የጥበቃ ሥራውን ሽፋን በማድረግ ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

0
866

አሕመድ ናጁ ሙክታር በተባለ የመኪና አስመጪ ድርጅት በጥበቃነት ይሠራ የነበረው መላኩ ሹመይ ሳሙን የአሠሪውን ቶዮታ ሪቮሉሽን ድብል ጋቢና መኪና በመስረቅ ክስ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ጥቅምት 26/2012 በዋለው ችሎት ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው የ6 ዓመት ከ6 ወር እስራት ፈርዶበታል።

በችሎቱ እንደተገለፀው፣ ተከሳሽ የሚጠብቀውን አካባቢ ሲያጠና ከቆየ በኋላ የግል ተበዳይ አሕመድ ናጁ ሙክታር ንብረት የሆነውን ታርጋ የለጠፈ እና ግምቱ 3.8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቶዮታ ሪቮሉሽን ደብል ጋቢና መኪና ለሽያጭ ቆሞ ከነበረበት ቦታ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን መኪናው የነበረበትን የሽቦ አጥር ቁልፍ በመስበር ከመኪናው ፊት ለፊት የነበሩ ሌሎች መኪናዎችን ቦታ በማስለቀቅ ሰርቋል።

አንደኛ ተከሳሽ መላኩ ሹመይ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ስሙ ሳር ቤት ኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የመኪና አስመጪ ድርጅት ጥበቃ ሲሆን፣ የመኪናውን ቁልፍ በመስረቅ ከመኪናው ፊት ለፊት የነበሩ ሌሎች መኪናዎችን ቦታ በማስለቀቅ እና ለአባሪዎቹ በመስጠት መኪናው ከጊቢ እንዲወጣ አድርጓል።

ኹለተኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ተስፋዩ ሃጎስ ለጊዜው ላልተያዙ አባሪዎች የመኪናውን ቁልፍ በመስጠት ብር 200 ሺሕ ተቀብሎ ድርጅቱን ቆልፈው ከተሰወሩ በኋላ መስከረም 6/2012 በፖሊስ ክትትል በትግራይ ክልል አላማጣ ከተማ ተይዘዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ ግለሰቡ ሆነ ብሎ ያለ አግባብ ለመበልጸግ የአሠሪውን ትእዛዝ አንቀፅ 669 በመተላለፍ በሚል የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን የሰነድ እንዲሁም የሰው ምሰክሮችን አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የሰው፣ የሰነድ እና አካባቢያዊ ማስረጃዎችን ሲሰማ የቆየው ችሎቱ፣ ተከሳሾች ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል ከ5 እስከ 25 ዓመት የሚያስቀጣ መሆኑን አብራርቶ ለድርጊቱ ይመጥናል ያለውን ቅጣት በመካከለኛ እርከን ማስተላለፉን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ እንደተናገሩት፣ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የፖሊስ ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት፣ የአካባቢ ፖሊስ ጣቢያዎች መዘጋትና በውስጣቸውም በቂ የፖሊስ ኃይል ያለመኖር እንደ ከፍተኛ ችግር እንደተነሱ ገልጸዋል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ልምድ ያላቸው እና በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ፖሊሶች ከተማው ውስጥ በሚገኙ 832 ቦታዎች መመደባቸውን ተናግረው ነበር።

በአዲስ አበባ ከሚታዩ የዝርፊያ ወንጀል ዓይነቶች መካከል ከባንክና ከሌሎች የንግድ ተቋማት ገንዘብ ይዘዉ በሚወጡ ዜጎች ላይ የሚፈፀም ቅሚያ፤ የመኪና ስርቆት፤ ውንብድና፣ በቀንና በሌሊት በመኖሪያ ቤት ወይም በድርጅቶች ዉስጥ በመግባት በጦር መሣሪያ አስገድዶ መዝረፍ ተጠቃሽ ናቸው።

ከወንጀል ዝርፊያ ስጋት ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሰኔ 12 ቀን 2011 በሰጡት መግለጫ፤ በከተማዋ ሞተር ብስክሌቶችን በመጠቀም በተደራጀ መንገድ ቅሚያ፣ ስርቆትና አልፎ አልፎ ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረው ነበር። በውጤቱም በአዲስ አበባ ከሰኔ 30 ቀን 2011 ጀምሮ ሞተር ብስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው ከቆዩ በኋላ ውሳኔው ተሻሽሎ ሕጋዊ ሒደቶችን ያሟሉ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here