“አድዋን ተዉት”- የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ለ’አድዋ ሩጫ’ አዘጋጆች 

የካቲት 17 ቀን 2016 የአድዋ ድል በዓልን ‘አድዋ ሩጫ’ በሚል ስያሜ ሊካሄድ የነበረው የአደባባይ ሩጫ እንዳይካሄድ መከልከሉን የ’አድዋ ሩጫ’ አዘጋጆች ለአዲስ ማለዳ በላኩላት መግለጫ ገለጹ።

አዘጋጆቹ ‘አድዋ ሩጫ’ ለማካሄድ ከባለፈው ዓመት የካቲት 20 ቀን 2015 ጀምሮ ለአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከኪነ ጥበብ ዘርፍ ጋር በአጋርነት ለመስራት በመጠየቅ ህጋዊ ሂደት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከሁነቱ በሚገኘው ከወጪ ቀሪ ገቢ ትርፍ ስልሳ በመቶው የአድዋ ድል ታሪክ እና የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ታሪክ በመፅሐፍ ሰንዶ ለህትመት የሚያበቃበት ዕቅድ የያዘ እንደነበርም መግለጫው አመልክቷል። 

ቢሮውም ጥያቄውን ተቀብሎ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ለስምንት ወራት በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አዲስ ማለዳ ከመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ተረድታለች።

በሂደቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ለአድዋ ሩጫ ፍቃድ መስጠቱን ለአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በደብዳቤ ያሳወቀ ቢሆንም፤ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው ስምምነቱን በድንገት እንዲቋረጥ አድርገዋል። 

የጋራ ስምምነቱ የተቋረጠበትንም ምክንያት “ቢሮው ምንም አይነት ከአድዋ በዓል ጋር የተያያዘ ስራ አይሰራም፤ የሚሰራም ከሆነ በመከላከያ ወይም በከንቲባዋ ይህንን ስሩ የሚል ዝርዝር ትዕዛዝ ከተሰጠ ብቻ ነው” የሚል መሆኑን ከራሳቸው ከቢሮዋ ሃላፊ “የጋራ ስምምነቱ እንዲቀጥል ባናገርናቸው ወቅት በሰጡት መልስ መረዳት ችለናል” ሲሉ አዘጋጆቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

የሩጫው አዘጋጆች “በገጠሙን በርካታ ተግዳሮቶች እጅ ባለመስጠት በቀን ጥር 22 ቀን 2016 ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የአደባባይ ሩጫ ለማካሔድ ለከተማ አስተዳደሩ ደብዳቤ እንዲጽፍልን በሚል በደብዳቤ ጠይቀናል” ብለዋል።

በዚህ ደብዳቤም ከላይ የነበረውን ዕቅድ በአሁናዊ አገሪቷ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት ዕቅዱን በማሻሻል ከሁነቱ ከወጪ ቀሪ የሚገኘውን ሙሉ በሙሉ ገቢ የምግብ ዕጥረት ለገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲውል የሚል መሆኑን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ይኸንን ጥያቄ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮው የተቀበለው ሲሆን ጥር 23 ቀን 2016 የትብብር ደብዳቤ እንደጻፈላቸው አመላክተዋል።

በመቀጠልም መከላከያ ሚንስቴር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ለከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ የሁነቱን ዝርዝር የሚገልፅ ደብዳቤ እና የንግድ ስራ ፍቃድ በአባሪነት በማያያዝ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ጥር 23 ቀን 2016 የአደባባይ ሩጫ ለማካሔድ ፍቃድ ስለመጠየቅ በሚል በቀጥታ ለከንቲባ ፅህፈት ቤት የካቢኔ ዘርፍ ሃላፊ ቢሮ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አንስተዋል።

የከንቲባ ጽህፈት ቤትም በምላሹ፤ በካቢኔ ዘርፍ ሃላፊ ጥበቡ ፍስሃ ፊርማ ለሩጫው ፍቃድ በመስጠት ለአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲሰጥ ደብዳቤ መጻፉ ተጠቁሟል።

ከላይ የተጠቀሱት የሚከለከታቸው አካላት ለሩጫው ፈቃድ በመስጠት የትብብር ደብዳቤ የጻፉላቸው ቢሆንም፤ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ ሩጫውን ማካሄድ እንደማይችሉ ገልጾላቸዋል።

አዘጋጆቹም ይህንንም ግብረ መልስ ሊያስቀይር ይችላል ያሉትን “ምናልባት በፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ከሆነ የምትከለክሉን የዚህን ዓመት በፕሮፌሽናል አትሌቶች ብቻ ማካሔድ እንችላለን የሚል አማራጭ ሃሳብ በቃል ያቀረብን ቢሆንም፤ ከቢሮ ውጪ እንድንቆይ ተደርጎ ከደቂቃዎች የስልክ ውይይት በኃላ ዳግም ተጠርተን “አድዋን ተዉት” የሚል ትዕዛዝ አዘል የክልከላ መልስ ተሰጥቶናል” ብለዋል።

አዘጋጆቹ አክለውም “በዚህም ሕገ ወጥ ክልከላ ድርጅታችን የሞራልና የገንዘብ ኪሳራ ያጋጠመው ሲሆን፤ ከምንም በላይ ደግሞ አኩሪ ታሪካችን የሆነውን የአድዋ ድል በዓል እንደዜጋ ማክበር አለመቻሉ ክፉኛ አሳዝኖናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ይህንን ክልከላ ለህዝብ ለማሳወቅ የሚዲያ ሽፋን የጠየቋቸው “አንዳንድ ሚዲያዎች ፍቃዳቸው እንዳልነበር ለህዝብ ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here