የባለፉት ጥቂት ሳምንታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አያሌ አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፤ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ከጥቂት ወራት በፊት ያቋቋመውን የአዲስ አበባ የባላደራ ምክር ቤት ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት እንደሚቀይረው ከዋሽንግተን ዲሲ ተሰምቷል፤ የፖለቲካ ተንታኝና አክትቪስት ጃዋር መሐመድ በበኩሉ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር መወሰኑን ካስታወቀም ሳምንታት ተቆጠሩ። በመደመር እሳቤ እየተመራሁ አንድ ወጥ ውህድ አገርዓቀፍ ፓርቲ እሆናለሁ ብሎ ኢሕአዴግ ከኹለት ሳምንት በፊት በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ደረጃ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።
ኢሕአዴግ የብጽግና ፓርቲ ተብሎ እንደ አዲስ በሚመሰረትበት ሂደት ህውሓት እንደማይሳተፍ መግለፁ ብዙዎችን ያስገረመ በሆነበት ወቅት ላይ አርብ ኅዳር 19 አመሻሹ ላይ የአሜሪካ ድምጽ የኦሮሚኛ ፕሮግራም መከላከያ ሚኒስትሩና እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ለማ መገርሳ መደመር በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እሳቤ እንደማይስማሙ እና በኢሕአዴግ ውህደት ላይ ተቃውሞ እንዳላቸው አስታወቁ። ኦቦ ለማ እንደተናገሩት በውህደቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማስታወቃቸውን ገልፀው ውህደቱ መሆን ካለበት በችኮላ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።
የአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ምርጫው በተቃረበ ቁጥር የፖለቲካ ተሳታፊዎቹ መልክ፣ ቁመናና የኃይል አሰላለፍ እንዲህ በፍጥነትና ለመተንበይ በሚያስቸግር ደረጃ ተለዋዋጭ መሆኑ የአገሪቱን የፖለቲካ ጡዘት ወዴት ያደርሰው ይሆን ስትል ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች፡፡
ወደ መገባደጃው እየገሰገሰ ያለው የኅዳር ወር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ማርሽ ቀያሪ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ያለ ምንአልባትም በታሪክ ምእራፍ ታሪካዊ ከሚባሉ ወራት መካከል የሚያሰልፉት ሁነቶች የተፈፀሙበት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የገዢው ግንባር ኢሕአዴግ ለአንድ ዓመት ያህል ሲዘጋጅበት የነበረውን የውህደት ጉዞ ከውይይት እና ከጥናት በመሻገር መሥራች እና አጋር ፓርቲዎቹ ፊት ቀርቦ የይለፍ ቃል ማግኘት የጀመረው በዚሁ በኅዳር ወር ነው። በዚህ ሂደት ውስጥም የግንባሩ ፊተኛ የነበረው ህወሓት ውህደቱን በተደጋጋሚ እየነቀፈ እና የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳ ሲሆን፣ በይፋ ውህደቱን እንደማይፈፅም ባይገልፅም በውህዱ ፓርቲ ውስጥ ግን እንደማይገባ ፍንጮችን የሰጠበት ወርም ነው።
በተጨማሪም በተሟጋችነት እና በሚዲያ ሙያ ላይ የተሰማሩት ኹለት ግለሰቦች የሚመሩትን ንቅናቄዎች ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ለማሳደግ ያላቸውን እቅድ ይፋ ያደረጉትም በዚሁ በኅዳር ወር ነው። የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት ወይም ባልደራስ ተብሎ የሚታወቀውን ንቅናቄ የሚመሩት እስክንድር ነጋ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬተር፣ የፖለቲካ ተንታኝና አክትቪስት ጃዋር መሐመድ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ሐሳብ እንዳላቸው ከመግለጽም ባለፈ ስለሚያራምዷቸው አጀንዳዎችም ጭመር በምእራቡ ዓለም ላሉ ደጋፊዎቻቸው የማብራራት እና የማስተባበር ሥራዎች መጀመራቸውንም በተለያዩ የብዙኀን መገናኛ ዘዴዎች ታዝበናል።
ከዚህ ቀደም በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆዩት እና የክልል ፓርቲ ሆነው ይመዘገባሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር አገራዊ ፓርቲ ሆነው መመዝገብ እንዲሁም ከትጥቅ ትግል መውጣት በየፊናቸው እያካሔዱት ያለው የሰላም እና የሰከነ ፖለቲካ ምኅዳር ጥያቄም ሌላኛው በኅዳር ወር የተስተዋለ ክስተት ነበር።
ፌዴራላዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከተመሠረተች ወዲህም የመጀመሪያው ክልል የመሆን ሕዝበ ውሳኔ በስኬታማነት ተገባድዶ፣ ያለ ምንም ግጭት ውጤቱ ይፋ ተደርጎ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ መልስ ያገኘው አሁንም በዚሁ ኅዳር ወር ውስጥ ነው።
ለምሳሌነት እነዚህን ኩነቶች እናንሳ እንጂ ውጤታቸው ይነስም ይብዛም በርካታ ፖለቲካዊ ክሰተቶች በኅዳር 2012 መስተናገዳቸውን እንዲሁም በኢትዮጵያ የፖለቲካ አየር ላይ ሊያመጡ ስለሚችሉት ውጤት ለመመልከት ያስገድዳል።
እጥፋቱ የቱ ጋር ነው?
