የአፍሪካ ግዙፉ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ በ13 ዓመታት ውስጥ 

0
669

መጋቢት 24 ቀን 2003 የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ግድብ በመሆኑ የህዳሴ ጉዟችን መሐንዲሶች እኛው፣ ግንበኞቹና ሠራተኞቹ እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዟችን ባለቤቶች እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው” በማለት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይን አስቀምጠው ነበር።

ኢትዮጵያ በስተምዕራብ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ውስጥ የተጀመረው የግድብ ግንባታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተ ቢሆንም አንዳንድ የተፋሰሱ አገራትን ደግሞ አስቆጥቷል። በዚህም ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በግንቦት ወር 2003 በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረዋል። 

እንደ አውሮፓዉያን አቆጣጠር በ201 በኢትዮጵያ ሃሳብ አቅራቢነት ‘የኢንቴቤ ስምምነት’ የናይል ተፋሰስ አገራት የትብብር ማእቀፍ በኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ብሩንዲ መካከል የተፈረመ ሲሆን ከኬንያ እና ቡሩንዲ በስተቀር ያሉት አገራት ስምምነቱን የአገራቸው ሕግ አካል አድርገውታል። ስምምነቱ የናይል ተፋሰስ አገራት በእኩልነትና በዘላቂነት ለማልማት እና ለማስተዳደር ያለመ ነበር። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም በዚህ አውድ የሚገነባ በመሆኑ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው። 

ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም የአባይ ወንዝ ፍሰት አቅጣጫ መቀየሯን ተከትሎ የቴክኒክ ባለሞያዎቹ ሪፖርት ቢያቀርቡም ኢትዮጵያና ግብጽ በሪፖርቱ አተረጓጎም ላይ ሳይስማሙ ቀርተዋል።

ይህን ተከትሎ የወቅቱ የግብጽ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ሙርሲ በግድቡ ዙሪያ ጠንከር ያሉ ትችቶችን መሰንዘር ጀምረው ነበር። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ላይ ኃይል መጠቀም የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ ከማንሳታቸው ባለፈ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምትከሳት ይገልጹ ነበር።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ዓመታዊ የሦስትዮሽ ስብሰባ ለማካሄድ፣ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የመሰረት ልማት ፈንድ በማቋቋም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ አቋቁመዋል። በአዲስ አበባ፣ ካይሮ፣ ካርቱም እንዲሁም ዋሽንግተን ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሚኒስትሮችና የደኅንንት ኃላፊዎች የተገኙባቸው በርካታ ውይይቶች ቢደረጉም እስካሁን የጋራ አቋም ላይ ባለመድረሳቸው አሁንም በይደር የተያዘ ጉዳይ ነው። ይኹን እንጂ አሜሪካ በድርድሩ ወደ አንድ ቡድን ያጋደለ አቋም አራምዳለች በማለት ኢትዮጵያ ወቅሳ ከውይይት መድረኮችም ቀርታለች።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን የተደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች አንዳንዶቹ ተስፋ ሰጪ መስለው ቢታዩም፤ የኢትዮጵያ እና ግብጽ መወቃቀስ ግን አልቀረም። ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አገራት በማይጎዳ መልኩ የዓባይ ወንዝን እንደምትጠቀም በተለያዩ መድረኮች ስትገልጽ፤ ግብጽ በበኩሏ በቅድሚያ በመካከላችው የማሰሪያ ስምምነት እንዲፈረም ከመወትወት ባለፈ ወታደራዊ አማራጭ እንደሚከተሉ ዛቻ ሲያስተላልፉ ነበር። 

ግድቡ በ2008 እና 9 ውሃ ለመያዝ በተቃረበበት ወቅት የግድቡን ሙሌት በተመለከተ በኢትዮጵያ የቀረበውን ሀሳብ ግብጽ አልቀበለውም በማለቷ ኢትዮጵያ “የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅና የውሃ ሙሌት ሥራውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የግብጽን ይሁንታ አልፈልግም” በማለት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብታለች።

ግብጽም በምላሹ ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን የመሙላት ሥራውን እንዳትጀምር ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብታ ነበር። 

በዚህ ሁሉ መሀል ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን እንዳትጠቀም እና ኢትዮጵያ ብድር አግኝታ የልማት ስራዎች እንዳትሰራ ለማድረግ ሀሰተኛ ትርክቶችን መፍጠር፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎችን መደገፍ እና በሃይማኖት ተቋማትና በሌሎች ጉዳዮች ለኢትዮጵያ የቤት ስራ ለመስጠት መታገላቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል። በግብጽና በብሪታንያ መካከል የተፈረመው የቅኝ ግዛት ስምምነት እና በግብጽ እና ሱዳን መካከል ብቻ የተፈረመ ስምምነትን በማንሳት በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለመሻር ጥረዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐምሌ 5 ቀን 2012 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጀመሪያ ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ እንደያዘ ይፋ ተደርጓል።

 አበይት ክስተቶች 

  • ለ21 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ህልፈት
  • ከመስከረም 2005 እስከ መጋቢት 24 ቀን 2010 ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ የቆዩት ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ ባልተለመደ መልኩ በፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸው 
  • የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 24 ቀን 2016 ወደ ስልጣን መምጣታቸው 
  • የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ሐሙስ ዕለት ጠዋት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በመኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው 
  • ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሃይድሮ መካኒካል ስራዎችን ወስዶ ሲሰራ የነበረው በወቅቱ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የተባለው ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውና ሌሎችም ሰራተኞች በሙስና ወንጀል መያዛቸው 
  • ሜቴክ ከተመሰረተበት 2002 ጀምሮ እስከ 2012 ድረስ በተደረገ የኦዲት ምርመራ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ታውቆ ነበር 

የግድቡ ሙሌት ቀጥሎ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2015 ድረስ አራት ዙር የውሃ ሙሌት በማድረግ ተጠናቋል። ይህን ተከትሎ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ከተፋሰሱ አገራት ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መቀጠል በአሮፓውያኑ 2015 የተፈረመውን የመርህ ስምምነት እና ዓለም አቀፍ ህግ የሚጥስ ነው ብትልም ቀሪ ግንባታው እንደቀጠለ ነው። 

የግድቡ ስራ ሲጀምር በሥድስት ዓመታት ውስጥ በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ እንዲጠናቀቅ ታቅዶ ነበር። ላለፉት 13 ዓመታት ከአርሶ አደር፣ ተማሪ፣ ባለሀብቶች፣ ዲያስፖራዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች እና የግል ሰራተኞች በአጠቃላይ መላው ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሲቪል ሥራ 99 በመቶ ተጠናቋል።

ዋናው የግድቡ ክፍል 107 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት የሚይዝ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ አንድ በመቶው ሥራ ብቻ እንደሚቀር የተገለጸ ሲሆን፤ የተርባይንና ጄኔሬተር ተከላ ሥራው 78 በመቶ መጠናቀቁ ተገልጿል። የግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግንባታው በሰባት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይና ሙሉ የፕሮጀክቱ በ2017 እንደሚጠናቀቅ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ለግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ከ 19 ቢሊየን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ባለፉት 8 ወራት 932 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here