የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመጾች ከትላንት እስከ ዛሬ

0
1449

ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ነው፤ መስፍን ማናዜ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሒሳብ፣ ኹለተኛውን በትምህርትና እቅድ ሥራ አመራር አግኝተዋል፤ አሁን ላይ ደግሞ በትምህርት ፖሊሲ አስተዳደር እጩ የሦስተኛ ዲግሪ (ፒ ኤች ዲ) ተማሪ ናቸው። መማር ብቻ አይደለም፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ዘልቀው አስተምረዋል፣ ጥናቶች አድርገዋል አልፎም በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

መለስ ብለው በዩኒቨርሲቲ የነበራቸውን ቆይታ ሲያስታውሱ፤ ከአሁኑ ጋር ያለውን ልዩነት ሳይጠቁሙ አያልፉም። በእርሳቸው የተማሪነት ዘመንም የተለያዩ የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያየ መንገድ እንደሚነሱና እነዚህም ግን በትምህርት ስርዓትና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ብቻ ነበሩ ይላሉ። ቆይታቸውም በአብሮነትና በመቻቻል የታጀበ ጥሩ ጊዜ እንደነበር ያወሳሉ።

መስፍን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አንድም በውስጣቸው ተማሪ በመሆን፣ አንድም ከመምህርነት ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች በማገልገል፤ የተቋማቱንና የተማሪዎችን እንዲሁም በዙሪያው ያሉ ሁኔታቸውን በሚገባ የተረዱ ሰው ናቸው ለማለት ያስደፍራል። ከዚህ በመነሳት አሁን ላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተስተዋሉ ስላሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እንዲሁም ተቋማቱ ከታሪክ አንጻር የአገር ፖለቲካና ማኅበራዊ ኑረት ላይ የነበራቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ከአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ ጥያቄዎች በተቃውሞ መልክ መነሳት የጀመሩት መቼ ነው?
ይህን በሦስት እንክፈለዉ፤ እንደሚታወቀዉ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ነዉ የከፍተኛ ተቋማት ትምህርት የተጀመረው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ቀዳሚ ሆኖ ነው የተቋቋመው። እዉነት ለመናገር ታሪክን ብናየዉ፣ እነዚህ ከኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ባሉት ሦስት መንግሥታት ውስጥ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ፖለቲካ ተኮር እንቅስቃሴ ነበር። ግን ዓይነቱ እና ይዘቱ ይለያያል ነው።

ይህ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ምኁራን የተስማሙበትና ያጠኑት ነገር ነው። በኃይለሥላሴ ጊዜ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ነበር። እንቅስቃሴው በአብዛኛው በብሔር እና በሃይማኖት ሳይከፈል ለጭቁኑ ሕዝብ ድምጽ መሆን ነው። በወቅቱ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ብናይ፤ ‹ወሎ ላይ ረሃብ አለ እሱ እንዴት ሆነ›፤ ‹የመንግሥት አወቃቀር በአግባቡ አገሪቱን እያገለገለ አይደለም›፤ ‹አሁን ያለው አወቃቀር የትም አያሻግርም› ዓይነት እንጂ የአማራ፣ የኦሮሞ ወይ የትግሬ ጥያቄ አይደለም፤ እንደ ተማሪ የሚጠየቅ ነዉ።

እነዚህ ጥያቄዎች ተማሪዎችን ከመንግሥት እንዲሁም ከፖሊስ አካላት ጋር አፋጥጠዋል፤ በደንብ ተጋፍጠዋል ግን እንደ ተማሪ ነው። በመካከል የሚነሱ ችግሮች ይኖራሉ፤ መነቋቆር ሊኖር ይችላል፤ በብሔር፣ በሐይማኖት የተለያዩ ነገሮች ሲደረጉ ግጭቶች ይፈጠራሉ፤ ምግብ ተበከለ ዓይነት ነገር ሊኖር ይችላል። ዋናዉ ቁም ነገር የነበረው ግን ለሕዝቦች ድምፅ መሆን ነዉ።

ብዙ ጊዜ የሚነሳው ደርግም ሆነ ኃይለሥላሴ የወደቁት በተማሪዎች ንቅናቄ ነዉ። በኃይለ ሥላሴ ላይ የሪፎርም ጥያቄዎች ስለነበሩ በዛ ምክንያት መንግሥት ወደቀ፤ ደርግ መጣ። ደርግ ላይ ደግሞ በተለይ የትምህርት ስርዓቱን ከሶሻሊስት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ጋር በማነካካቱ እና ጥብቅ የሆኑ ቁጥጥሮች ዩኒቨርስቲዎች ላይ በመፈለጉ ምክንያት፣ ተማሪዎች በድጋሚ ተነሱ። መጀመሪያ ላይ የደርግ መንግሥትን ራሱ መሬት ለአራሹ እና ሌሎች በኃይለ ሥላሴ የተነሱ የተወሰኑ ጥያቄዎች ስለተመለሱ ከደርግ መንግሥት ጋር ተስማምተዉ ነበር። ግን በጊዜ ሒደት የሚነሳው የሕዝብ ጥያቄ ስለሆነ፤ ወታደራዊ መንግሥት ፈርሶ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፤ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ይሁን፣ የሚሉ ጥያቄዎች እንደገና በተማሪዎች ኅብረት መጠየቅ ጀመሩ።

በአጠቃላይ ሲታይ፣ በኃይለሥላሴ እና በደርግ የነበረዉ የተማሪዎች ንቅናቄ ያተኮረዉ፣ አገራዊ ጉዳዮች ጋር፤ እነርሱ ተበድለዋል ብለዉ ለሚያምኑት ድምጽ ከመሆን ጋር፣ ከትምህርት ነጻነት ጋር፤ አልፎ ተርፎ የራሳቸዉን ማኅበር (የተማሪዎች ኅብረት) ማቋቋም ጋር የተያያዘ ነበር። የራሳቸው ልሳን ነበረቻቸው።

