ውክልና ከማኅበረሰቡ አካል ሆኖ በመውጣት የሚገኝ አይደለም የሚሉት በፍቃዱ ኃይሉ፤ የውክልና አረዳዳችን ትክክለኛም ሆነ አግባብ እንዳልሆነ ያነሳሉ። በዚህም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተባሉና የሆኑ ክስተቶችን እንደማሳያ አስቀምጠው፤ የውክልና ነገር በፖለቲካው እንዲሁም በማኅበራዊ ኑሮ እያስከተለ ያለውን ቀውስ ያብራራሉ። አንድ ድርጊት አድራጊውን ብቻ ይወክል ይሆናል እንጂ፤ አድራጊው ወጥቶበታል የሚባለውን ማኅበረሰብ ይወክላልም ሆነ አይወክልም ብሎ ማሰብ የደቦ ፍርደ ገምድልነት ነው ሲሉም ይሞግታሉ።
የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ፣ እ.ኤ.አ. በ2013ቱ “የቢግ ብራዘር” ትዕይንት ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያዊት በትዕይንቱ ላይ ፆታዊ ግንኙነት ፈፅማለች በሚል ከማኅበራዊ ሚዲያው እስከ መደበኛው ድረስ በቁጣ ተንጠን ነበር። “ተዋረድን” የሚል የቁጭት ድምፅ እዚህም እዚያም ሲውለበለብ ነበር። ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያን “መልካም ሥም” በዓለም ፊት ስላጎደፈች፣ ኢትዮጵያውያንን ወክለው ‘እንከሳታለን’ የሚሉ “ጠበቆችም” በየሚዲያው በውዳሴ ሥማቸው ሲነሳ ነበር።
ከዚህ መለስ ያሉት ሰዎች ደግሞ “ከእናንተ መካከል ሀጢያት ያልሠራ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት” የሚል የኦሪት ዘመን ፍርድን የሻረ ርሕራሔ ለማሳየት ሞክረዋል። ሌሎቹ ደግሞ “የነውሯ ክፋቱ አገራዊ ገጽታ የሚያበላሽ መሆኑ ነው” አሉ። የድርጊቱን ወንጀል አለመሆን ለጊዜው እንርሳውና፥ ነገሩን ሴቲቱ አድርጋው ቢሆን እንኳን ኢትዮጵያዊ ከመሆኗ በቀር ኢትዮጵያን ወክላ የሔደችበት ሁኔታ የለም።
ኢትዮጵያዊ በመሆኗ ብቻ ትወክለናለች ቢባል እንኳን የበላችው፣ የጠጣችው እንደማይወክለን ሁሉ ይህም እንደዚሁ መታየት ነበረበት። ግለሰቦች የፈለገውን ዓይነት ቡድን ውስጥ ቢገኙ የግል ነጻነት (personal autonomy) አላቸው፤ በደቦ አስተሳሰብ ግን እንደዛ አይባልም። ስለሆነም ወጣቷ በደቦ ተወገዘች። በዚህም ሳቢያ ወደ አገር ቤት መመለስ ፈርታ በዚያው እንደቀረች ሰማን። መጨረሻዋ ምን እንደሆነ ሲነገር አልሰማሁም።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ግለሰቦች በግለሰብ አቅማቸው የወሰኑትን ውሳኔ፣ የቡድን በማድረግ ከአቅማቸው በላይ አሸክምና ኀላፊነት እንጭንባቸዋለን። ይህ ሸክም አንዳንዴ እነርሱን ቀጭቶ ይገድላቸዋል። ሌላ ጊዜ በእነርሱ ሥም ሌላ ሰው ላይ የደቦ ፍርድ ያስፈርዳል።
“እኛን አይወክሉንም”
በሌላ በኩል፣ ብዙ ጊዜ ግለሰቦች የሚያደርጓቸው መልካም ነገሮች እና የሚያስገኟቸው ድሎች የማኅበረሰባቸው ወይም የአገራቸው ድሎች ተደርገው ይቆጠራሉ። ነገር ግን ሌሎች ግለሰቦች የሚያስነውር ጥፋት ሲሠሩ ደግሞ ድርጊታቸው “እኛን አይወክልም” ይባላል። በተለይ በአገራችን ፖለቲካ በጦፈው ብሔርተኝነት እና በተወሰነ ደረጃም ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ዙሪያ ተመሳሳይ ነገር ይነገራል። ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲፈፀም “ኦሮሞን አይወክልም፣ አማራን አይወክልም…” ሲባል እንሰማለን። መስጊድ ወይም ቤተ ክርስትያን የእምነቱ ተከታዮች ባልሆኑ ሰዎች ጥፋት ሲደርስበት “ክርስትያንን አይወክልም፣ ሙስሊሙን አይወክልም…” ይባላል።
