የሐኪሞች እና ነርሶች ፍልሰት ዓይደር ሆስፒታልን ጫና ውስጥ እያስገባው ነው

0
453

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ በዓመት ውስጥ በትላንትናው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ የጎበኙት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዓይደር ሆስፒታል የሰራተኞች ፍልሰት አሳሳቢ እንደሆነበት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ከተደረገው ጦርነት አስቀድሞ ከ10 ሚልየን በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች ህክምና እና ተጓዳኝ አገልግሎቶች ሲሰጥ የቆየው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዓይደር ሆስፒታል ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ቁሳዊ ጉዳቶች ደርሰውበታል። 

በዚህም ከድንገተኛ ህክምና ውጭ ስራ ማቋረጥን ጨምሮ የተጓደለ አገልግሎት እየሰጠም ቢሆን ተቋሙን መልሶ ለማደራጀት የሚደረገውን ጥረት የባለሞያዎች ፍልሰት እንዳከበደበት የዓይደር ሆስፒታል ቺፍ ነርሲንግ ኦፊሰር ኤደን ካሳሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ዓይደር ሆስፒታል የማስተማሪያ ተቋምም ስለሆነ ከጦርነቱ መጀመር በፊት በጠቅላላ 4 ሺህ ሰራተኞች የነበሩት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 4 ሺህ 600 የሚሆኑት የዓይደር ሆስፒታል ሰራተኞች ቢሆኑም በዚህ ወቅት ግን ሰራተኞች በየጊዜው ከሆስፒታሉ እየለቀቁ ይገኛሉ።

“4 ሺህ 600 የሚሆኑት የዓይደር ሆስፒታል ሰራተኞች የነበሩ” ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ በመቶዎች የሚሆኑት ለቀው “አሁን 3 ሺህ 200 አካባቢ” የሚሆኑ ሰራተኞች እንደሚገኙ ኤደን ካሳሁን ተናግረዋል።

በተጨማሪም “አሁን በጣም ፈተና የሆነው የሐኪሞች እና የነርሶች መልቀቅ በብዛት አለ፣ ወደሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ ነው” የሚሉት የዓይደር ሆስፒታል ቺፍ ነርሲንግ ኦፊሰር ኤደን ካሳሁን፤ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ከወርሃዊ ክፍያ በተጨማሪ የምደባ ጊዜ የሚሰላበት (በተለምዶ ዲዩቲ) ክፍያ የሚታሰብላቸው ቢሆንም ባለፉት 17 ወራት ምንም ዓይነት ክፍያ አለመከፈሉ ተጨማሪ ተግዳሮት ሆኗል ሲሉ አሳስበዋል።

የህክምና ባለሞያዎች በብዛት ወደውጭ ሀገራት እየተጓዙ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥም ወደተለያዩ አካባቢዎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እየወጡ መሆኑንም አዲስ ማለዳ ተገንዝባለች። 

እንደሆስፒታሉ ምንቾች ገለጻ ጦርነቱ ሲቆም ያልተከፈሉ ክፍያዎች ተከፍለው ስራ እንደሚቀጥሉ የበርካታ ሰራተኞች ተስፋ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተከፈለ ክፍያ አለመኖሩ ከጊዜ ወደጊዜ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ለመልቀቃቸው ምክንያት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ያለው የኑሮ ውድነትም ለሐኪሞችና ነርሶች መልቀቅ ሰበብ እንደሚሆን ተጠቅሷል።

በዚህ ከጦርነት ማግስት የዓይደር ሆስፒታል አገልግሎትን ለማሻሻል የቁሳቁስ ርብርብ በሚደረግበት ወቅት የሰው ሀብት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ነው ያሉት ኤደን ካሳሁን የሚወጡትንም የሚተካ ባለሙያ አለመገኘቱ ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ያመለክታል። 

በየጊዜው የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ ፈተና ግን እየበዛ ቢሆንም ከሶስት ዓመታት በፊት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቁሳቁስ ምንም ጥገና አልተደረገላቸውም መባሉንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ በትላንትናው ዕለት በዓይደር ሆስፒታል ተገኝተው አገልግሎቱን የጎበኙ ሲሆን ያለውን ክፍተት በሚገባ እንደጠቆሙ እና ለዚህም ብዙ ነገር እንጠብቃለን ሲሉ የሆስፒታሉ ቺፍ ነርሲንግ ኦፊሰር ተስፋቸውን ገልጸዋል። ከስምንት ወራት በፊትም የጤና ሚኒስትሯ ጎብኝተውት የሄዱት ሆስፒታል ብዙ አዲስ ነገር የለውም የተባለ ሲሆን “ብዙ ተስፋ ተሰጥቶናል፤ ተስፋ እናደርጋለን፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ጥሩ አይደለም” ሲሉ ኤደን ካሳሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የዓይደር ሆስፒታል በአሁኑ ሰዓት የኩላሊት ታማሚዎች ትጥበት የሚያደርጉበት የዳያሊሲስ ህክምና ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የሚገኝ ሲሆን ሲቲ ስካን (CT Scan) እንዲሁም በክልሉ በዓይደር ሆስፒታል ብቻ የሚገኘው ኤም አር አይ (MRI) መሳሪያም አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ አውቃለች።

ከዚህ ባለፈ የሆስፒታሉ የድንገተኛ ህክምና ቦታው ደረጃውን የጠበቀ ካለመሆኑ ባለፈ ለሁሉም ታካሚ መድረስ የሚቻልበት የሰው ሀብት እና የቁሳቁስ የለም ተብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here