አስቻለው ፈጠነ (አርዲ)፡ በኮራ ሽልማቶች የታጨውና የመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅ የሆነለት ባለሞያ ከአዲስ ማለዳ ጋር

0
1306

50 አካባቢ የሚሆኑ ከሳሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራትን የሙዚቃ ስራዎች በየዓመቱ አወዳድሮ በሚሸልመው ኮራ አዋርድስ በባህል ሙዚቃ ዘርፍ ጥር 3 ቀን 2016 ‘አስችለ’ የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሙ ለአድማጮች ያደረሰው አስቻለው ፈጠነ እጩ ሆኗል። አስቻለው በኮራ ሽልማቶች መታጨቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ ‘አስቻለ’ አልበም ለውጭ እስታንዳርድም ጭምር ታስቦ የተሰራ መሆኑን ነግሮናል። 

የተለያዩ አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች ከዘመናዊ መሳሪያዎች ጋር ያጣመረው የአስቻለው ፈጠነ አልበም አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ጉምዝኛ፣ አረብኛ እና ሌሎችም ቋንቋዎች ተሰባጥረውበታል። “ሙዚቃ በብዙ ሕግ እንዲታጠር አልፈልግም” በማለት አዲስ ድምጽ ለመፍጠር ስለመሞከሩም ይናገራል።  አስቻለው ፈጠነ (አርዲ) በባህል ሙዚቃ ዘርፍ ከ40 እጩዎት ተርታ ተደርጎ በአፍሪካው ኮራ አዋርድ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተወዳደረ ይገኛል። 

አዲስ ማለዳ፡ ከአልበምህ በፊት ከሰው ጋር የተዋወቅክባቸው ስራዎችህ ምን ይመሳላሉ?

አስቻለው ፈጠነ፡ ከአልበሜ በፊት 5 ስራዎች ሰርቻለው እናትዋ ጎንደርን ጨምሮ ያለፉት ስራዎቼ እንደታሰበው አድማጭ ባያገኙም እናትዋ ጎንደር ግን በይበልጥ ከሰው ጋር አስተዋውቆኛል። አድማጭ ጋር የበነረው ምላሽ ቆንጆ እና የሚያበረታታ ነበር።

አዲስ ማለዳ፡ ‘አስቻለ’ አልበም እንዴት ተሰራ? ሂደቱን በአጭሩ አጫውተን

አስቻለው ፈጠነ፡ አልበሙ 2 ዓመት ከ8 ወራት የፈጀ ስራ ነው፤ በራሳችን [ቡርቧክስ] ስቱዲዮ ስለተሰራ እና በየቀኑ ሲሰራ ስለነበር እንጂ ከዚህ በላይ ጊዜ ሊፈጅ ይችል ነበር። ቡርቧክስ አልበሜ የተሰራበት ስቱዲዮአችን ስያሜ ነው፤ በደቡብ ጎንደር አካባቢ ያለ ብዙ ታዋቂ አዝማሪዎች የወጡበት ቦታ ነው፤ ከዛ በመነሳት የሰራናቸው ሙዚቃዎች በአብዛኛው የባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያን የያዘ ስለሆነ ቡርቧክስ ተብሏል።

አዲስ ማለዳ፡ አሁን በአፍሪካ ደረጃ በባህላዊ ሙዚቃ ታጭተሃል፤ አልበሙ ሲሰራ በውጭ አገራት መለኪያዎች ታስቦ ነበር?

አስቻለው ፈጠነ፡ ደረጃውን የጠበቀ እና ኢትዮጵያን ሊያስተዋውቅ የሚችል ስራ ለመስራት አስበን ነው አልበሙን የሰራነው፤ እድሉ ከተገኘም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ጭምር።

አዲስ ማለዳ፡ በአፍሪካው ኮራ አዋርድ የታጨህበት ሄደት እንዴት ነበር?

አስቻለው ፈጠነ፡ በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ብዬ ያደረኩት የተለየ እንቅስቃሴ የለም፤ ከኢትዮጵያ ብዙ የተመረጡ ሙዚቃዎች ነበሩ ከነሱ መሀል ‘እናትዋ ጎንደር’ አንዱ ነበር፤ የኔ ስራ እንደተመረጠ ከተነገረኝ በኋላ ድምጽ መሰብሰቡ ሂደት ተጀመረ ማለት ነው። እጩ የሆነውም በባህል ሙዚቃ ዘርፍ ነው።

አዲስ ማለዳ፡ የመጣህበት የሙዚቃ ስልት ለየት ያለ ነው፤ ከዚህ በኋላ በዚሁ የመቀጠል ሀሳብ አለህ ወይስ የተለየ ነገር እንጠብቅ? 

