የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ከመንግስት ጋር በማበር” ፓርቲውን ለማፍረስ ሞከሯል በሚል በሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ተከሰሰ

0
547

ሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በፓርቲው የቀድሞ አባላት ላይ ክስ መመስረቱን ለአዲስ ማለዳ በላከላት ጽሁፍ አስታውቋል።

ፓርቲው ክስ የመሰረተው “ቦርዱ የፓርቲው ውስጠ-ጉዳይ ላይ ጠልቃ በመግባት” እንዲሁም ከፓርቲው ከተሰናበቱት የቀድሞ አባላት ጋር በማበር የሀገሪቱ ህግና የኢፌዴሪ ህገመንግስት በተፃረረ መልኩ የተለያዩ “ህገወጥና አደገኛ ውሳኔ” በማስተላለፋቸው መሆኑ አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።

የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ በላከው እና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጻፈው የክስ መጥሪያ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐብሄር ምድብ ችሎት የተጻፈ ነው።

ፓርቲው እንዳስታወቀው “ፓርቲውን ለማፍረስ ከመንግስት ተልዕኮ ወስደው የፓርቲውን ህልውና ለአደጋ በማጋለጣቸው ምክንያት በፓርቲው ህገ-ደንብ መሠረት ከፓርቲው የተሰናበቱ” አባላት ጋር የምርጫ ቦርዱ ተባብሯል ሲል ከሷል።

እንዲሁም ፓርቲው ከዚህ በፊት በዲሲፕሊን ጥሰት ምክንያት ከፓርቲው የተሰናበቱ ግለሰቦች የፓርቲውን ንብረትና መስሪያ ቤት አስረክበው በስርዓት መውጣት ሲገባቸው “ከመንግስት ተልዕኮ በመቀበልና በቦርዱ አጋዥነት ለቀው ባለመውጣታቸውና በፓርቲው ስም የተለያዩ ህገወጥ እንቅስቃሴ” እያደረጉ ይገኛሉ በተባሉት
👉🏿 ጴጥሮስ ዱቢሶ
👉🏿 ቦርሳሞ ቦሮጄ እና
👉🏿 ማቴዎስ ካኑ ላይ ክስ መመስረቱን ገልጿል።

ከዚህ ቀደም የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ጴጥሮስ ዱቢሶ እና በግብረ አበሮቻቸው አማካይነት ፓርቲውን ከውስጥ ለማፍረስ ሲሰሩ ተጨባጭ ማስረጃ አግኝቻለው በማለት የዲስፕሊን እርምጃ በመውሰድና በማገድ ፓርቲውን ከመፍረስ መታደግ ተችሏል ሲልም ፓርቲው መግለጹን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

ሲፌፓ በተወሰደው የዲሲፕሊን እርምጃ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተከሳሾች በቀረበለት አቤቱታ ለመሻር የሄደበት አካሄድ “አደገኛ” በመሆኑ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል ሲል የካቲት 11 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ አሳስቦ ነበር።

በተመሳሳይም የሲዳማ ፈደራሊስት ፓርቲ “ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በመንግስት አካላት የተቀናጀ ፓርቲውን የማፍረስ ሴራ” ከአገራዊ ምክክሩ ሊወጣ እንደሚችል መግለጹን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

“በአጠቃላይ እየደረሰብን ያለው እስር፣ አፈና፣ ስደት፣ ሁከት፣ እንዲሁም ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የመንግስት አካላት የተቀናጀ ፓርቲውን የማፍረስ ሴራ በሀገራዊ ምክክር የለውጥ ተስፋ እንዲንቆርጥ አድርጎናል” ሲል ገልጾም ነበር።

በዚህም የፌደራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ክሱን ለመስማት ለ ግንቦት 12 ቀን 2016 ልደታ ምድብ ችሎት አንደኛ ምርጫ ፍትሃብሔር ቀጥታ ክስ ችሎት እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ለቦርዱ ልኳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here