ከዛ ደርግ ሔደ አሁን ያለዉ መንግሥት መጣ። በአሁን ጊዜ በተማሪዎች የሚታየዉ በተለይ ከመምህራን ጋር ብዙም የማያረካ ግንኙነት ነው። አንድ ክስተት ብናነሳ፤ መንግሥት ባያምነዉም ከ40 በላይ ፕሮፌሰሮች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለ አግባብ ተባርረዋል። ከዛ ዉጭ በ1993 [ጊዜውን ካልተሳሳትኩ] ይመስለኛል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት ያህል ተዘግቶ ነበር። ተማሪዎች የሌሎች ተማሪዎች ጥያቄ ይመለስ በሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ከፖሊስ ኃይል ጋር ተጋጭተው ተዘግቶ ነበር።
አሁን የምናየው ግን ከዚህ ጉዳይ የተለየ ነው። ይመስለኛል አገሪቱ የብሔር ፌዴራሊዝም በመከተልዋ ምክንያት (አግባብነት የለዉም ማለቴ አይደለም) ብዙኀኑ ለብሔር ስሱ (ethnic sensetive) ሆነ። ስለዚህ አሁን እየሆነ ያለው እንደ በፊቱ አገራዊ ከመሆን ይልቅ የራስን ጎሳ ወይም ዘዉጌነት ላይ ተመርኩዞ እንቅስቃሴ ማድረግ። ይሄ ደግሞ ኹለት የተለያየ ብሔር ያላቸዉ ተማሪዎች መካከል ግጭት አመጣ።

ለምን? ታሪኩ በራሱ እንደሚባለው፤ ድሮ የመደብ ልዩነት አለ ነበር። ብሔር ሳይነካ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ የሚባል ሕዝብ አለ። አሁን ተለይቶ ወደ ብሔር የመጣ ይመስላል። ያ አስተሳሰብ ስላለ፤ አንዳንዴ እንደ አገር የሚያሳዝን እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪነት ከተማሪዎች የማይጠበቅ የብሔር ግጭት በተቋማቱ እናያለን። በአጠቃላይ አዝማሚያውን ስናየዉ ከአገራዊ ጉዳዮች መጥቶ መጥቶ ወደ ብሔር ተኮር ደረጃ ላይ ነዉ። የሃይማኖት ነገርም ነበረው፤ እሱ ስለተዳፈነ፤ ተቋማቱ ዓለማዊ (Secular) ናቸው ተብሎ እንዲቆም ስለተደረገ ነው።

አሁን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠየቁና የሚነሱ ጥያቄዎች ግልፅ ናቸው? አጀንዳቸውስ ምንድን ነው?
በራሱ በትምህርት ጽንሰ ሐሳብ ላይ የትኛውም የትምህርት ተቋም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድረስ፣ ከማኅበረሰቡ ተጽእኖ የተለየ አይደለም። ሲስተም ሞዴል የሚባል ነገር አለ፤ የትምህርት ተቋማት በውጪው እንቅስቃሴ ማለትም በፖለቲካ፣ በማኅበረሰቡ፣ በመንግሥት፣ በፖሊሲ ተከብበዋል። ባዶ ስፍራ ላይ ያሉ አይደሉም። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማለት አዲስ አበባ ላይ ያለ ነው፤ የአዲስ አበባ ፖለቲካና የአዲስ አበባ እሳት ይገርፈዋል። አክሱም ዩኒቨርሲቲም እንደዛው። የትምህርት ተቋማት ከውጪው አካባቢ ጋር መስተጋብር አላቸው።

አሁን ላይ ያሉት አጀንዳ አላቸው ወይ? አጀንዳ ካላቸው የሚያውቁት ተማሪዎቹ ናቸው። ግን የማንክደው አንድ ሐቅ አለ፤ የፖለቲካ አለመረጋጋት በአገሪቱ አለ። ልክ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብዝኀነት የአገሪቱን ብዝኀነት እንደሚወክለው ሁሉ፣ አንዳንድ ጊዜ የአገሪቱ ፖለቲካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሊመጣ ይችላል። ያ ማለት ከውጪ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሊንጸባረቅ ይችላል፤ መስተጋብር ስላለ።

ቀርቦ ላየው፤ በተለያየ ጊዜም ስላየነው ነው። የበፊቱ አገራዊ አጀንዳዎች ሲሆኑ የአሁኑ ደግሞ የሚመስው ‹‹እዚህ ቦታ የእኔ ብሔር ተማሪዎች ተጎድተዋል፤ ስለዚህ…›› የሚል ነው። የውጪው ፖለቲካ ነጸብራቅ ነው ማለት ይቻላል። ይሄ ከምን ጋር ሊሔድ ይችላል፤ ምንአልባት የፖለቲካ ሰዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ አንድ ጥሩ ስፍራ (landscape) ስለቆጠሯቸው ሊሆን ይችላል።

ለምን ይሆን ዩኒቨርሲቲዎች ለዚህ ተመራጭ ስፍራ የሚሆኑት?
ብዙ መላምት ልታስቀምጪ ትችያለሽ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ያንቺን ፍልስፍና እና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል በርከት ያለ ቡድን አንድ ቦታ ማግኘት በራሱ ተስማሚነት አለው። ዩኒቨርሲቲዎች ላይ እንደምናየው በተለይ በአገራችን ሁኔታ፤ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዶርም ተሰጥቷቸው አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አንድ ካምፓስ ውስጥ አብረው ነው የሚኖሩት። ውጪው ላይ የተበታተነ ማኅበረሰብ ነው ያለው፤ እየጠራሽ ነው የምታሰባስቢው። እንዲህ ምቹ አካባቢዎች [ዩኒቨርስቲዎች] ውስጥ ግን የአንቺን ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሚከተል ኹለት፣ ሦስት ወይም ዐስር ተማሪ ካለ፣ እነዛን ሰዎች ተከታይ በማድረግና ያንቺን ርዕዮተ ዓለም በተሻለ መልኩ ሊያዛምቱልሽ ይችላሉ።

በኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት እድሜ ወሳኝ ነው። ብዙ ነገር ለማወቅ የሚጓጉበት ጊዜ ነው። ልክ አንድ ሕጻን ከተወለደና መራመድ ከጀመረ በኋላ ሁሉን ለመንካት እንደሚፈልገው ሁሉ፤ ከሰውነት እድገት ጋር ሊያያይዙት ይችላል። በፖለቲካው በኩልም ፖለቲካውን ለማወቅ ጉጉ ከሆኑ ደግሞ እንዲህ ያለ አጀንዳ ሲመጣ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ።

በኢኮኖሚ እየታገሉ ያሉ ተማሪዎች ደግሞ አሉ። እንደሚታወቀው በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከቤተሰብ ተለይቶ ራቅ ወዳለ ቦታ ሔዶ ስለሚማር፤ በመደለልም ጭምር አጀንዳ መስጠት ይቻላል። በዋናነት ግን ዩኒቨርሲቲ ላይ ርዕዮተ ዓለምን በተለይ በግጭት ደረጃ የምታመጪው ከሆነ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙ ባለቤት ወይም ዋናው ከጀርባ ያለው በቀላሉ እውቅና ማግኘት እና አጀንዳን ማራፈገፍ ይችላል።

ለምን? የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሁን ላይ ማኅበራዊ ሚድያውን ይጠቀማሉ። ኢንተርኔት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል። በተጨማሪ አጥፊ አጀንዳ ከተያዘና ያንን አጀንዳ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተሰጥቶ በተቋማቱ ግጭት ተነሳ ማለት፣ ከዳር እስከ ዳር ሁሉም ጥግ ያለ ቤተሰብ ልጅ ስለላከ፣ በፍጥነትና በቀላሉ ትኩረት ያገኛል፤ እናም አጀንዳ ላለው አካል ትልቅ መድረክ ይሆናል። እነዚህ ነገሮች ይመስሉኛል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለየ ዒላማ የሚያደርጓቸው።

በእነዚህ የትምህርት ተቋማት እነዚህን ነገሮችን ማካሔድ ወይም ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ መድረክ መጠቀም በመሠረቱ ትክክል ነው?
አግባብነት አለው ወይ የሚለውን በውጤት እንገምግመው። እንደተባለው ማንኛውም ተማሪ በሰላም የሚፈልገውን የፖለቲካ መብቱን ትሰጪዋለሽ። ግን አሁን በምናየው ደረጃ ከሆነ ውጤቱ ምንድን ነው ሲባል የምንሰማው’ኮ ሞት ነው። ሞትን ማንም አይቀበል።

ከዛ በተጨማሪ በተማሪዎች መካከል ግጭት ሲመጣ ከተማሪ ሕይወት ማጣት፣ ከንብረት መውደም ቀጥሎ ቀጥታ ትምህርት ላይ የሚመጣ ነገር አለ። አሁን በአብዛኛው እንደምናየው ትምህርት ይቆማል። ይሄ ቀጥታ የትምህርት ጥራቱ ላይ ይመጣል፤ ተማሪዎች እየተማሩ አይደለም። ዐስራ አምስት ቀን እና አንድ ወር ትምህርት ከተቋረጠ፣ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ካልገቡ፤ በምንም ዓይነት ጥራት ያለው ትምህርት ይማራሉ ማለት ይከብዳል።

በተለይ አንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች የበለጠ ጊዜ የሚፈልጉ አሉ፤ ችግር ሲከሰት ግን ጊዜን አጣጥሞ አግባብነት ያለው ትምህርት መስጠት አይቻልም። አንድ ሴሚስተር አራት ወር ነው ሲባል በዘፈቀደ አይደለም፤ ትምህርቱን ለመስጠት የሚያስፈልገው ጊዜ ታይቶ ነው። ከዚሁ ላይ ያለአግባብ ጊዜ ከተነሳበት የሚፈጠረው ችግሩ ግልጽ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ እንውሰደው። አሁን ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲው ሲጋጩ ‹‹ይሄን ለቀቄ እሔዳለሁ፤ እኔ ወደ ክልሌ እሔዳለሁ›› ሲባል፤ የትም ቦታ ላይ የኢትዮጵያን መስተጋብር እናጠፋለን። አንድነት አብሮ ባለመኖር ሳይሆን አብሮ በመኖር ነው። አንድነት ስል ባለበት ቦታ፣ ማንም ሰው በብሔርም ይሁን በሃይማኖት ምንም በደል ሳይደርስበት ካልን በኋላ፣ ቀጥሎ ትልቁን ኢትዮጵያዊነት የምታመጪው አብሮ በመኖር ነው። ተማሪዎች ለቅቀው ወጡ። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው በብዝኀነት ደረጃ የሚያውቀው ነገር አለ፤ ለቅቀው ከሚሔዱ ተማሪዎች ቋንቋና ባህል አይጋሩም፤ ይህን ያጣሉ።

አስተማሪዎችም ናቸው አይደለ ከዩኒቨርሲቲዎች እየሸሹ ያሉት?
በተለይ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ላይ አሁን በምናየው ደረጃ አንዳንዶቹ ላይ በጉልህ በሚታይ መልኩ ነው የሚለቅቁት። አንዳንድ መምህራን ለቅቀው በመሔዳቸው ምክንያት በብሔሩ ያሉ ተማሪዎች ላይ ስስነት ይታያል። ያ ቀላል ተጽእኖ አይደለም ያለው። የሰው ልጅ ጸባይ ስለሆነም ተማሪ ከቦታ ቦታ ሲሔድ፤ እርሱን የሚመስል ሰው ይፈልጋል። እሱን የማይመስል ሰው ሲያይ አይደነግጥም፤ እሱን የሚመስል ሰው ካለ። እሱን የሚመስል ሰው ስንል በባህል፣ በቋንቋ የሚጋራው ነው። ከሌለ ግን ምቾት ሊሰማው አይችልም።

