በሁለት ዓመታት ብቻ 103 ሰዎች ከሕግ ውጪ በመንግሥት እና ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተገድለዋል- የኢሰመኮ ምርመራ

0
536

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና መደበኛ ባልሆኑ ታጣቂዎች፤ ለታጣቂ ኃይሎች አልያም ለመንግስት መረጃ ትሰጣላችሁ፣ ሎጂስቲክ ታቀርባላችሁ እና የቡድኑ አባል ናችሁ በሚሉ ምክንያቶች እንዲሁም በዘፈቀደ ጥቃቶች 103 የሚሆኑ ሰዎች በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከሕግ ውጪ ተገድለዋል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት የካቲት 15 ቀን 2016፤ በኦሮሚያ ክልል በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶችና የዓለም አቀፍ ሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ ከመስከረም 1 ቀን 2014 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ድረስ የተደረገ የተደረገ ባለ 11 ገጽ የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

በኢሰመኮ ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋ እና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች ላይ ለሁለት ዓመታት እና ሁለት ወራት ምርመራ ማድረጉን ገልጿል።

በታጣቂዎችና በመንግስት የጸጥታ አካላት ሲቪል ሰዎች ከሕግ ውጪ መገደላቸውን፣ ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ መታገታቸውን እና ዘረፋ የተፈጸመባቸው መሆኑን ከተጎጂዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ ነዋሪዎች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ማረጋገጥ መቻሉን ኮሚሽኑ አመላክቷል።

በዚህም በክልሉ “ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መድኃኒት ትልካለህ፤ ልጅህ ሸኔን ተቀላቅሏል” በሚል የገርበ ጉራቻ ነዋሪና የአገር ሽማግሌ በመከላከያ ሠራዊትና በቀድሞ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት ተይዘው ገርበ ጉራቻ ከተማ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ ለአንድ ወር ከታሰሩ በኋላ፤ ኅዳር 10 ቀን 2014 ምሽት ላይ በጥይት ተገድለው አስከሬናቸው ካምፑ አካባቢ መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል”። 

በተመሳሳይም በሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ ነዋሪ የነበሩ 14 የአዋሬ ጎልጄ ቀበሌ ነዋሪዎችን የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር በማዋል በመኪና ጭነው ጎሃጽዮን ከተማ ወደሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ከተወሰዱ በኋላ ሚያዝያ 25 ቀን 2014 መገደላቸው በኢሰመኮ ሪፖርት ተመላክቷል። 

አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ባገኘችው ሪፖርት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሰኔ 16 ቀን 2015 በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ቦራ ወረዳ፣ ጀርሜ ቦራ ቀበሌ “የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ 10 ሲቪል ሰዎችን፣ እንዲሁም ነሐሴ 26 ቀን 2015 ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ መቂ ከተማ 10 ሲቪል ሰዎችን” ገድለዋል።

የመብቶች ኮሚሽኑ በዚሁ ሪፖርት ላይ ምላሻቸውን ለማካተት ለኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፤ መስከረም 24 ቀን 2016 ደብዳቤ መላኩን የገለጸ ሲሆን “ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ” ምላሽ እንዳልተገኘ አዲስ ማለዳ ከኢሰመኮ ሪፖርት ተረድታለች። 

በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ላይ ነሐሴ 21 ቀን 2015 “በአማራ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች” በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች በሥራ፣ በመኖሪያ ቤት እና በመንገድ ላይ መገደላቸውንም ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እነዚህ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ላይ “ሆን ተብሎ እና በተስፋፋ ሁኔታ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ በመሆናቸው፤ እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተብለው ሊመደቡ የሚችሉ ናቸው” ሲልም አሳስቧል።  

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ የተቀመጡ ክልከላዎችን የሚጥሱ እና የጦር ወንጀሎችን እንዲሁም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ሊያቋቁሙ የሚችሉ ስለሚሆኑ የተሟላ የወንጀል ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተመልክታለች።

በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ እና በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

እንዲሁም መንግስት በክልሉ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ግጭት የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባሎች ተጠያቂ ለማድረግ ነጻ፣ ግልጽ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት መጀመር እንዳለብት አጽንዖት ሰጥቷል።

በተጨማሪም በግጭቱ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ ሊደረግ እንደሚገባ ኢሰመኮ ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተገንዝባለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here