ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር 139 ፍልሰተኞችን ወደ አገራቸው መመለሱን አስታወቀ።
ተመላሾቹ በዚህ ሣምንት በኹለት ዙር በተደረገ ትብብር ወደ አገራቸው የተመለሱ መሆናቸውን ኤምባሲው ገልጿል።
የኢትዮ-ጂቡቲ-የመን መንገድ እጅግ አደገኛና የተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በተደራጀ መልኩ የሚፈፀምበት ቦታ ከመሆኑም በላይ፤ በየቀኑ ዜጎችን ለሞት እየዳረገ ያለ አስፈሪ መንገድ መሆኑም ተመላክቷል።
ይህንን ለመቅረፍም በሚዲያ ተቋማት ማህበረሰቡን በማስተማር፣ ከሕግ እና ጸጥታ ተቋማት ጋር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል መከላከል ሥራዎች ላይ በጋራ በመስራት እንዲሁም ፍልሰተኞችን ወደ አገር ቤት በመላክ በየቀኑ እየተባባሰ ያለውን የስደት ሞት መቀነስ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።
በቀጣይ ቀናትም ሕገ-ወጥ ፍልሰተኞችን ወደ አገር ቤት የመላኩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኤምባሲው አስታውቋል፡፡



