ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 4 ቢሊየን 972 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ፤ 5 ቢሊየን 185 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
በዚህም ሚኒስቴሩ የእቅዱን 104 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካት መቻሉን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ ፈቃደ ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ግብር ከፋዮች አሁን ላይ ኹሉም በሚባል ደረጃ በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸው ገቢው በአግባቡ እንዲሰበሰብ እና የተሻለ እቅድ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህንን የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሰው ኃይሉ ላይ በአመለካከት እንዲሁም አቅምን የሚያጎለብቱ ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ስልጠና በመስጠት የሰው ኃየሉን በቁጥርም በጥራትም የተሻለ ለማድረግ የተሰራው ሥራ ለውጥ ማምጣቱንም አንስተዋል፡፡
“በቀጣይም የተሻለ አፈፃፀም ለማምጣት በሩብ ዓመቱ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ከዚህ በበለጠ መሰራት አለበት” ሲሉ ያሬድ አሳስበዋል፡፡