ቀለል ባለ መልኩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመሩ ላይ ያለው ግልፅ የሚባለው እና በፓርቲ አደረጃጀቶች ጭምር እየተንጸባረቀ የመጣው ለውጥ የአንድነቱ ጎራ እና የብሔርተኞች ጎራ የሚለው እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ኢሕአዴግም የፖለቲካ አደረጃጀቱን እና ብሔር ላይ ብቻ ያተኮረ የፖለቲካ አደረጃጃቱን ገሸሽ በማድረግ በፓርቲው ፕሮግራም አጠራር መሃል ላይ ለመቆም የወሰደው እርምጃ ለውጥ ቢሆንም፣ የመብት ተሟጋች የነበሩ ሰዎች ግን በአንድ ግለሰብ ሲገፋ የነበረውን አጀንዳ በተደረጀ መልኩ በፓርቲ ደረጃ ይዘን እንደመጣለን ማለታቸውን ያን ያህል የተለየና ትልቅ ለውጥ ነው ብለው እንደማያምኑም የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ትንተናዎችን የሚሰጡት መሐመድ አሊ መሐመድ ያስረዳሉ።
ተሟጋቾች ሌሎችን በግል ሲተቹ እንደመቆየታቸው አጀንዳቸውን ወደ ፓለቲካዊ አደረጃጀቶች ማምጣትና ኀላፊነትን መውሰድ የተለያየ መጠን ያለው ኀላፊነት ስለሆነ፣ ይህ ቀላል ነገር አይደለም ሲሉም ይሞግታሉ። የመሟገት ሥራ አንድ ግለሰብ እስካሳመነው ድረስ እንደልቡ መንቀሳቀስ የሚያስችል ቢሆንም የፖለቲካ ሥራ ውስጥ መግባት ግን የቡድን ሥራን የሚጠይቅ እንዲሁም የሌሎችን ሐሳብና ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ የጋራ አቋም ላይ መድረስ የሚፈልግ ነውም ይላሉ።
በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ግዙፍ አድርገው ሲመለከቱ የነበሩት ጃዋር መሐመድ እና እስክንድር ነጋ ልምዳቸው፣ እውቀታቸው እና በፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፉ የቆዩበት አቅም የሚፈተሽበት ነውም ብለዋል። ግለሰቦቹ በብዙ ሽኩቻ በታፈነው የብሔር ፖለቲካ፣ ልምድ ያላቸው ውስጥ ከመግባት ይልቅ አዲስ ፓርቲ መጀመር ከፈለጉ፤ የሚያጋጥሟቸውን ትግሎች እና መጠላለፎች የሚያልፉበት መንገድም የበለጠ ፈታኝ ነው።
‹‹ጀዋርም ሆነ እስክንድር የራሳቸው ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች ይዞ ከመምጣት ይልቅ በእነሱ ስር ተጠልለው ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚሞክሩ አባለትን ይዘው የሚመጡ ከሆነ የጠነከረ የፖለቲካ ድርጅት የመፍጠር ኀይላቸው ከባድ ነው የሚሆነው›› ሲሉም ያስረዳሉ።
ነገረ የብልፅግና ፓርቲ
ከ 1981 ጀምሮ በኹለት ጥምረቶች ኋላም ቆየት ብሎ አራት የብሔር ድርጅቶችን በማቀፍ ገዢ ግንባር ሆኖ ለ 28 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደረው ኢሕአዴግ ከ1994 ጀምሮ እፈፅመዋለሁ ሲለው የነበረውን ውህደት በአንድ ዓመት ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦችን በማካሔድ ጭምር ወደ ማገባደዱ ላይ ይገኛል። በተለይም ግንባሩ ይታወቅበት የነበረውን የልማታዊ መንግሥት መርህ እንዲሁም መዋቅሩን በየክልሉ ከተዋቀሩ ፓርቲዎቹ በመቀየር ውህድ ወደ መሆን የተቃረበበት እንደሆነም በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የፕራግማቲክ ካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ስርዓትን የሚያራምደው እና በዐስር ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ ብልፅግናን ያመጣል የተባለው የኢኮኖሚ ፕሮግራም፤ ልማታዊ መንግሥትን እንደሚተካም ፓርቲው የውህደት አጀንዳውን አቅርቦ ባፀደቀባቸው መድረኮች ላይ ተሳታፊ የነበሩ አባላት ይናገራሉ። ይህም የአገር ጥቅምን የሚያረጋግጥ ሆኖ በተገኘ ጊዜ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅድ ሐሳብን የያዘ ነው።
አወቃቀርን በተመለከተም አሁን ካለው የኢሕአዴግ መዋቅር ሳይፈርስ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን እና የሥልጣን እንዲሁም የተግባር ለውጥ በማድረግ የሚፈፀም እንደሆነ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ያስረዳል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አባል እንደሚሉትም፣ ከህዋሃስ ጀምሮ የነበረው የፓርቲ መዋቅር እንደሚቀጥል በመድረኮች ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ መተዳደሪያ ደንቡ ግን ‹‹የአካባቢ አካላት›› በሚል አጠቃሎ እንዳስቀመጣቸው ያስረዳሉ።