ወድደን አይደለም፤ ፈቅደንና ስለፈለግንም አይደለም፤ የአስተማሪዎችን ብዝኀነት የምንጠብቀው። የአስተማሪዎች ብዝኀነት ከተማሪዎች ብዝኀነት በቀጥታ ይገናኛል። አንድ ተማሪ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ከሔደ በኋላ፣ በዛው ጊዜ የትምህርትና የአካባቢ ለውጥ ጫና አለ፤ ከእነዚህ በኋላ አንዳንድ ጊዜ እሱን የሚመስለው ሰው ሲያገኝ በራስ መተማመን ሊኖረው ይችላል።

ግልጽ ነው፤ በየዩኒቨርሲቲው ሐሜት አለ። ‹‹እኛ ጋር ያሉ መምህራን ከዚህ ቡድን ስለሆኑ ይበድሉናል›› ይላሉ። ግን ተበደሉም አልተበደሉም፤ እነርሱን የሚመስል ሰው ይፈልጋሉ። ይህንንም ወድደን ያመጣነው አይደለም፤ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሔር በደንብ ስለገባን ነው። እነሱን የሚመስል ሰው ሲመጣ ቢያንስ መረጋጋት ይመጣል። በራስ መተማመንንም ሊጠብቅ ስለሚችል አግባብነት አለው።

ከታዳጊ ክልሎች አንጻርስ፤ በመምህራን ደረጃ?
አሁን በሚታየው አካሔድ እንደውም ከነዛ ክልሎች የመጡ ወደ መጡበት ክልል የሚያዘነብሉ ናቸው። መምህራንማ የሉም ማለት ይቻላል። በታዳጊ ክልሎች ያሉ መምህራን ራሱ፤ በአብዛኛው የሚመርጡት ከኖሩበት ባህልና አኗኗር አንጻር እዛው አካባቢ ዩኒቨርሲቲ ካለ፣ በዛው መቆየትን ነው። ግን መሆን የነበረበት በሆነ መንገድ አስማምቶም ቢሆን እንደ ትምህርት ተቋም ጠይቆም በየቦታው መኖር ነበረባቸው። ግን በትክክል፤ ሌላ ቦታዎች አለመሔዳቸው በጣም ትልቅ ተጽእኖ ይፈጥራል።

የፖለቲካ እና መሰል ጥያቄዎች ከየት የት ነው የሚሔዱት፤ ከዩኒቨርሲቲዎች ወደ ማኅበረሰቡ ነው ወይስ የተገላቢጦሽ?
በሒደት ባየነውና በምናውቀው ደረጃ ሲታይ፣ በኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመነ መንግሥት የነቃ የምትይው ትውልድ በዩኒቨርሲቲ ስለነበር፤ ከዩኒቨርሲቲ ወደ ውጪ ነበር የሚወረወረው [አጀንዳ]። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ምንድን ነው፤ አሁን ላይ በመንግሥት ሥልጣን ይዘው ያሉ ሰዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሰዓቱ በፖለቲካ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ናቸው። እንደውም ውጪው ላይ የነበረው የፖለቲካ ስርዓት ከለላ የሚሰጥ ነበር፤ መንግሥትን የሚከላከል። እንጂ ወሳኝ ጉዳይ የሚነሳው ከዩኒቨርሲቲዎች ነበር።
ነገሩ አግባብነት እንዳለው ማኅበራዊ ጥያቄ ነው የሚነሳው። ብዙውን አጀንዳ የሚሰጡትም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። አሁን ሲታይ ግን የሚመስለው፤ አስቀድሞ እንዳልኩት ዩኒቨርሲቲና ማኅበረሰቡ መስተጋብር አላቸው፤ እንደምንሰማውም የተማሪ ግጭት ተፈጥሮ መግለጫ ሲሰጥ ‹‹የተማሪዎች አጀንዳ አይደለም፤ ግጭት ላይ የገቡት ራሱ ተማሪዎች አይደሉም›› ነው የሚባለው።

ስለዚህ የሚመስለው የፖለቲካ አጀንዳው ራሱ ከውጪ ለተማሪዎች እየተሰጣቸው፤ አንዳንዴም በእረፍት ጊዜአቸው በደንብ እንዲያጠኑት ተደርጎ ከዛ በኋላ የገቡበት ዓይነት ነገር ነው። ያንን የተገነዘበ በሚመስል መልኩ ነው ላለፉት ኹለት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳችሁን ከፖለቲካ አጀንዳ አርቁ ሲሉ የምንሰማው። ይህ የሚያሳየው እሳቤው በመንግሥት ደረጃ እንዳለና እንደሚታወቅ ነው።

መንግሥትም ያውቃል ካልን በቂ ጥንቃቄ ተደርጓል ወይ፤ እንደ ቅድመ ጥንቃቄስ ምን መደረግ አለበት?
በሥነ ጽሑፉ ያለ ነገር ግን እኛ አገር ይጎድላል ብዬ የማስበው ነገር አለ። እንደ ኢትዮጵያ ብዝኀነት ያለበት አገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዝኀነትን አጀንዳ አድርገው ነው መኖር ያለባቸው። ስልታዊ እቅድ ወስጥ አስገብተው በብዝኀነት መገለጫ ላይ በደንብ አትኩረው እንደሚሠሩበት እርግጠኛ መሆን አለባቸው፤ በደንብ መሥራትም አለባቸው።