አስቻለው ፈጠነ፡ የሙዚቃ መንገድ ብዙ ነው። እኔም የእራሴ የተለየ ነገር አለኝ ነገር ግን በዚህ ብቻ መወሰን አልፈልግም። እንደሁኔታው የሚቀየር ነገር ሊኖር ይችላል፤ የባህል ሙዚቃ መሳሪያውን የማካተቱ ነገር እንዳለ ሆኖ ጥሩ ስራዎችን ለመስራት ሀሳብ አለኝ። 

አዲስ ማለዳ፡ ቀጣይ እቅድህ ምንድን ነው?

አስቻለው ፈጠነ፡ ከዚህ በኋላ በሀገር ውስጥ ኮንሰርቶች እና ከሀገር ውጭ ደግሞ ቱር ይኖረናል። ጊዜው ሲደርስ ቀን እና ቦታውን እናሳውቃለን።

አዲስ ማለዳ፡ በሙዚቃ ስራ ሂደትህ ያጋጠሙህ ተግዳሮቶችስ? 

አስቻለው ፈጠነ፡ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፌያለሁ፤ ከክፍለ ሀገር መጥቶ ከተማ ውስጥ መኖር በራሱ የሚፈትን ሆኖ ሳለ ዘፋኝ መሆን ተጨማሪ ፈተና ነው። ግን የተለፋበት ነገር ሰው ጋር ደርሶ ጥሩ ምላሽ ሲኖረው የነበረውን ችግር ያስረሳል፤ ከዚህ ባለፈ አዲስ ነገር ለሰው ማስተዋወቅ ትልቅ ነገር እና ትግስት የሚጠይቁ ነገሮች ናቸው። 

ውልደት እና እድገቱ ቻግኒ የሆነው አስቻለው ክራር መጫወት የጀመረው ከልጅነቱ ነበር። የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስብስብ ያለበት ቻግኒ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ናት ይላል አስቻለው።

አስቻለው ፈጠነ የትውልድ ሥፍራው እና በተለያዩ ክልሎች የመኖር እድሎች መኖሩ በአልበሙ ላይ ያካተታቸውን ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ጉምዝኛ፣ አረብኛ፣ ግዕዝ እና ሌሎችን ቋንቋዎች ለመጠቀሙ እንዲሁም እና ባህሎቹን በቅርበት ማወቁ ለ’አስቻለ’ አልበም ጥሩ ግብዓት እንደሆነው ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። 

የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ‘አስቻለ’ ሙዚቃ ገና በልጅነት አፍላ እድሜው በያዘው ፍቅር ያሳለፈውን ጉዳት፣ አፍቅሮ ማጣቱንና ብቻውን መሆንን የመረጠበትን ጊዜ የተጫወተበት ሲሆን

 “ውሃ አጣጭ ብሎ ተጋምዶ፣ ጎጆውም ጎጆ አልሆነ
ቀለሙም ቀለም አልሆነ፣ አስቻለው ክራሩን ይዞ መነነ” ሲል ገልጾታል።

አስቻለው በዚህ አላበቃም አድዋ ወርዶ እምዬ ሚኒሊክ ብሎ እንዳዲስ ወኔ ቀስቅሷል፤ በእምቅ ግጥሞቹ ታሪክም አውስቷል፤ ወይዘሮ ተሰሩ እንደምን አደሩ ሲል ቅኔ ዘርፏል፤ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ አስቻለው “ወይዘሮ ተሰሩን እኔ ጽፊያለው አድማጭ ይተርጉመው” ሲል ተናግሯል።

የብዙ አድማጮችን ቀልብ የሳበው አስቻለው በእናትዋ ጎንደር ቅምሻ ልባቸውን ሰርቆ በአልበሙ ደግሞ ብዙዎች በትዝታ ከቀያቸው መልሷል፤ በሙዚቃው መማረካቸውን በተመስጦ ሰምተው በደስታ እንባ ብዙዎች ማድነቃቸው የማህበራዊ ትስስር ግጾች ይመሰክራሉ። በርካቶች አዲስ እና ጥሩ ስራን ስላቀረበላቸው በተለያዩ ማህበራዊ ገጾቻቸው አስቻለውን አመስግነዋል፣ አድንቀዋል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here