በግጭቱ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን በሳምንት ውስጥ ሶስት እጥፍ ጨምረዋል፤ ከ50 ሺህ በላይም ደርሰዋል- የመንግስታቱ ድርጅት

0
296

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ከሚገኙት አላማጣ እና ሌሎችም ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ አጎራባች እና በዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ መሸሻቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

 

የተፈናቃዮች ቁጥር ከአንድ ሳምንት በፊት ሚያዝያ 8 ቀን ከተመዘገበውም “በሶስት እጥፍ ጨምሯል” ሲል የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ገልጿል። ይህንንም ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ህጻናት በሕይወት ለማትረፍ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ውስን መንግስታዊ እና ሰብዓዊ ድርጅቶች በዋነኛነት የምግብ እና የጤና አገልግሎቶችን ማቅረብ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተፈናቃዮች ብዛት ጋር የተጣጣመ አይደለም።

በአላማጣ ከተማ እና በራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፍላ ወረዳዎች ከሚያዚያ 5 እና 6 ቀ 2016 ጀምሮ በተቀሰቀሰው የትጥቅ የተደገፈ ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50ሺ በላይ መድረሱን የዞኑ ባለስልጣናት መግለጻቸውንም ነው ተ.መ.ድ ያስታወቀው።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና አረጋውያን በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ከቆቦ በሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ‘ጋራ ሌንጫ’ አካባቢ የኢንዱስትሪ ክፍት ቦታ ላይ ተጠልለዋል ተብሏል።

በወልዲያ እና ቆቦ ከተሞች የፌደራል ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን ተከትሎ ትላንት ሚያዝያ 14 ቀን 2016 የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ እንደነበረም ተገልጿል። በአላማጣ እና ቆቦ መካከል የንግድ ትራንስፖርት በአላማጣ እና በማይጨው መካከል ባለው መንገድ መቀጠሉን ቢሮ ጠቁሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገምጋሚ ቡድን በሚያዚያ 19 ቀን 2016 መደበኛ የእርዳታ ጥያቄን ተከትሎ በአማራ ክልሎች ላይ ተሰማርቷል ተብሏል። ይኹን እንጂ አዎንታዊ ለውጦች ቢኖሩም እየጨመረ ከሚመጣው የተፈናቃዮች ቁጥር ጋር ያልተመጣጠነ መሆኑ ተገልጿል።

“የህወሓት ኃይሎች ጀምረውታል” የተባለው ጥቃት ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ “ህወሓት እጁ የለበትም” ያለ ሲሆን በአንጻሩ የአማራ ክልል መንግስት “ህወሓት አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሞብናል” በማለት የሚቃረን መግለጫ ማውጣታቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ በዚሁ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጻ “ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ልዩ መብት በማጎናፀፍ በሌሎች ክልሎች በሌለ እና ፈጽሞ በማይታሰብ መልኩ ታጣቂ ኃይል የማሠማራት መብት በመሰጠቱ” አሁን በአማራ ክልል ያለው ቀውስ እንዲቀጣጠል መነሻ ነው ሲል መክሰሱ ይታወሳል።

የፌደራል መንግስቱ ጉዳዩ በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈታ መግለጹን ተከትሎ የሕዝብ አሰፋፈር እና የተፈናቃዮች “ትክክለኛነት” ጉዳይ እያወዘገበ የሚገኝ ሲሆን ለሕዝበ ውሳኔ የማይመች ሁኔታ ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች ውንጀላዎች ይደመጣሉ።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here