የፖለቲካ አጀንዳ ሲወረወር፣ እሳት ከማጥፋት የሚያድን ዘላቂ መፍትሔ በዩኒቨርሲቲ ማምጣት ያስፈልጋል። መጀመሪያ ብዝኀነትን የሚያስተናግዱባቸው ዘዴዎች መኖር ነበረባቸው።

እነዚህም፤ አንደኛ ተማሪዎችን ሲቀበሉ ጀምሮ በታቀደ መልኩ ስለ ብዝኀነት መድረክ ሊኖሯቸው ይገባል፤ ተማሪዎች የሚወያዩበት። አሁን ጥሩ ጅማሬ አለ። ለምሳሌ አዳዲስ ተማሪዎች ሲገቡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ተሰብስበው እየተቀበሉ ነው። በኹለተኛ ደረጃ ለፍሬሽ ማን የሚሰጥ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና አለ። እዛ ውስጥ በትኩረት የብዝኀነትና የእኩልነት ጉዳዮች መታየት አለባቸው። ከሌላ ብሔርና ሐይማኖት ጋር መኖርን እንዲያውቁ ሊሠለጥኑ ይገባል።
ቀጥሎ የዩኒቨርሲቲ አመራር ታትሮ በየጊዜው የተለያዩ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የባህል መሪዎችን እያመጡ ፎረሞች ፈጥሮ ተማሪዎች በነጻነት የሚያውቁትን እያነሱ እንዲወያዩ መፍቀድ አለበት። ያኔ አሁን ተማሪዎችን የሚያጋጭ ተራ የምንለው አጀንዳ ግልጽ ይሆንላቸዋል።

አሁን ተስተካክሎ ሊሆን ይችላል፤ በአዲሱ ፍኖተ ካርታ። ቀድሞ የትምህርት ስርዓቱ ይህንን በመመለስ ይቀረው ነበር። በብዛት ብዝኀነትን ክፍል ውስጥ የሚማሩበት ክፍለ ጊዜ ወይም የትምህርት ዓይነት ሊኖር ይገባል። የምህንድስና ተማሪ ትኩረቱ ሙያው ላይ ነው፤ የሕግም ከሆነ እንደዛው። ግን ኮርሶች መኖር አለባቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ብዝኀነት ያለን ሰዎች ስለሆንን።

አንድ ተማሪ ብዝኀነትን በተመለከተ የወሰደው ኮርስ አለ ወይ ሲባል፤ ከሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ውጪ የለም፤ እሱም ቁንጽል በሆነ መልኩ ነው። አሁን ላይ የተጨመሩ የትምህርት ዓይነቶች አሉ። በጣም ብዙ ጊዜ የእኛ ተማሪዎች የሚተቹት ሳያገናዝቡ የማንንም አጀንዳ ያራግባሉ ተብለው ነው። ለዚህ ኀላፊነት ሊወስድ የሚገባው የትምህርት ስርዓቱ ነው። በጥልቀት የማሰብና የማገናዘብ (Critical Thinking) ዓይነት የትምህርት ዓይነቶች የሚያመጡት ነገር አለ።

ቀጥሎ መምህራን፤ መምህራን በራሳቸው ለዩኒቨርሲቲ ብዝኀነት ትኩረት መስጠት አለባቸው። አስተማሪ በክፍል ውስጥ ከእያንዳንዱ ተማሪ መልስ የሚቀበልበት ፊት/ገጽታው በራሱ ለእያንዳንዱ ተማሪ የሚሰጠው ትርጉም አለ። መምህራን እንዲህ ያለ ሥልጠና ቢሰጣቸው፤ ክፍል ውስጥ ‹‹የኔ ብሔር ስላልሆነ በመጥፎ ያየኛል፣ የእኔ ሐይማኖት ስላልሆነ…›› የሚለውን ሐሜት ለማስቀረት ያስችላል።

ይህ ከሆነልን፤ አንድ ተማሪ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ቢመጣ የራሱ መብት እንደሆነ ማሳወቅ። ግን እነዛ ኮርሶች የሚነግሩት ነገር አለ፤ የሚሰጠውና የሚያዳብራቸው ነገሮችም አሉ። ከዛ ተነስተን በብስለት ሊያዩና እንዲህ ያለ ግጭት ውስጥ ላይገቡ ይችላሉ። ግጭትን በጣም መቀነስ ይቻላል። የመጀመሪያ ዘዴ ሊሆን የሚገባው ይህ ነው፤ መከላከል። የምትከላከይው ብዝኀነትን በማበረታታትና ለተማሪዎች በደንብ በማስተማር ነው። በተጨማሪም የባህል ፌስቲቫል እንዲኖር፤ የእምነት ፌስቲቫል ባላደላ መልኩ እንዲከወን ማድረግ። እኩልነት የሚሰማው ወይ በጥሩ መልኩ የተስተናገደ ተማሪ፤ ሌላ አጀንዳ ቢኖረው ራሱ ግጭት ውስጥ አይገባም።
ይህን ሁሉ አልፎ ከመጣ ግን በጣም ሰላማዊ መንገድ ያስፈልጋል። እዚህ ጋር የዩኒቨርሲቲ አመራሮችን ብቃት ይጠይቃል። እንዳለመታደል ሆኖ በጣም በስህተት፤ አሁን ያሉ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች በአብዛኛው ከአካባቢያቸው ናቸው። እያንዳንዱ ቦታ እየገባ ያለው የአካባቢው ሰው ነው፤ ነገር ግን አመራሩም ብዝኀነት ሊኖረው ይገባል።

ከዛ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲፈጠር የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በብስለት መንቀሳቀስ አባቸው። አይብስማ! ከተማሪ ሕይወት ማጣትና መጎዳት፣ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የትምህርት ቁሳቁስ መውደም የሚብስ ስላልሆነ በእቅድ ደረጃ ተቀምጦ መፍታት ያስፈልጋል።