አዲስ ስታንዳርድ የተባለው የድረገጽ ሚዲያ ከታማኛ ምንጮቼ አግኝቼዋለሁ ባለው እና በበይነ መረብ ላይ በሰፊው ሲዘዋወር የቆየው የብልፅግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብም፣ 11 ቋሚ የፓርቲውን አካላት ይዘረዝራል። ከእነዚህ ውስጥም በጥቅሉ ‹‹የአካባቢ አካላት›› የተባለው አወቃቀር ውስጥ ከቀበሌ አወቃቀር እንደሚጀምር ያስረዳል።
በኢሕአዴግ የቀደመ መዋቅርም አንድ ህዋሃስ ከሦስት እስከ አምስት ሰው የሚይዝ ሲሆን ይህም በሕገ ደንብ ያልተገደበ እና ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህም ቁጥሩ ወደ ሃምሳ ከፍ ይበል የሚል ጥያቄ ተነስቶ የተለያየ ክርክር ሲደረግበት ነበር። ነገር ግን ሳይቋጭ የቆየ ጉዳይ እንደነበረ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነባር አባል ያስረዳሉ።
የመተዳደሪያ ደንቡ ከዘረዘራቸው ቋሚ አካላት ውስጥ ባይጠቀስም በተመሳሳይ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ሦስት ላይ ‹‹የፓርቲው መሠረታዊ ድርጅቶች በአባላት የሥራና የመኖሪያ ቦታ የሚደራጁ ሲሆን፣ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ይቋቋማሉ›› ይላል። ‹‹መሠረታዊ ድርጅት የሚባላው ኹለት ህዋሃሶችን የያዘ መዋቅር ሲሆን በአንድ ወረዳ ስር ያሉ ሁሉም መሠረታዊ ድርጅቶች በወረዳው መዋቅር ስር ይሆናሉ›› በማለት የፓርቲው አባል ያስረዳሉ።
ገዢው ግንባር እስከ ዛሬ ሲከተል የመጣውን የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅር ለመቀየር ማሰቡን በሐዋሳው ጉባኤ ይፋ ካደረገ በኋላ አጋር ፓርቲዎች በሚል የውሳኔ ሰጪነት ሚና ያልነበራቸውን የአፋር፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ ፓርቲዎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ፣ ነገር ግን ድምፅ መስጠት ሳይችሉ እንዲሳተፉ ወስኖ ነበር።
በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ለመዋሃድ የአፋር ብሔራዊ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የሃረሪ ብሔራዊ ሊግ፣ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም የቤንሻንጉልና ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት በተለያየ ደረጃ የውህደት አጀንዳውን አፅድቀዋል።
ከግንባሩ አውራ ፓርቲዎችም ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በተገባደደው ሳምንት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ጠርተው ውህደቱን አፅድቀዋል።
ምንም እንኳን ፓርቲው በፍጥነት የውህደት አጀንዳውን ከሚደርሱበት ተቃውሞ በተቃራሪ እየገፋ ቢሄድም በመጪው ስድስት ወራት ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ መስራች ድርጅቶቹ የብልጽግና ፓርቲን ደንብ እና ፕሮግራም ባፀደቁባቸው ጉባኤዎች ላይ መነሳቱን የፓርቲው አባላት ይናገራሉ፡፡
አዳዲሶቹ ክስተቶችና ምርጫ
ምርጫ 2012ን የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተ ዝርዝር የምርጫ እቅድ በተለምዶ ይፋ በሚደረገበት የመስከረም ወይም የጥቅምት ወር ላይ ስለምርጫው ምንም የተባለ ነገር የለም። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ከሦስት ወራት በፊት ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተየየት፣ ቦርዱ የጊዜ ሰሌዳውን የማሰናዳት ሥራው ሲጠናቀቅ፣ እያንዳንዱ ሥራ በምን ያህል ጊዜ ይጠናቀቃል የሚለው ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተናግረው ነበር።