ዩቫል ሃራሪ “21 Lessons for 21 Century” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አል ባግዳዲ የተባለው የአይሲስ መሪን ጠቅሰው፣ ክርስትያኑ ባራክ ኦባማ “አል ባግዳዲ እስልምናን አይወክልም” ብለው መከራከራቸውን በትዝብት ይጠቅሳሉ። እንደ ሃራሪ ገለጻ ስለ አንድ እምነት መናገር የሚችለው አማኙ ራሱ ነው። አል ባግዳዲ ሙስሊም ነኝ፣ ይህም ድርጊት የእስልምና ነው፣ ካለ ክርስቲያኑ አይደለህም ሊለው አይችልም እንደማለት ነው። በሃራሪ ቋንቋ “እስልምና ሙስሊሞች ሁን እንዳሉት ይሆናል።”
በየትኛው እምነት እና ብሔራዊ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እምነታቸውን የሚተገብሩበት ፍልስፍና ወይም ብሔረሰባቸውን እንዳገለገሉ የሚቆጥሩበት ማኅበራዊ-ግላዊ አረዳድ አላቸው። “አንድን ቡድን ወክለን ነው ያደረግነው” የሚሉት ነገር ብዙ የሚያስደስታቸው ወይም የሚያስከፋቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
ነገር ግን እነርሱ ድርጊቱን ሊፈፅሙ የሚችሉት ራሳቸውን ወክለው ነው። የየትኛውም እምነት ተከታይ ወይም የየትኛውም ብሔራዊ ስብስብ አባል ተሰብስቦ “እኛን ወክለህ እነ እከሌን አጥቃልን” የሚል ውክልና እስካልሰጠ ድረስ “እነ እከሌን እወክላለሁ” ማለት አይችልም። ይሁንና “እኛን አይወክሉንም” የማለት ውክልና የተሰጣቸውም ሰዎች የሉም። እዚያው ስብስብ ውስጥ ድርጊቱ ይወክለናል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ይወክለናል የሚሉትን አይወክሏችሁም ማለት እወክላችኋለሁ ከማለት አይለይም።
የአንድን ግለሰብ ድርጊት ግለሰቡ ወጥቶበታል የሚባለውን ማኅበረሰብ ይወክላል ብሎ ብቻ ሳይሆን አይወክልም ብሎ ማሰብም የደቦ ፍርደ ገምድልነት ሊሆን ይችላል። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ድርጊቱ አድራጊ ግለሰቡን እንደሚወክል ብቻ ነው።
የውክልና ፖለቲካ
ውክልናን ብዙ ሰዎች የሚረዱት ከአንድ የማኅበረሰብ ክፍል የወጡ ግለሰቦች ማኅበረሰቡን ወክለው ሲሠሩ፣ ሲናገሩ ወይም ሌላ ነገር ሲያደርጉ ነው። እንበል በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ 10 ሴቶች እና 10 ወንዶች አሉ። ይህም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሴቶች 50 በመቶ ውክልና አግኝተዋል ይባላል። በርግጥ በነባራዊው እውነታ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ቦታዎች ላይ ስለማይታዩ የመጣ እንደሆነ መረዳት ቢቻልም፥ ወንዶች 50 በመቶ ተወክለዋል ሲባል አንሰማም። የሆነ ሆኖ ይህ ዓይነቱ ውክልና ምን ዓይነት ውክልና ነው? እውን ሴት ሚኒስትሮቻችን ኢትዮጵያውያንን ሴቶች ይወክላሉ? በምን መንገድ?