የውጪ ኃይል ማስገባት የመጨረሻው ደረጃ ነው መሆን ያለበት፤ በጣም የመጨረሻው። እነዚህ ነገሮችና የዩኒቨርሲቲ መሪዎች በራሳቸው የሚያደርጓቸው የአመራር ክህሎት ሲታከልበት፤ ተማሪዎች ወደ ግጭት አይገቡም። ከሆነ ግን በአግባብ ቁጭ አድርጎ በሰከነ መልኩ መወያየት። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቅር የሚላቸው ተንቀናል ዓይነት ስሜት ነው። አንድ ጉዳይ ሲያነሱ በፍጥነት ሰብስቦ ማናገር ስለሌለ ነገሩን ያባብሰዋል።

ስለዚህ በየደረጃው ያሉ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ወቅታዊና አግባብነት ያለው መልስ መስጠት አለባቸው። የመጀመሪያው ብዬ የማስበው ተማሪዎችን ሰብስቦ ማወያየት ነው። ተማሪዎችን ሰብስቦ ማናገር ካለ ችግር ሊፈታ ይችላል፤ ሊሆንም የሚገባው ይህ ነው። በውጪ የታጠቀ ኃይል ሊገባ የሚችለው በጣም ከአቅምና ቁጥጥር በላይ፤ እሱም በውይይትና ከገቡም በኋላ በትንሽ ጣልቃ ገብነት ነው።

መኖራቸው በራሱ [የታጠቀ ኃይል] ኹሉት ተጽእኖ አለው፤ የውጪ ኃይል ሲያዩ የሚብስበት ሁኔታ አለ፤ በአንጻሩ መኖራቸው ደግሞ ሊያረጋጋ ይችላል። ግን በጣም ከአቅም በላይ ሲሆን፤ ትእግስት ያለው ጣልቃ ገብነት ነው መሆን ያለበት። ግን በአብዛኛው ነገሮቹ ሳይከሰቱ ለመከላከል የዩኒቨርሲቲ አመራርና ማኅበረሰብ በጣም ወሳኝ ነው።

ስለ ብዝኀነት አንስተናል፤ ብዙ ሴት ተማሪዎች በሁክት ውስጥ ተሳታፊ አይደሉም። ነገር ግን የጥቃት ሰለባ ሆነው እናያለን። የተለየ ጥበቃ አያስፈልጋቸውም?
በአብዛኛው ሴቶች በአመጽ ላይ የማይሳተፉት ከተፈጥሮ ጸባያቸው አንጻር ነው። ወንዶች ወደ ብጥብጥ ይሔዳሉ፤ ሴቶች ወደኋላ ቀረት ይላሉ። ስለሴት ተማሪዎች ብቻ አነሳን እንጂ፤ የትኛውም ቦታ አመጽ ቢነሳ አመጽ ቀስቃሽ ተጎድቶ አያውቅም፤ ንጹሕ ሰው ነው ተጎጂ።

ስለ ግጭት ስናወራ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ተሳትፎ ላይ፣ ሌሎችም ስፍራዎች ላይ የሴት ተማሪዎች ጋር ያለ የተዘነጋ ክፍተት አለ፤ ይህ የማይካድ ሐቅ ነው። በታቀደ መልኩ እየተሠራበት ነው ወይ፤ እየተሠራ ነው። ስርዓተ ፆታ ቢሮ መኖሩ አንዱ ነገር ነው። ሌላው ለምሳሌ ሴት ተማሪዎችን አወዳድሮ መሸለም እንደ አጠቃላይ አለ። ለአዳዲስ ገቢዎች ምሳሌ እንዲሆኑ። ከዛም አልፎ ለማበረታታት መሸለም አለ።

በቂ ነው ወይ ምንም የሚባል አይደለም፤ ግን ጅምሩ ደስ ይላል ነው። የተለየ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ወይ አጠያያቂም አጨቃጫቂም አይደለም። ይሄ ሲባል ግን በእንክብካቤ በመያዝ ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳ ተሸካሚ ሴቶችን አናፈራም ማለት አይደለም።

ይህን ጥያቄ ያነሳሁት በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ሲነሳ ሴት የፖሊስ አባላትን አብሮ መላክ አልተለመደም፤ ፍተሻ ሊያስፈልግ ይችላል። እንዲሁም ጾታዊ ጥቃትም ይከሰታል፤ ሴቶች ላይ። ከዚህ አንጻር እንዲታይ ነው?
ከብዙ ነገር አንጻር አግባብነት ያለው ነው። ለምሳሌ ሴት ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ሴት ፖሊሶች አለመግባታቸው ትልቅ ክፍተት ነው። እርስ በእርስ ነው መረዳዳት የሚችሉት። እንደውም ወንድ ፖሊሶች ሴቶች ዶርሚተሪ መግባታቸው አሳፋሪና አግባብ ያልሆነ ነው። የዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንኳ ሴቶች ዶርሚተሪ መግባት ኖሮባቸው ሲገቡ በከባድ ጥንቃቄ ነው።

ከዛም ውጪ እንደተባለው በቀላል ተጎጂ ስለሚሆኑ፤ በማረጋጋት ውስጥ አለአግባብ ተጠቂ እንዳይሆኑ በተመሳሳይ ጾታ ፖሊሶች ማስተናገድ፤ ካልሆነ እነሱንም በቀላሉ ማረጋጋት ስለሚቻል፤ የተለየ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ የማያጨቃጭቅ ጉዳይ አይደለም። በአብዛኛው ተጠቂ ሲሆኑ የምናያቸው እነሱ ስለሆኑ፤ የጊቢ አመራር ልዩ አትኩሮት መስጠት አለበት፤ ይህም ያግባባል። ጅምሩ ጥሩ ሆኖ ሳለ ግን ክፍተት አለ፤ አመራሮችም በደንብ ሊያጤኑት ይገባል።

