡንም ጠቁሟል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ጥቅምት 22/2016 መደበኛ ስብሰባውን ያደረገ ሲሆን፤ በስብሰባውም ወረርሽኙን በዝርዝር በመገምገም፣ ስለበሽታው ለትግራይ ሕዝብ በይፋ እንዲገለጽ ወስኗል።
በዚህም መሰረት ካቢኔው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የሚመራ ግብረ ሃይል ለማቋቋምም የወሰነ ሲሆን፤ እያንዳንዱ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቢሮዎች ወረርሽኙን ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ መመሪያ መስጠቱ ተገልጿል።
የክልሉ ሕዝብም ይህንን አስቸጋሪ የጤና ኹኔታ ተረድቶ ራሱንና አካባቢውን ከዚህ በሽታ እንዲጠብቅ እንዲሁም፤ መንግሽት በየጊዜው የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ አቅርቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኮሌራ ወረርሽኝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን በመግለጽ፤ ለበሽታው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።



