ኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት እያቋቋመች ነው። በ2013 የጸደቀውን የመዋዕለ ነዋይ (ካፒታል) ገበያ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ 1248/2013 ተከትሎ፤ የግምጃ ቤት ሰነድ፣ ቦንድ፣ አክሲዮን እና ሌሎች ገበያዎችን በኢትዮጵያ ለማስጀመር ሂደት ላይ መኾኑ ይታወቃል።
አዲስ ማለዳ የመዋዕለ ነዋይ ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት ምስረታን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሕግ አማካሪ በሱፍቃድ ተረፈ በአዋጁ መሠረት ፍርድ ቤቱ “የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሥልጣን ይኖረዋል” ብለዋል። ፍርድ ቤቱ በአዋጅ ተቋቁሟል የተባለ ሲሆን “በቅርቡ” ኃላፊዎች ተሹመውለት ወደ ሥራ እንደሚገባ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሕግ አማካሪ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ለሽብር ድጋፍ ማዋል እንዲሁም ሌሎች የረቀቁ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት ዘርፍ በሆነው የመዋዕለ ነዋይ ገበያ፤ ደህንነቱ እና ተዓማኒነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከአራት የደህንነት አጋሮች ጋር የተዓማኒነት ግብረ ኃይል ስምምነት ተፈራርሟል።
በዚህ ግብረ ኃይል ውስጥ የኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጋር ተጣምረዋል።
ከፍርድ ቤቱ ጎን ለጎን በትላንትናው ዕለት በይፋ የተፈረመው “የተዓማኒነት ግብረ ኃይል” ዋና ዓላማን የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ እንደገለጹት፤ ገበያው አዲስ እንደመሆኑና የረቀቁ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት መሆኑ፣ ጊዜ የማይሰጡ በቀን ውስጥ በሚልየን የሚቆጥር ግብይት የሚፈጸምበት በመሆኑ በካፒታል ገበያ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መቆጣጠር ነው።
በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው በሃሰተኛ የትርፍ ህዳግ አክሲዮን መሸጥን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን በመቀነስ ገንዘባቸውን ፈሰስ ለሚያደርጉ ሰዎች መተማመኛ ማስፈለጉም ለግብረ ኃይሉ መቋቋም ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋን ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ እንደተናገሩት አሁንም ክትትል እየተደረገባቸው የሚገኙ ሕገ ወጥ የአክሲዮን ሽያጭና ግዢዎች የሚገኙ ሲሆን “እስካሁን እዚህ ገበያ ላይ ሲሰራ የነበረው ከሕግ ወጣ ያሉ ተዋንያንን በተቻለ አቅም ስንመክር ነበር፤ አንዳንዶቹ ላይ አስፈላጊ የሆነ ክትትል እየተደረገ ነው” ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ነገር ግን የወጣው ሕግ በአጠቃላይ “አስቻይ እንጂ ከልካይ አይደለም” ሲሉ ብሩክ ታዬ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የካፒታል ገበያ ራሱን የቻለ ፍርድ ቤት ለምን አስፈለገው ለሚለው ጥያቄ የሕግ አማካሪው በሱፍቃድ፤ የመዋዕለ ነዋይ ግብይቶች በባለሞያዎች መታየት ያለበት መሆኑ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል። በተጨማሪም በመደበኛ ፍርድ ቤት ከጊዜ፣ ከወጪ እንዲሁም ከባለሞያዎች እይታ አንጻር የተለየ “ቀልጣፋ” የዳኝነት ስርዓት እንደሚያስፈልግ የሕግ አማካሪው በተለይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ አምስት ዳኞች እንደሚኖሩት የተገለጸ ሲሆን፤ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢው በሕግ ዘርፍ እንዲሁም ቀሪዎቹ ሦስት ዳኞች የታክስ፣ ሒሳብና ሌሎች ተያያዥ ዘርፍ የካበተ ልምድ እንዲኖራቸው አዋጁ ያስገድዳል።
“የተዓመኒነት ግብረ ኃይል” አባል የሆነው ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በበኩላቸው “በዚህ ገበያ የሚሳተፉ ሁሉ ሕግ አክብሮ፣ ስርዓት አክብሮ ከሰራ በግሉም ይጠቀማል፤ ለአገርም ይጠቅማል። ሕግና ስርዓት ጥሶ የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን የሚያስከትለው ተጠያቂነት የአስተዳደር ቅጣት ብቻ ሳይሆን ከዛ ያለፈ ከበድ ያለ የወንጀል ተጠያቂነት ሊያስከትል እንደሚችል” አሳስበዋል።
ግብረ ኃይሉ ማጭበርበር ባለበት እና በሕገ ወጥ የአክሲዮን አቅርቦት ላይ የተሰማሩ እንዲሁም ገንዘባቸውን ፈሰስ ያደረጉ ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲያጡ ሰበብ የሚሆኑ አክሲዮን ሻጮችን ለፍርድ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ራሱን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ታሳቢ በማድረግ ከ“የተዓማኒነት ግብረ ኃይል” በተጨማሪ በመንግስት ተቋማት መካከል የተፈረመ የቴክኖሎጂ ግብረ ኃይል ስምምነትን ይፋ አድርጓል።
በዚህም ባለስልጣኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት በጋራ የመዋዕለ ነዋይ ገበያውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተፈጠረው ግብረ ኃይል የደህንነት ደረጃን ከፍ ማድረግ ዓላማው ነው።