ብዙ ዓይነት ማኅበራት አሉ፤ እነርሱን እንዴት ይታያሉ፤ ግጭት እንዳያባብሱስ እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?
እንደ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትልቁ ክፍተት እንቅስቃሴው በአግባብ ያለማስኬድ ክፍተት ነው። ከማኅበራት ብትነሺ አግባብነትና ፍትኀዊነት ባለው መልኩ የተደራጀ የተማሪ ኅብረት ሲኖር፣ ብዙ የተማሪ ጥያቄ በኅብረቱ በኩል ይመለሳል፤ ለአንቺም ራስ ምታት አይሆንም። በኹለተኛ ደረጃ ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሰላም ፎረም የሚባል አደረጃጀት አለ። በእርግጥ ብዙ ሰዎች ከተጠሪነት ጀምሮ በጣም ወደ ፖለቲካውና ደኅንነቱ አስጠግተው፤ በከባድ መጠራጠር የሚያይዋቸው አሉ። የክለቡ አባላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ጥርጣሬ ይፈጥራል።

በአግባቡ መጠቀም ቢቻል ግን፣ የሰላም ፎረም የሚባለው ለምሳሌ፣ ትክክለኛ እቅድ ቢኖረው ለግጭት መፍታት ትልቅ አስተጽኦ ይኖረው ነበር። ተማሪ ችግሩን ለመምህር ከማውራት ይልቅ ለጓደኛው ቢያወራ ነው የሚቀልለው፤ አብረው ስለሚኖሩ እርስ በእርስ በቀላሉ ይግባባሉ። እዚህ ላይ አትኩሮት ሰጥቶ የተማሪ ኅብረት፣ የተለያዩ ክለቦችን አድርጎ አግባብነት ባለው ልቅ ባልሆነ መልኩ፤ ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ሚና እንዲወጡ ማድረግ ላይ ክፍተት ስላለ እንጂ፣ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸው ነበር።

ችግሮቹን በዝርዝር ብናነሳ?
የአትኩሮት ማነስ አለ፤ የተማሪ ኅብረት ሲዋቀር ብዙ ተማሪዎች የሚያነሱት የውክልና ጉዳይ አለ። በአግባቡ አልተወከልንም ይባላል፤ ሁላችንም ብሔር በሚባለው ቦይ እየፈሰስን ስለሆነ። እንዲሁም በእኩል ተወዳድረው ወይም በብሔር ውክልና ላይኖረው ይችላል፤ ትክክለኛ መስፈርት ወጥቶለት፤ በዛ መሠረት ሁሉም ተስማምቶ ሲመረጥ ብሔርና ሃይማኖት ጥያቄ አይሆንም። ፍትኀዊነት የሚነሳው መስፈርቱ ግልጽ ከሆነ ነው፤ የተማሪ ሕብረቱ የሚወክለውና የሚያንጸባርቀው ሙሉ ተማሪን ስለሆነ።

አጠራጣሪ የሆኑ አደረጃጀቶች፤ ለምሳሌ እንደ ሰላም ፎረም ዓይነት አሉ። በጣም አግባብነት ያለውና ብዙ ሚና መጫወት የሚችሉ ግን ካላቸው ሚና አንጻር አጠራጣሪ የሆኑትን ደግሞ ማጥራት። ዓላማቸውን፣ በምን ዓይነት መንገድ ይንቀሳቀሳሉ የሚለው ግልጽ ሲሆን ይስተካከላል።

የፖለቲካ ድርጅቶች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሠሩ ነበር። ከአሁን በፊት በኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት ላይ ተሠራ ከምለው ትልቅ ስህተት መከከል አንዱ እሱ ይመስኛል። አሁንም ጥቅሙን ስላልተረዳሁት ምንም ልል አልችልም። የምገምተው ጥቅም ምንድን ነው፤ ‹‹የኔን ፖለቲካ ሐሳብ ያራምዳል›› የሚል ነው። ፖለቲካው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የገባ ጊዜ ነገሮች የተበላሹ ይመስለኛል።

ጥቅምም ካላቸው፣ በተለይ መደበኛ በሆነ መንገድ ከሆነ፣ ወጣ ብለው ቢሆን ይሻላል። የግል ፖለቲካን ማራመድ መብት ይሆናል። በዚህ ደረጃ ገብተን እንሥራ የሚለው ግን ምንም አይታየኝም፤ ጥቅሙ። እውነት ለመናገር ብዙ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የፖለቲካ ደርጅት አይደለም ፖለቲካ አያውቁም። ይህን በማያውቁበት ሁኔታ ተማሪዎች ላይ ብዙ መሥራት የምንችለው ነገር እያለ ይህን ማስገባት ትልቁ ስህተት ይመስለኛል።

እነርሱ እንደውም ከዛ የጸዱ ቢሆኑ ጥሩ ነው። ማተኮር ያለብን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች፣ የአመራር ቁርጠኝነት ላይ ከተሠራ፤ ማንም ሰው አጀንዳውን ቢያቀርብ ተማሪው ያነብባል። ዩኒቨርሲቲ ከሌላ የትምህርት ተቋም የሚለየው በንባብ ተጋላጭነት መጨመር ነው። ስታነቢ የአንቺ የምትይው የተበደለ ሊመስልሽ ጥያቄ ሊኖርሽ ይችላል። እነዛን መድረክ ሲኖር ግን ስትተነፍሺ፣ ስትከራከሪ ለሞት፣ ለጥቃት አይደርስም፤ ይረግባል።

መፍትሔው የትምህርት ስርዓት ውስጥ ነው። ከውጪ የሚመጣ መፍትሔ የለም። እርግጥ ነው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የውጪው ትኩሳት መግባቱ አይቀርም። ለዛ ደግሞ የአስተዳደሩ የአመራር ብቃት የተማሪን ስሜትን አጥንቶ፣ እድሜአቸውን አይቶ፤ ከ18-23 ስለሆኑ፣ በዛ የተማሪ እድሜ ላለ አስተሳሰብ የሚመጥን ቁመና ይዞ መገኘት ነው።