በተጨማሪም ለቦርዱ ቃል የተገቡ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፎችን ካሰባሰቡ በኋላ እና የሎጂስቲክስ እና የኦፕሬሽን ክፍሉ በሚያቀርበው ሪፖርት መሰረት ቦርዱ የምርጫ ማካሔጃ ጊዜዎችን ተመልክቶ የደረሰባቸውን ደረጃዎች ይፋ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
አሁን ባሉት አዳዲስ ለውጦች ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት ሶሊያና ሽመልስ፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪ፣ በተለይ አዲስ የወጣው ምርጫ አዋጅ፣ እና ማስፈጸሚያዎች በቶሎ አንዳጠናቀቁ የሚደረገው ማስተጓጎል ካልቆመ በእርግጥም ጊዜውን ይገፋዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹አዲስ ሪፎረም እያልን በድሮ ሕግ መመራት አንችልም፣ ምርጫውም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚተዳደሩበትን ሕግ ማስተካከል ስላለብን እሱ ላይ እየሠራን ነው›› ብለዋል።
የሪፎርሙ እና የምርጫው ጊዜ ተቀራርቧል የሚባል ከሆነ ግን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ችግር ሳይሆን በአገር የመጣ ጉዳይ ነው ብለው እንደሚያምኑ ያስረዱት ሶሊያና፣ ለውጡ ራሱ የመጣው በዚህ ጊዜ በመሆኑ ይሄ የእኛ ጉድለት አይደለም ይላሉ።
‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምዝገባ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዳይካሔዱ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ ከሕጉ መዘግየት በተጨማሪ ራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹በተለይም የሕጉ መጽደቅ ሂደት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ያለ ማንኛውም አይነት ውይይት በማደናቀፍ፣ እንዲስተጓጎል በማድረግ፣ እንዲሁም በሕጎቹ ላይ ውይይት እንዳይደረግ በመበተን ሂደቱ ወደፊት እንዳይሔድ እያደናቀፉ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ። ‹‹ኀዳር 19 ሊደረግ የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ላይ ለ,ደረግ የነበረ ውይይት እንኳን ብናይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ምን መሆን አለበት የሚል መመሪያ ቦርዱ አዘጋጅቶ ለሁሉም ፓርቲዎች ልኮ ግብአት ለመሰብሰብ ቢጠራም ምንም ሃሳብ ሳይሰጡ ስበሰባው ተበትኗል›› ሲሉ እንቅፋቶቹን አስረድተዋል።
‹‹በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ ቦርዱ እየተዘጋጀ ነው፣ የፓርቲዎችን ምዝገባም ለማጠናከር እየሞክርን ነው፣ በቦርዱ በኩል ይሄ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ሲሉም ተናግረዋል።
የምርጫ ሕጎችን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎችን ያዘጋጁት እና በኔዘርላንድ ሄግ መሠረቱን ባደረገው የዓለማቀፍ የሕገ መንግሥት የምርምር ኢንስቲቱት (አይዲኢኤ) አርታኢ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ እየተከናወኑ ያሉ የፓርቲ እንቅስቃሴዎች ምርጫ ቦርድን ሥራ አያውኩም። አብዛኛው ችግር የፓርቲዎቹ እንጂ የቦርዱ አይደለም፣ የአካሔድ ሂደት ጥሰት አለ የሚባለውም ምርጫ ቦርድን የሚመለከተው ፓርቲዎቹ ሊመዘገቡ ሲሔዱ ነው ሲሉ አደም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ አሁን የተለያየ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ምስጢር እያደረጉ ሲሆን፣ ይህም የሚጠበቅ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። እስከ ምዝገባ ባለው ሂደት ግን ፓርቲዎች የየራሳቸውን አካሔድ ይከተላሉ። ነገር ግን እስከ ኹለት ወር ድረስ ባለው ጊዜ መመዝገብ ይችላሉ። የኢሕአዴግ ውህደትም ቢሆን እስከ ዛሬ ድረሰ ባሉ መዋቅሮች