ሌላኛው የውክልና አረዳድ ደግሞ አንድን ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ሰው ተመሳሳይ ሐሳብ ወይም አጀንዳ የሚያንፀባርቁ ሰዎችን ወክሎ ሲናገር ወይም ሲቀርብ ነው። እንደምሳሌ “በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ” የዛሬ 50 ዓመት ገደማ የጻፋት መጣጥፍ እስካሁን የምታነጋግርለት ዋለልኝ መኮንንን እንውሰድ። ዋለልኝ በዛሬው የብሔር አረዳድ አማራ ነው ተብሎ ይታመናል። ይሁንና ብዙዎቹን የአማራ ብሔርተኞችን ብንጠይቅ ዋለልኝ አማራን አይወክልም እንደሚሉ አያጠራጥርም። ውክልና ከማኅበረሰቡ አካል ሆኖ በመውጣት የሚገኝ አይደለም። ነገር ግን አስተሳሰቡን የሚደግፉለት የሌላ ዘውግ ብሔርተኞች የሐሳቡን ውክልና ቢቀበሉም እንኳን እኛን ወክሎ ምክር ቤት ይግባልን አይሉትም።
“እኔን አይወክለኝም”
በኢትዮጵያ ፖለቲካ “እኔን አይወክለኝም” የሚለውን ሐረግ ያክል የማስታረቅ ኀይል ያለው ነገር ግን ወዳጅ አልባ ንግግር የለም። አማራ ነን ወይም ትግሬ ነን የሚሉ ወይም ደግሞ እነርሱ ባይሉም እኛ በማኅበራዊ ትውስታችን እንደዚያ ናቸው ብለን የምናወሳቸው የቀድሞ መሪዎች ‘እንደዚህ ዓይነት በደል በእንደዚህ ዓይነት ሕዝብ ላይ አድርሰዋል’ ሲባል “እኔን አይወክለኝም” ለማለት ድፍረት ያላቸው ግለሰቦች፣ ምናልባት ስለ እውነት ፍለጋ፥ የሐቅ ማጣራት ውስጥ ካልገቡ በቀር ለፀብ የሚጋበዙበት ምክንያት የለም። ነገሩ በታሪክ ብቻ የሚገደብ አይደለም። እንደግለሰብ መቆም መፍራት እና ብዙ መዘዝ ያስከትላል።
ብሔርተኝነት ብዙ ጊዜ ባልሠሩት ሥራ መኩራት ወይም ራስ ላይ ባልደረሰ በደል መቆዘም ነው። ኹለቱም በውጤታቸው አደገኛ ናቸው። ኩራቱ ወደ ትምክህት፣ ቁዘማው ወደ በቀል በቀላሉ ይሸጋገራሉ። “እኔን አይወክለኝም” የሚለው ሐረግ ከኹለቱም ያድናል። እዚህ ላይ አንድ ድርጊት የሚወክለው አድራጊውን ነው የሚለው ከተጨመረበት “ፀብ ያለሽ በዳቦ ቀይሪኝ” እያሉ ቢፈልጉት እንኳን አይገኝም።
በቅርቡ በየዩኒቨርሲቲው የተከሰቱት ግጭቶች ካየናቸው ከዚህ የመነጩ ናቸው። በተማሪዎቹ ሞት ከሚከሰተው ሐዘን ባልተናነሰ፥ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚዛመትበት ሰበብ ልብ ይሰብራል። ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ተማሪዎች በመገደላቸው ምክንያት ሌላ በየዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ አማራ ተማሪዎች በሙሉ ተጠያቂዎች እና የጥቃት ዒላማዎች ሆኑ። ከዚህ በፊትም አማራ ክልል ያለ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነ ትግራይ ተወላጅ በደቦ ፍርድ ሲገደል፣ ትግራይ ክልል ያለ አማራ የዩኒቨርሲቲ ተወላጅ በደቦ ፍርድ ተገድሏል።
የውክልና አረዳዳችን አቅሉን ሲስት ውጤቱ እስካሁን እንዳየነው ነው። የዛሬ መቶ ዓመት ለተሠራ ስህተት የሱን ቋንቋ የሚናገር ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ሌላ ሰው ተጠያቂ ይሆናል። የዛሬ መቶ ዓመት ለተሠራ ስኬትም ወራሹ የማያውቀው “ወገኑ ነኝ” ባይ ነው። ኮምፓሱን የሳተው የውክልና አረዳድ የዘመንን፣ የቦታ እና የሐሳብ ውክልና አያውቅም። መርሑ “ከእኛ ካልሆንክ ከነርሱ ነህ” ሲሆን፥ የሚያሳዝነው ከ“እኛም” እኔን አይወክልም፣ ከ“እነርሱም” እኔን አይወክልም ባይ መጥፋቱ ነው። ግለሰቦች ራስ ገዝ ባልሆኑበት፣ ቡድኖች ራስ ገዝ ይሆናሉ ማለትም ዘበት ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012