ያለዝግጅት ፈተናውን መውሰድ አንችልም፤ የተቃውሞ ድምጽ እያሰባሰብን ነው- ቅሬታ አቅራቢ የህክምና ባለሙያዎች

0
1338

አዲስ ገቢ የህክምና ልዩ ዘርፍ (ስፔሻሊቲ) ተማሪ ሀኪሞች የድህረ ምረቃ መግቢያ ፈተና (GAT) ተፈተኑ ተብለናል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢ የህክምና ባለሙያዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ። 

አዲስ ማለዳ ከጤና ሚኒስቴር ይፋዊ ገጽ እንደተመለከተችው የካቲት 4 ቀን 2016 በትምህርት ሚኒስትር ጥያቄ መሠረት የ2016 የድህረ ምረቃ መግቢያ ፈተና (GAT) ፈተና “በቅርብ ቀናት” እንደሚኖር እና ተፈታኞች በቆ ዝግጅት ያድርጉ የሚል ማሳሰቢያ ተሰራጭቷል። 

ይሁን እንጂ በታህሳስ ወር አጋማሽ 2016 አገር አቀፍ የህክምና ልዩ ዘርፍ (ስፔሻሊቲ) ባለሞያዎች መመዘኛ ፈተና ተሰጥቶ ምደባ መውጣቱን አዲስ ማለዳ አውቃለች። 

በዚህም መሠረት መመዘኛውን ያሟሉ ከ1 ሺህ 600 በላይ የህክምና ባለሞያዎች ካሳለፍነው ወር ጥር 10 ቀን 2016 ጀምሮ በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ምደባ መሰጠቱን ተከትሎ ባለሞያዎቹ “ወደተመደብንበት ቦታ ሥራ ለቀን ቤተሰብ ይዘን ከሄድን በኋላ ፈተና መፈተን አለባችው” ተብሏል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

አዲስ ማለዳ በህክምና ባለሞያዎቹ ቅሬታ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴርን ለማናገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። ነገር ግን ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የህክምና ባለሞያዎች እንደተናገሩት ወደ ጤና ሚኒስትር በስልክ  ደውለው ስለሁኔታው ሲጠይቁ “ጤና ሚኒስቴር ስለጉዳዩ እውቅና እንደሌለው እና የትምህርት ሚንስቴር ውሳኔ” ስለመሆኑ ተገልጾላቸዋል። 

በመሆኑም “ቅሬታችንን በሰላማዊ ሰልፍ ለማቅረብ የተቃውሞ ድምጽ እያሰባሰብን ነው” ሲሉም የህክምና ባለሞያዎቹ ገልጸውልናል።  

“ከትምህርት ሚኒስትር የወጣ ትዕዛዝ ነው በሚል ከመግባቢያ ሰነዳችን ውጭ በሆነ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች ሀኪሞችን እንዳይጠሩ፤ የጠሩም እንዲመልሱ በመደረጉ ሥራችንን ለቀን ቤተሰብ ይዘን ከህግ አግባብ ውጭ ለእንግልት እየተዳረግን ነው” በማለት ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአንጻሩ የቅድመ ምረቃ ፈተና ስለመኖሩ እና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲል ያሳሳበው የጤና ሚኒስቴር መሆኑን ልብ ይሏል።

የህክምና ባለሞያዎቹ ቅሬታቸውን ወደ አገሪቱ የሀኪሞች ህብርት መውሰዳቸውን ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛው ጋር ባደረገችው ቆይታ የሀኪሞቹ ቅሬታ ከምን ደረሰ ስትል ጠይቃለች። 

የማህበሩ ፕሬዝዳንት “ቅሬታቸውን ከተመለከትን በኋላ ለሚመለከተው ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከጤና ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር ሙከራ አድርገናል” ያሉ ሲሆን “ስለጉዳዩ እንደሚወያዩበት እና የመጨረሻ ውሳኔያቸውን እስኪያሳውቋቸው እንዲጠብቁ” ተነጋግረናል ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢ የህክምና ባለሙያዎቹ ጉዳያቸውን አሁንም በደብዳቤ የትምህርት እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ለመጠየቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም “አገራችን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የምታደርገውን የፖሊሲ ማሻሻልና የፈተና ጥራት የምንደግፍ ቢሆንም ወቅቱንና ሁኔታዎችን ባላገናዘበ መልኩ ከማስፈጸሚያ መመሪያ ውጭ፤ የአካልና የስነ ልቦና ዝግጅት ባልተደረገበት በዚህ ወቅት ፈተናውን ለመውሰድ የማንችል መሆኑን እንዲረዱልን” ሲሉ ጥያቄያቸውን በአጽንዖት አቅርበዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here