ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል 270 ሺሕ የሚሆኑና እራሳቸውን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት በማለት የሚጠሩ የሠራዊት አባላት ዳግም ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የሰራዊቱ አባላት ለኹለት ዓመታት ከፈዴራል መንግሥት ጋር በነበረው ጦርነት ተሳታፊ የነበሩ መሆናቸውን ዘ ኒው ሂውማኒቴሪያን ዘግቧል።
“በባለስልጣናቱ የተረሳሁና እንደ ማስቲካ ታኝኮ የመጣል አይነት ሆኖ ነው የተሰማኝ” በማለት ያሉበትን ኹኔታ ያስረዳችው የ24 ዓመቷ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበረችና በጦርነቱ ወቅት ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት የደረሰባት ወጣት ናት።
ወጣቷ ከስምምነቱ በኃላ ድጋፍ እንደሚደረግላት ቃል የተገባላት እና የሥራ ዕድል እንደሚያመቻቹላት የተገለጸላት ቢሆንም፤ እስካሁን ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላገኘች ትናገራለች።
እንዲሁም የሥራ ዕድል ይመቻችላቿል ቢባልም እስካሁን ምንም እንዳልተደረገ በመግለጽ፤ በጦርነቱ ጊዜ ጉዳት የደረሰበትን ፋብሪካ በማጽዳት እየኖረች እንደምትገኝ ገልጻለች።
በተመሳሳይም አንድ ወጣት “ምንም አይነት ድጋፍ አልተደረገልንም” ያለ ሲሆን፤ ከላይ የተጠቀሰችውን ወጣት ሀሳብ በመጋራት “የተረሳን መስሎ ይሰማኛል። ምንም የተፈታ ችግር የለም። ለዚህ ብለው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መስዋዕትነትን መቀበላቸውን ማመን ይከብዳል” በማለት ስሜቱን አጋርቷል።
አባላቱ ትልቅ ችግር ዉስጥ ነው ያሉት የተባለ ሲሆን፤ በቂ መጠለያና ምግብ በሌለበት ኹኔታ በትምህርት ቤቶች ዉስጥና በሌሎች ቦታዎች መስፈራቸው ነው የተገለጸው።
በተመሳሳይም በካምፖቹ ዉስጥ ያለው ኹኔታ አስከፊ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ባሉበት አካባቢ ምንም አይነት ጥበቃ አለመኖሩም ተመላክቷል።
ዘገባው በጦርነቱ ላይ ተሳትፊ የነበሩ አካላትን ትጥቅ የማስፈታት ሂደት በዓለም ላይ ብዛት ቁጥር ያለው መሆኑን አመላክቷል፡፡ መንግሥት ሂደቱን የሚከታተል ብሔራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን ማዋቀሩም ጠቁሟል።
ይሄን ተከትሎ መንግሥት የሚመራበትን የስርዓት ማዕቀፍ በማዘጋጀት 15 በመቶ ወጪውን በራሱ ለመሸፈን አቅዶ የተባበሩት መንግሥታትን እርዳት የጠየቀ ሲሆን፤ የገንዘብ ድጋፍ አለማግኘቱን ተከትሎ ሥራው እስከ አሁን አለመጀመሩም ተገልጿል።
የብሔራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን መሪ የሆኑት ተሾመ ቶጋ የሂደቱን በዝግታ መሄድ ያመኑ ሲሆን፤ ለዚም “ከባዶ በመጀመራችን ነው” ማለታቸውን ዘገባው ገልጿል።
አክለውም ታጋዮቹን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል የሚያስችል ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ አለም ዓቀፍ መርሆችን መሰረት ያደረገ መርሀ ግብር መዘጋጀቱ አመላክተዋል።
በመጨረሻ “ይሄ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው እነዚህ ሰዎች ለጦርነት የሰለጠኑ ናቸው። እነሱን ያለክትትልና ድጋፍ መተው ከባድ አደጋዎች አሉት ይሄንን ሁሉም ሰው የሚገነዘብ ይመስለኛል” ሲሉም ገልጸዋል።
የሂደቱ መዘግየት መደበኛ ባልሆኑ ካምፖች ዉስጥ የሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎችን ሊያስቆጣ እንደሚችልና መረጋጋት የጀምረውን የትግራይ ሰላም መልሶ ሊያደፈርሰው ይችላል የሚል ስጋት መኖሩም ተመላክቷል።