በመጠቀም የሚደረግ ስለሆነ ቴክኒካዊ የሆኑ መስፈርቶችን ካሟሉ ምዝገበው ቀላል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ምርጫ ቦርድ በተለይ የሲዳማ ምርጫን ያካሔደበት መንገድ ትልቅ ሥራ ነው የሚሉት አደም፣ አንዳንድ አገራት እድሜው ለምርጫ የደረሰ የሕዝብ ቁጥራቸው ነው፣ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ማሳካቱ የሚደገፍ ነው ሲሉ አደም ያብራራሉ። ነገር ግን ሪፈረንደም ኹለት ምርጫ ብቻ ያለበት እና የሲዳማ ሪፈንደም ባሕሪያት ከምርጫ የተለዩ ናቸው፣ ይንን ወደ አገር ደረጃ ማሳደግ ግን ሰፊ ሥራ ይጠይቃል ባይ ናቸው።
አደም አክለውም ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎችም ከመራጮችም ጋር ሥራውን ማካሔዱ ጫናውን ያከብድበታል፣ እስከ ሃምሳ ሚሊዮን መራጮችን መዝግቦ፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ ማሠልጠን ብቻውን ከባድ ያደርገዋል። ፓርቲዎች የሚያስፈልጋቸውን ሁኔታ አሟልተው ከመጡ ያን ያህል ጊዜ አይወስደም ብለዋል።
‹‹የብልፅግና ፓርቲ ለዘመናት አጠናክሮ የሠራው የፓርቲ መዋቅር ስላለው፣ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን አስተባብሮ ለማሟላት እና ለመመዝገብ ሰፊ ጊዜ ይወሰድበታል ብዬ አላምንም። ባልደራስም በአዲስ አበባ ብቻ ስለሆነ እንቅስቃሴው ለማስተባበር አይርቅም፤ በምክር ቤቱም ቀደም ተብሎ የተዘረጋው መዋቅር ይጠቅመዋል። ጃዋርም ቢሆን ምንም እንኳን ይፋዊ ባይሆንም የተቀናጀ መዋቅር ያለው የድጋፍ ሰንሰለት እንዳለው ስለሚታወቅ ሦስቱም ፈጥነው ሥራቸውን ከሠሩ በቦርዱ ሥራም ላይ ሆነ በምርጫ ሂደቱ ላይ ያን ያህል ጫና አያመጣም›› ሲሉ አደም በሰፊው ይሞግታሉ።
ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 47 ሺሕ እንደጨመረ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። አገራዊ ምርጫ ከ250 ሺሕ እስከ ሶስት መቶ ሺህ የሚደርሱ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ማሰማራት ሊያስፈልገው እንደሚችልም የቦርዱ ጥናት አመልክቷል።
ኹለቱ ነፃ አውጪ ግንባሮች
ከኹለት ዐስርት ዓመታት በላይ በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆዩት እና በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ በመጠው ለውጥ በሰላማዊ መልኩ ለመታገል ወደ አገር ከገቡት የፖለቲካ ኀይሎች ውስጥ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር እና ኦነግ አገራዊ ፓርቲ ሆነው ከመመሥረት ባሻገር የሰላም እና የመረጋጋት ጥሪዎችን ሲያቀርቡም ይደመጣሉ።
የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥቱን በቂ የሰላም ማስከበር እንዲሁም የእርቅ ሂደት አላካሔደም፤ ይህም ሊሻሻል ይገባል›› በሚል ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ተሰምቷል። በሶማሌ እና በአፋር መካከል ተከስተው ስለነበሩ ግጭቶች በወጡ መግለጫዎች፣ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሚዲያዎችም ግጭትን ከማባበስ ተቆጠቡ ሲል ተደምጧል።
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ከወታደራዊ ክንፉ ተለይቶ እና አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ ከመመዝገቡ ባሻገር፣ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይም የኢትዮጵያን መሰረት የሚያናጉ እና ፀረ ዴሞክረሲያዊ የሆኑ የፖለቲካ ባህሎች እየተለመዱ መጥተዋል ሲል፤ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየታየ የመጣውን የተማሪዎች እርስ በእርስ የመጠቃቃት ድርጊትም በጥልቅ ተችቷል። የእምነት ተቋማት ላይም እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ያወገዘው ግንባሩ፣ እንዲህ ዓይነት የሞራል ውድቀት ውስጥ መግባታችን ያሳዝናልም ሲል መግለጫው ላይ አካትቷል።