እንዲህ ሲሆን ነው የሚሻለው እንጂ ፖለቲካው በደንብ መውጣት አለበት። ይህ በመዋቅር መልኩ የሆነውን ነው ያልኩት። እንጂ የትኛውም ተማሪ በራሱ መብቱ ነው፤ የራሱን ሐይማኖት ያራምዳል፤ ከተቋሙ ውጪ። የፖለቲካ አስተሳሰብም እንደዛው።

አገራዊ ምርጫ እየመጣ ነው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም ምርጫ ይካሔዳል። በዛ አጋጣሚ የሚኖሩ ክዋኔዎችን ተከትሎ ገጭቶች እንዳይፈጠሩ ከወዲሁ ምን መደረግ አለበት?
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ ይወክለኛል የሚሉትን መምረጥ አለባቸው፤ ይሄ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ነው። ከአካባቢያቸው ስለራቁ የሚፈልጉትን ፓርቲ/ቡድን አለመምረጥ የለባቸውም፤ መሳተፍ አለባቸው። ኹለተኛ በተሳትፎ ደረጃ ቢነሳ፤ ቁጥሩ ቀልድ አይደለም። ከ45 በላይ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ከመቶ እና ኹለት መቶ ሺሕ በላይ ተማሪዎች የሚይዙ ናቸው። ይህ ትልቅ የሆነ ዴሞክራሲያዊ መብት ያለው ዜጋ ስለሆነ፣ መምረጥ አለባቸው፤ አያጨቃጭቅም።

ከዛ በኋላ ግን ሌላ ነገር ውስጥ እንዳይገባ በምን ዓይነት መልኩ መቆጣጠር አለባቸው የሚለውን፤ ከዚህ በፊት ያለውን በጨረፍታ ነው የማውቀውና ብዙ ባልል እመርጣለሁ። መሆን አለባቸው የምለው ግን እያንዳንዱ ሒደት ከምንም ጋር እንዳይያያዝ ማድረግ ነው። ሲጀምር አስቀድሞ እንዳልነው የትምህርት ጊዜ አለ። ግን ኖረም አልኖረ፤ የፈተና ጊዜም ቢሆን ፖለቲካው ትኩረት ሳቢ ሆኗል።

እንዴት እንደሚያደርጉት ባላውቅም በጥንቃቄ፤ ምርጫ ቦርድና የዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴሩም አለ፤ በጋራ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር። ፓርቲዎች ራሳቸውን ቢያስተዋውቁም ለተማሪዎች ግብዓት ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ የሚገባውን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት፣ እቅድ ተይዞለትና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማሪዎችን ጊዜ በማይሻማ መልኩ በደንብ ከታቀደ በደንብ ሊሠራ ይችላል። ካልመረጡ መብታቸውን መጣስ ብቻ ሳይሆን የባሰ ተቋማቱን የጦር ሜዳ ማድረግ ነው። እናም የሚጠይቀው እቅድ ነው፤ ሁሉም በሚገባ ማሰብ ያለባቸው ነው። ይህም የተማሪዎችን ጊዜ በአግባብ ከመጠቀም ጋር የሚሔድ ሊሆን ያስፈልጋል። በዚህ መሠረት ግጭት ሳይመጣ መጠናቀቅ አለበት ብዬ አስባለሁ።

በመጨረሻ በተደጋጋሚ እንደሚባለው አሁን ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጣም መስከን የሚጠበቅበት ጊዜ ነው። ያመኑበትን አጀንዳ አለማንሳት አይደለም፤ ይሄ አግባብነት ያለው ነገር አለ። ነገር ግን እየተሔደበት ያለውን መንገድ ጥቅምና ጉዳቱን መመዘን አስፈላጊ ነው፤ በእነርሱ። ቀድሞ እንዳነሳሁት አሁን እየተሔደባቸው ያሉ መንገዶች ምን እየሰጡ ነው፤ የተማሪ ሞትን፣ ተማሪ ጊቢ ለቅቆ መውጣትን፣ እርስ በእርስ መጠላላትን፣ ትምህርት ማቋረጥን ነው። ጥቅሙ ምንድን ነው?
ይሄ ካልሆነ 21 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪነት እንደሚጠይቀው፤ አግባብነት ባለው መልኩ ጥያቄ ማንሳት፣ በውይይት ማመንን፣ የራስን መብት አስከብሮ አብሮ መኖርን ከምንም በላይ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። ‹‹ግድ ሆኖብኝ እንጂ ከአንተ ጋር መማር አልፈልግም›› የሚሉ ነገሮች የትም አያደርሱንም። ነገ ከነገ ወዲያም ቆም ብለው ሲያስቡበት፤ የራሳቸው ያልነበረ ነገር ከሆነ ደግሞ፤ በጣም ይቆጫቸዋል። ምክንያቱም እውነት ለመናገር እየሔድንበት ያለው መንገድ፣ ተማሪዎች እየሔዱበት ያለው መንገድ አገርን ማፍረስ ስለሚያደርስ።

ቆም ብሎ አስቦ፣ በመረጋጋት፣ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን አንስቶ፣ መብትን አስከብሮ ከሌላው ጋር አብሮ መኖር ጎን ለጎን ማስኬድ የተሻለ ነው። የዩኒቨርሲቲ አመራሮችም ግጭት ሲከሰት እሳት ማጥፋት ሳይሆን፣ ያለፈውን ልምድ አይቶ፣ በምን ዓይነት መልክ ተማሪዎች የሚወያዩበት፣ ሐሳብ የሚገልጹበት መድረክ ይፈጠር የሚለውን አስበውበት አቅደው ሠርተውበት፤ በተማሪዎች መካከል መቻቻል ማምጣት ላይ ማተኮር አለባቸው፤ ይህ የሚዋጣ ይመስለኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here