ከአዋሽ ቁልቢ የሚወሰደው መንገድ ሊታደስ ነው

0
747

የኢትዮጲያ መንገዶች ባለሥልጣን በኦሮሚያ ክልል ከአዋሽ መኢሶ እንዲሁም ከአዋሽ ቁልቢ ድሬዳዋ ያሉት ኹለት መንገዶች እንደሚታደሱ ገለፀ።
የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንደገለጸው፤ መንገዶቹ ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆኑ በመሆናቸው መልሶ የመገንባት እንዲሁም የተሻሉ መስመሮችን የመዘርጋት እቅድ አለው። ባለሥልጣኑ አክሎም ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ አገር ተጫራጮች እንዲሳተፉ እደሉ እንዳመቻቸ ገልጿል።

የዚህ መንገድ መሠራት በዋነኛነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን የሚያሳልጥ ከመሆኑም በላይ በመስመሩ ላይ የሚደርሱትን አደጋዎች ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ እንደሚገመት የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልፀዋል። የፕሮጀክት ግንባታ በመጪው ሦስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ እና የግንባታው እንቅስቃሴም ጨረታው እንደተጠናቀቀ እንደሚጀመር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ይህ መንገድ መሠራቱ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመፍጠር እንደሚረዳ፣ በተለይም በጅቡቲ መስመር ከፍተኛ የደረቅ ወደብ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ላቅ ያለ ለውጥን ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ አክለው ጠቅሰዋል።

ባለሥልጣኑ በያዝነው በጀት ዓመት 91 የመንገድ ፕሮጀክቶችን በ150 ቢሊዮን ብር ለመሥራት አቅዶ መነሳቱን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በአገሪቱ ረጅም ድልድይ የሆነው የአባይ ድልድይ ሥራ እንደሚካተት ተጠቅሶ ነበር። በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ትስስርን የሚያዳብሩ ፕሮጀክቶች በዚህ በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚሰጣቸውም ባለሥልጣኑ ገልጿል።

በአንደኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ 100 ሺሕ ኪሎ ሜትር የነበረውን የአገሪቷን የመንገድ ሽፋን በኹለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ በእጥፍ በማሳደግ እና 200 ሺሕ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ከዚህ በፊት ባለሥልጣኑ መግለጹ ይታወሳል። ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የመንገድ ሽፉኑ ከ121 ሺሕ በላይ ደርሶ እንደነበርም ሪፖርት አድርጓል።

በ1982 19 ሺሕ ብቻ የነበረው የመንገድ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለመንገድ የሚወጣው ገንዘብ ለመሠረተ ልማት በዓመት ከሚወጣው ሩቡን ይሸፍናል። ከባለፈው ዓመት በፊት በነበሩት 20 ዓመታትም አገሪቷ ለመንገድ ያወጣችው ወጪ 11 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ባለሥልጣኑ ገልጾ ነበር። በኹለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት መንገዶች መካከል የሐዋሳ የክፍያ መንገድ ይገኝበታል። በዚሁ ጊዜ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚሠሩ ዘመናዊ መንገዶች እንደሚኖሩም ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here