ያለፉት ስድስት ዓመታት መንግስት ቅድሚያ መስጠት ላለበት ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጥ እና አገሪቱን የመበተን አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት ተስፋፍተው ያሉበት እንደሆነ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ገለጹ።
የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበት ስድስተኛ ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2016 ነበር። በተለያዩ አካባቢዎች የድጋፍ ሰልፎች ከመደረጋቸው ጎን ለጎን የፓርቲው አባላት “ፍሬያማ” ስድስት ዓመታት እንዳለፉ እየገለጹ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የለውጥ” ስድስተኛ ዓመትን አስመልክተው “በለውጡ መሃንድስ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተመራው የለውጥ ኃይል በብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተና ውስጥ ሆኖ በርካታ ስኬቶችን በመጎናጸፍ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ያለፉትን ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ጉዞ በፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ምን ይመስላል በማለት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራሮችን ጠይቃለች።
በቅርቡ ከእስር የወጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አብርሃም ሀይማኖት ሰላም በሌለበት ልማት የለም ብለዋል። “ይኼነው የሚባል ሕዝብን የሚያኮራ የሚያስመሰግን ስራ አለ ብሎ ለመናገር የሚያበቃ ስራ ባይኖርም ከሀገር ውጭ የነበርነውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ግቡ መባሉ እንዲሁም በሕዳሴ ግድቡ ላይ የተሰራ የልማት ስራ ጥሩ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ቃል አቀባይ በቃሉ አጥናፉ በበኩላቸው ከስድስቱ ዓመታት በፊት የነበሩት 27 ዓመታት “ጨለማ” ነበር ብለው ያለፉት ስድስት ዓመታት ግን “ድቅድቅ ጨለማ” ነው በማለት ተናግረዋል።
ይህን ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ “ያለፈው 6 ዓመት ምንም ጥሩ ነገር የለውም። የብዙ ሰው ደም የፈሰሰበት፣ ከቤቱ የተባረረበት እንዲሁም የተሰደደበት ነው። ጅማሮው ብዙ የሚስተካከል ነገር ያለበት የሚመስል ተስፋ ሰጪ የነበረ ቢሆንም ሂደቱ ግን በተቃራኒው “ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል” ብለዋል።
የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ የስድስት ዓመታቱን ሂደት ገልጸው ነበር። በመግለጫቸውም መንግስት በሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ ችግሮችን በድርድርና በውይይት ለመፍታት፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ይህ አማራጭ ተቀባይነት ሲያጣ” የአገሪቱ ሕግ “በሚፈቅድለት” አኳኋን ሕግ የማስከበር ስራ መስራቱን እና እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም የሕግ ማስከበር ስራው “ውጤት እያመጣ” ነው ብለው “ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን” እንዲሁም “በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር መቻሉን” የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እዩኤል ሰለሞን በበኩላቸው ያለፉት ስድስት ዓመታት የዘር ፖለቲካ የገነነበት እንዲሁም የፖለቲካን ፍላጎት በኃይል የመቆጣጠር ድርጊቶች የተስተዋሉበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ በሺድ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የተስፋ ጅማሮ የታየበት ጊዜ የነበረ ቢሆንም “እነዚህ ተስፋ የነበራቸው ነገሮች ብዙ አልቆዩም፤ እየሳሱ እና እየቀጨጩ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው”።
የነእፓ አመራሩ እንደገለጹት ከቃላት ግጭት እስከ ጦርነት የደረሱ አለመግባባቶች ብዙ ውድመት እና ብጥብጥ መፍጠሩን ገልጸው “አለመግባባቶችን በዴሞክራሲያዊ ውይይት ከመፍታት ይልቅ ኃይል የተመረጠበት ጊዜ” መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አብርሃም ሀይማኖት “እነደሀገር ያለፉት ስድስት ዓመታት ዋጋ የከፈልንበት እንደዚህ በተለየ ሁኔታ ብዙ መከራ ያየንበት ጊዜ የለም” በማለት ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የእስካሁን ቆይታ የገለጹት።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ያለፉት አምስት ዓመታት “በየዕለቱ” በሚባል ደረጃ ጦርነት መኖሩን ይገልጻል። በሰሜን ኢትዮጵያም ለሁለት ዓመታት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት ውጊያ ተካሄዷል። ያለፉት ዘጠኝ ወራት ደግሞ በአማራ ክልል የተከሰተው የትጥቅ ውጊያ እንደቀጠለ ነው።
የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር “ገዢው ፓርቲ የሰላም እና የሕግ የበላይነት ላይ ምንም ስራ የሰራ አይመስልም” ሲሉም የሁኔታውን አስከፊነት አስረድተዋል።
“የፌደራል መንግስቱ ከጦርነት ሊያሶጣን አልቻለም” የሚሉት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ ደግሞ “ከአንዱ ጦርነት ወደሌላው እየገባን ነው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅማቸው የተዳከመበት ስብሰባ እንኳን ማድረግ ያልቻልንበት ጊዜ ነው” ብለዋል።
በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ባህሪዎችም “ብዙ ረሀብ ያለበት፣ ሆስፒታሎች የአገልግሎት ችግር ያለባቸው፣ የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ያላመጡበት ነው” ሲሉም የነእፓ አመራሩ ገልጸዋል።
ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በተመለከተ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አብርሃም ሀይማኖት የውጭ ግንኙነቱ “ወጣገባ የሚል በግልጽ ያልታወቀ ፖሊሲ ነው” ብለዋል። የተመሰረተው በጥቅም ላይ ይሁን በአገሪቱ ጥቅም ላይ በወል አይታወቅም” ብለው ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት ጤናማ ባለመሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ አመላክተዋል።
በተጨማሪም ከኤርትራ ጋር ጥሩ የመግባባት ጅማሮ ያሳየ ግንኙነት እንደነበረ የሚያስታውሱት አብርሃም ሀይማኖት፤ ምክንያቱ በውል በማይታወቅበት ችግር የሰላም ግንኙነቱ መበላሸቱን እና ከሶማሊያ ጋር አሁን ያለው ውጥረትም ግንኙነትን እንዳሻከረ ያስረዳሉ። በሰላም ረገድ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ለጎረቤት ሀገራት ቢሆንም ላለፉት ስድስት ዓመታት ይህን ተግባር አላየንም ሲሉም የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ አስተዳደር የተከወኑ የከተማ ልማቶች ጥሩ የሚባሉ እና ለቱሪስት መስህብነት ታስበው የተገነቡ ስለመሆናቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገልጸው ነገር ግን ለዚህ ፈሰስ የተደረገው መዋዕለ ንዋይ የሀገሪቱን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት፣ የግብርና ዘርፍ ለመደገፍ ቢውል አልያም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር መለየት ቢቻል የተሻለ እንደነበር ጠቁመዋል።
የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ በሺድ በስድስቱ ዓመታት እንደ ጥሩ ነገር የሚነሱት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋም እንዲሁም ከብዙ ውድመት በኋላም ቢሆን የትግራይ ክልል አንጻራዊ ሰላም ናቸው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ “ምድራዊ ሃይል ሊያስቆመው የማይችለውን የብልጽግና ጉዞ” ላይ ስለመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የስድተኛ ዓመት በዓለ ሲመትን አስመልክቶ እየገለጹ ቢሆንም ገዢው ፓርቲ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አገሪቱ እንደ አገር ለመቀጠል ትቸገራለች ሲሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገልጸዋል።