ብሔር ተኮር ፓርቲ የሆኑት ኹለቱ ድርጅቶች እያሳዩት ያለው የአቋም መሻሻል ሌሎች ከተመሳሳይ ባህር ለሚያጠምዱ ፖርቲዎች ውድድሩን የሚያከር ነው ሲሉ አደም ይናገራሉ። እነዚህ ፓርቲዎች እስከዛሬ ከሚታወቁበት አቋም ለየት ባለ መልኩ የመለዘብ እና የመስከን አዝማሚያዎች ይታይባቸዋል።
‹‹ኢትዮጵያዊነትን የሚቀበል እና አብረን እንሥራ የሚሉ የለዘቡ አቋሞች ይታያሉ። ይህም ለምሳሌ በኦሮሚያ የጃዋርን ወደ ምርጫ መምጣት ብዙ ሰው ከአዲስ የብልፅግና ፓርቲ ጋር ቢያያይዘውም በእኔ እይታ ግን ኦነግን፣ ኦፌኮን እና ሌሎች በብሔር ፖለቲካው ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸውን ፓርቲዎች የሚያሰጋ ይመስለኛል›› ሲሉ አደም ይናገራሉ።
አዲስ አበባ
በአዲስ አበባ ላይ ኢዜማ፣ ባላደራው ምክር ቤት እንዲሁም ከብሔርተኞች ጎራም አብን እናሸንፍበታለን ብለው የሚያስቡት ነው የሚሉት መሐመድ አሊ ሰፊ፣ መዋቅር ያለው ኢሕአዴግ በተለይ በታከለ ዑማ (የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ) በኩል ያለው ተቀባይነትም የሚናቅ አይደለም። ይህም ከተማዋን በመጪው ምርጫ ዋና የትግል አውድማ የመሆን እድሏን ሰፊ ያደርገዋል ይላሉ።
ነገር ግን ከአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ ብዙ ያልጠሩ ነገሮች አሉ። አብዛኛው የከተማው መራጭም ፓርቲዎቹ የያዙትን አጀንዳ አይቶ እና መዝኖ የሚመርጥ ይሆናል። ነገር ግን ገዢው ፓርቲም ሆነ ኢዜማ ምንም ዓይነት የጠራ አጀንዳ እስከ አሁን የላቸውም፣ መሠረታዊ አጀንዳ መሆን የሚችለው የነዋሪውን ችግሮች፣ ፍላጎቶችና ስሜቶች ተረድቶ መልስ ያለው አጀንዳ ይዞ መምጣት የሚችለው ፓርቲ ማሸነፉ የማይቀር ነው።
‹‹ይቅር ገዢው ፓርቲ ኢዜማም ራሱ ለተጀመረው ለውጥ እንቅፋት መሆን አልፈልግም በሚል እንደ ሰጎን ራሱን የደበቀበት ነው፣ በዚህ ረገድም እንደ አብን ያሉት አቋማቸውን በመግለፃቸው ዋልታ ረገጥ ነው ቢባልም ቢያንስ ግን ሐሳባቸው ታውቋል›› ሲሉ መሐመድ ይናገራሉ።
አደም በበኩላቸው አዲስ አበባ ላይ ያለው የመራጭ ቅርምት ምን አልባት ውጤቱን ከታሰበው ውጪ ሊያደርገው ይችላል ይላሉ። የአንድነት ኀይሎች የሚባሉት አዲስ አበባ ላይ ያላቸው ደጋፊ ተመሳሳይ በመሆኑ፣ ለሦስትና ለአራት ሲከፋፈሉት ከፍተኛ ድምጹን የብሔር ኀይሎች ለማግኘት ያልተገመተ እድል መስጠቱ አይቀርም።
‹‹ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቀኑትን ደጋፊዎች በከፋፈሉ ቁጥር ለብሔርተኞች ከፍተኛ እድል የሚሰጥ ነው፣ ብሔረተኞችም ደጋፊዎችን እርስ በእርሳቸው በተከፋፈሉ ቁጥር ለአንድነት ኀይሎች እድል እየሰጡ ስለሚሔዱ ይህ በጋራ ለመሥራት ሊያስገድዳቸው ይችላል። በአጠቃላይ ባልደራስ፣ ኢዜማ እና ብልፀግና አንድ ላይ ካልሠሩ አዲስ አበባ ላይ የመሸነፍ እድል ሊኖራቸው ይችላል›› እንደ አደም እይታ።
የባልደራሱ ምክር ቤት አባል የሆኑት ስንታየሁ ቸኮል ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የባደራሱ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት የመሸጋገር ጥያቄ ለስድስት ወራት ሲነሳ የነበረ እና ይህም በጥናት ጭምር የታገዘ ነበር ይላሉ።
‹‹ሰብሳቢያችን ወደ ውጪ አገር ሲሔዱ በእዛ ያለውም ማኅበረሰብ ጥያቄውን ያንሳ አንጂ የአዲስ አበባ ደጋፊዎቻችን ቢሮ ድረስ በመምጣት የአዲስ አበባን ነዋሪ መብት ለማስከበር ፓርቲ መሥርተን እንድንንቀሳቀስ ጥያቄዎች ነበሩ›› ብለዋል።
እንደ ስንታየሁ ገለፃ የባልደራሱ ምክር ቤት ወደ ፖለቲካው የመግባት ምንም ዓይነት ፍላጎት ያልነበረው ቢሆንም፣ አሁን በያዘው መንገድ ግን ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ አቅጣጫውን ሊቀይር እንደሚችል ተናግረዋል። አክለውም ውሳኔውን የሚያጸድቀው ምክር ቤቱ መሆኑን እና ኹለት አማራጮች መኖራቸውንም ጠቁሟል። ምክር ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ፓርቲነት መቀየር እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎች ወጥተው ወደ ፖለቲካው ገብተው የባልደራስ እንቅስቃሴ ግን ሊቀጥል እንደሚችልም ተናግረዋል።
የህወሓት አቋም ወዴት ያመዝናል?
ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ እና የሕግ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አደም እንደሚሉት፣ ህወሓት ሦሰት አማራጮች አሉት። አንዱን መምረጡም የማይቀር ነው ሲሉ ይናገራሉ። የመጀመሪያ ምርጫው ብልፅግና ፓርቲን አልቀላቀልም ብሎ ብቻውን ፓርቲ ሆኖ መንቀሳቀስ እንደሆነ ያስረዳሉ። ምን አልባትም ህወሓት እስከምርጫው ድረስ በራሱ ቆይቶ ከምርጫው በኋላ ግን ከማንኛውም ድርጅት ጋር ተደራድሮ ግንባር የመመሥረት እርምጃ ሊወስድ ይችላል። እንደ አደም ገለጻ፣ ዴሞክራሲ በጠነከረባቸው አገራት ግንባር የሚፈጠረው ከምርጫ በኋላ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ግንበሩ ቀድሞ ተፈጥሮ የሚጠብቀው ምርጫውን ኢሕአዴግ እንደሚያሸንፍ ስለሚያውቅ ነው።
‹‹ኹለተኛው እና ዝቅተኛ እድል ያለው አማራጭ ከብልፅግና ፓርቲ የሚፈልገውን ነገር በድርድር እና በማስተማመኛ ካገኘ ምን አልባትም ውህደቱ ውስጥ የመግባት እድል ሊኖረው ይችላል›› ሲሉ አደም ይናገራሉ። ‹‹ሦስተኛው አማራጭ በተለይም በብሔርተኝነት አካሄድ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ተሰባስቦ ይልቁንም ብልጽግና ፓርቲን የሚፈታተን ግንባር ሊመሠረት ይችላል።››
ህወሓት በተለይም ለዓመታት ካለው ታሪካዊ ልዩነቶች ምክንያት ከብዙ ፓርቲዎች ጋር በቀላሉ ተስማምቶ ከምርጫ በፊት የመጣመሩ ጉዳይ ትንሽ ቢያጠራጥርም፣ ወደ ፊት ከምርጫው በኋላ ግን አጋርነት ሊፈጠር ይችላል ሲሉ አደም ያስረዳሉ።
ህወሓትን አስልተው የሚተቹት መሐመድ አሊ ግን ‹‹ፓርቲው አሁን ባለው የብልፅግና ፓርቲ መዋቅር ውስጥ የማይገባ ከሆነ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው በራሱ አምሳል ሌሎቸ ድርጅቶችን ጠፍጥፎ መሥራትና ከእነርሱ ጋር ግንባር በመፍጠር እራሱን ማዕከል በማድረግ እነዛ ፓርቲዎች በሚመሯቸው ክልሎችን የመዘወር እርምጃ ይወስዳል›› ሲሉ ይናገራሉ።
ሕገ መንግሥቱ
‹‹መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሕግን ማዉጣት የሚችል ሲሆን፣ ቋንቋን በተመለከተም እንዲሁ ሕግም ሆነ ፖሊሲ ማውጣት ይችላል። ሕገ መንግሥትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ግን ቀጥታ ሕዝቡን የሚመለከቱ እና በሕዝቡ የሚወሰኑ ናቸው››
በቋንቋ ብቻ ሳይሆን በብዙ ጉዳዮች ሕገ መንግሥቱ ላይ የሚነሱ የቆዩ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ የሚሉት በሪሁን፣ እነዚህ ጥያቄዎች ሁሉንም ሕዝብ ባሳተፈ መልኩ እንዲፈቱ መንግሥት ሁኔታዎችን ማመቻችት አለበት ባይ ናቸው። በፌዴራል የሥራ ቋንቋ ላይ እየተወሰደ እንዳለው እርምጃ፥ በክልሎች የሥራ ቋንቋዎችን የማሻሻል ተመሳሳይ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸውም ይላሉ።
‹‹አሁንም የፌዴራል ስርዓቱ እየተተገበረ ነው ማለት ይከብዳል፣ ለፌዴራል ስርዓት መተግበር ዋናው ማሳያ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ ነው። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ማሳያ የሕግ የበላይነት ነው። አሁንም ድረስ በተለያዩ ክልሎች የሰዎች መሞት፣ መፈናቅል፣ ንብረት መውድም እና አለመረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ ይታያል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ክልሎች ፈርጥመዋል ማለት አይቻልም። ስርዓት አልበኝነት ነው ጡንቻ ያወጣው›› እንደ በሪሁን አስተያየት።
ሆኖም የፖለቲካ ኀይሎች በሕገ መንግሥቱ ላይ የያዙት በጣም የተራራቀ እይታ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግን በጣም ከባድ ሊያደርገው ወይም ሊያዘገየው ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ይገልፃሉ። ለምሳሌነትም የፈዴራል የሥራ ቋንቋ ጉዳይ ሲነሳ፣ አጠቃላይ የፌዴራል ስርዓቱ መወቅር እና የመገንጠል መብት የመሳሰሉት ተያይዘው መነሳታቸው አይቀርም።
የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕገ መንግሥቱን በተከተለ መንገድ ብቻ ይካሔዳል በሚል ጥቅል ሐሳቡን ጠቅሷል። የባልደራስ እንዲሁም የጃዋር መሐመድ አቋም በሕገ መንግሥቱ ላይ በተለይም ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከገቡ በኋላ ያልተገለፀ ቢሆንም፣ ኹለት የተለያዩ ጽንፎች ላይ መቆማቸውን ግን ከዚህ ቀደም ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ቀጣዩ ምዕራፍ ምንድን ይሆን?
የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-ደንብ ለፓርቲዎቹ በቀረቡበት መድረኮች ላይ ከተነሱ ሐሳቦች መካከል አጋር የተባሉት ፓርቲዎች አሁንም በትልቁ ውህድ ውስጥ ገብተው ድምፃቸውን እንዳያጡ የሚለው ይገኝበታል። በዚህም በተለይ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ወደ ውህዱ ፓርቲ ሲቀላቀል ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። ይህም የራስን በራስ የማስተዳደር ሂደቶች መቀጠልን ጨምሮ ‹‹በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የሚኖረን ውክልና የሕዘብ ቁጥር፣ የቆዳ ስፋት፣ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን እንዲሁም የጂኦፖለቲካል እና ስትራቴጂያዊ አቀማመጣችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይገባዋል›› የሚል ነው። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጦም ውህደቱን መቀበል ጀምሯል።
በተጨማሪም ፓርቲዎቹ የሚያስተዳድሯቸው የልማት ድርጅቶች ጉዳይ እና በእነዚህ ስር ያሉ ሚዲያዎች ጉዳይ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ከምርጫ ሕጉ በመነሳት ከፓርቲ ለማስወጣት እየታሰበ እንዳለም በውይይት መድረኮቹ ተነስቷል።
‹‹እነዚህ ሂደቶች ምርጫውን የሚገፉት ከሆነ ውሳኔው የአራት ኪሎ እና የፓርላማ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ማሳተፍ አለበት፣ ምክንያቱም የምርጫ መራዘም የምርጫውን ውጤት ስለሚወስን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል›› ሲሉ አዳም ያስጠነቅቃሉ። ‹‹ከውጪ ሆነው አስተያየት የሚሰጡ አካላት አሁን ወደ ሜዳው መግባታቸው ሞራላዊ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ግዴታ ጭምር የሚጥል የራሱ የሆነ መልካም ገፅታ አለው።
አርብ አመሻሹ ላይ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የኦሮሚኛ ክፍል ከመከላከያ ሚኒስቴር እና የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበር ጋር ባካሄደው ቃለ ምልልስ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የትግል አጋር ብሎም የለውጡ ሃይል መስማቸው የሚጠራላቸው ለማ መገርሳ ለመደመር ፍልስፍና እንዲሁም ለብልፅግና ፓርቲ ያላቸውን ተቃውሞ በይፋ ያሰሙበት ነበር፡፡ የውህደት ሃሳቡ ላይ ያላቸውን ልዩነት ሲገልጹ መቆየታቸውን የተናገሩት ለማ በአስፈላጊነቱም ሆነ በወቅታዊነቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ይፋ አድርገዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲን እውን የማድረግ ጥያቄ ላይ በኦዴፓ ውስጥ ያለው ፖለቲካ ትልቁ መሰናክል መሆኑ አይቀሬ ነው የሚሉት አደም ዐቢይ ይህንን ፍጭት አሸንፈው በየፓርቲዎቹ የውህደት አጀንዳው እንዲጸድቅ ማድረጋቸው አስገራሚ ነውም ይላሉ፡፡ የኦዴፓ ተቃውሞ በርትቶባቸው ቀርቶ እንዲሁም ለዐቢይ በክልሉ ማሸነፍ ከባድ ይሆናል የሚሉት፣ በብልፅግና አወቃቀር ግን በጠቅላይ ሚኒስተርነታቸው የሚቀጥሉበት እድል ሰፊ ነው ሲሉም አደም ተናግረዋል፡፡
አደም እንደሚሉት የኅዳር ወር ክስተቶች ቀላል የማይባሉ ናቸው። በመጪው ወራቶችም የሚቀጥል ይሆናል፤ ይህ የምናየው ድርጊትም ጅማሬ ነው። ‹‹ይህ ሂደት የመጀመሪያው ነው፤ ምን አልባትም የመቀላቀል ሂደቶች ይኖራሉ፣ ምክንያቱም የአማራጮች መብዛት ሕዝቡን እንዳያደናግሩ›› ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012