ኹለቱ ጎራዎች በአሜሪካ

0
394

ባሳለፍነው ሳምንት በሕግና አስተዳደር እኔን የሚስተካከለኝ የለም፣ እኔ የዴሞክራሲ መለኪያ ነኝ ባይ፤ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በኹለት ጎራ የተከፈሉ ኢትዮጵያዊያንን ጩኸትና ተቃውሞ ስታስተናግድ ሰንብታለች። የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ በፖለቲካ አክቲቪስትነቱ የሚታወቀው ጃዋር መሐመድ እና በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኛ እና የሰብኣዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ በቀናት ልዩነት አገረ አሜሪካን ረግጠዋል።

በዚህ የአሜሪካ ጉዞ ታዲያ በተለይም ደግሞ ጃዋር አድባር የተቀበለችው አይመስልም። ከደጋፊዎቹ እና ከአድናቂዎቹ ጋር የገጽ ለገጽ ውይይት ለማድረግ በርካታ መርሃ ግብሮችን ቢያቅድም፣ በሔደበት ኹሉ ጠንከር ያለ ተቃውሞ መርሃ ግብሮችን እስከ ማስሰረዝ የዘለቁ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ገጥመውታል።

ዴንቨር ኮሎራዶ፣ ሲያትል፣ ዋሽንግተን ዲሲ እነዚህ ኹሉ በጃዋር ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች አቅላቸውን የሳቱ የአሜሪካ ከተሞች እና ግዛቶች ነበሩ። ‹‹ጃዋር ገዳይ ነው፣ አሸባሪ ነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጠፉት ነፍሶች ተጠያቂ ሊሆን ይገባል›› እና መሰል መፈክሮችን ከፍ አድርገው ያውለበለቡ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከምሥራቅ አሜሪካ ጫፍ ምዕራብ አሜሪካ ጠርዝ ድረስ ተሰድረው ሰንብተዋል።

በተለይ ደግሞ በሲያትል ጎዳናዎች ላይ የግዛቷ ዝነኛው የዜና አውታር የዜና ሽፋን እስኪሰጠው ድረስ የኦቦ ጃዋርን ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች፣ የአንዲት እናት ልጆች እሰጥ አገባ እጅግ ላቅ ያለ ነበር። ማዶ ለማዶ ተኹኖ የቃላት ውርወራው፣ ፀያፍ ስድድቦች አንዳንዴም ሳቅ የሚያጭሩ መዘላለፎች በስፋት ታይተውበት በአገር ቤት ዘንድም ትዝብትን ሲጭር ሳምንቱ ተገባዷል።

በሌላው በኩል ደግሞ እምብዛም ያልተጮኸለት ከተቃውሞው ድጋፉ የበረከተለት የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በዋሽንግተን ተገኝቶ ነበር። በዚህ ወቅት ታዲያ የአዲስ አበባ ባለአደራ ኮሚቴ (ባልደራስ) ወደ ፖለቲካው ጎራ ለመቀላቀል እየተንደረደረ እንደሆነም የሚያትቱ ንግግሮችን አሰምቷል። የሳምንቱ መነጋገሪያ የሆኑት የእነዚህ ኹለት ተጽእኖ ፈጣሪዎች የአሜሪካ ጉዞ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾችም ሲቦካ እና ሲጋገር የሰነበተ የሳምንቱ መነጋገሪያ፣ ሐሳብ መሰናዘሪያ ባስ ሲልም ቡድን መለያ የሆነ ጉዳይ ነበር።

በጃዋር ጉዳይ እምብዛም ግድ የማይሰጣቸው ግለሰቦች የተደረገበትን ተቃውሞ እና ትእይንተ ሕዝብ በመታዘብ ፍትኀዊ አይደለም በማለት ወደ ዘርና ሐይማኖት ሲያያይዙት ሰንብተዋል። ይህንም ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ፣ ጃዋርን እደግፋለሁ›› የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቲሸርት ያደረጉ ወጣቶች ምስል በስፋት ሲሰራጭ ሰንብቷል። ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያዊያንን በተለይ ደግሞ በአገረ አሜሪካ የሚኖሩትን በአንድ ሰው ጉዳይ ኹለት ቦታ የከፈለ ቡድናዊ ሳምንት ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here