በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር እስከ ሞት ድረስ ያሉ ከባድ ቅጣቶች እንደሚያስፈልጉ የሕግ ባለሞያዎች ገለጹ

0
446

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የተበዳይ [ሳሮን/ ለዘገባው ሲባል ስሟ የተቀየረ] እናት በልጃቸው ላይ በተፈጸመ ጾታዊ ጥቃት፤ ከአንድም ሁለቴ ብቻ ሳይሆን ተበድለውም በሰቀቀን እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል። የሳሮን እናት “ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በምልበት ወቅት የመጀመሪያውም የሁለተኛውም ልጄ ላይ የደረሰው ጥቃት አስደንጋጭና ለብዙ ውጣ ውረዶች የዳረገኝ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

በመጋቢት ወር አጋማሽ በቀናት ልዩነት ውስጥ የሦስት ዓመት ህጻን እንዲሁም የ90 ዓመት አዛውንት ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ጫፎች የተፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ጨምሮ፤ አዲስ ማለዳ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የተፈጸሙ እና እንደማሳያ የሚጠቀሱ በሴቶች ላይ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ለመዳሰስ ባደረገችው ጥረት የፍትሕ ሂደቱ የሚያደርስባቸው በተበዳዮች ላይ ተጨማሪ በደልን እንደሚያደርሱ የሚያመላክቱ ታሪኮችን ተመልክታለች። የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ቤተሰቦችን እንዲሁም የሕግ ባለሞያዎችን አዲስ ማለዳ አነጋግራለች።  

ጥቅምት 1 ቀን 2014 ወላጆቻቸው ለስራ በሌሊት ጥለዋቸው የወጡት የ17 ዓመቷ ሳሮን ከታናሽ እህቷ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው በተኙበት ሦስት ጎረምሶች ቤት ውስጥ ገብተው የሚያደነዝዝ መድኀኒት በመርጨት አስገድደው ደፍረዋታል። በልጃቸው ላይ የተፈጸምውን ጥቃት ለፖሊስ ያመለከቱት ቤተሰቦቿ “ምንም ማስረጃ ባለመኖሩ እንዲሁም ድርጊቱን ፈጻሚዎቹ ባለመያዛቸው” የሚሉ ምክንያቶች ተሰጥቷቸው አሁንም ፍትህን እንደናፈቁ አሉ። 

የፖሊስ ምላሽ ይህ ቢሆንም፤ ወጣቷ ከተለያዩ የብዙኀን መገናኛ ጋር ባደረገችው ቆይታ “ከጥቃቱ በኋላ ለማይግሪን እና ለጭንቀት መዳረጓን” ተከትሎ ህመሟ በመበርታቱ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል መላኳን ትገልጻለች። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን መደበኛ ህይወቷን ለመመለስ እየሞከረች ያለችው ወጣት ሳሮን ግን “ከቤት ለምን ትወጫለሽ” የሚል ማስፈራሪያ ከ200 ብር ጋር በተደጋጋሚ ይላኩላት ነበር። 

ይህን ድርጊት ከአባቷ ጋር በመሆን ለፖሊስ ሲያመለክቱ “እንደዚህ የሚያሳስብ ነገር አይደለም። ስጋት ካለሽ ግን ደውይልን።  ብሩን ሄዳቹ ቡና አፍሉበት” የሚል ምላሽ እንዳገኙ አዲስ ማለዳ ሰምታለች። በዚህ ብቻ ያላበቃው ጥቃት፤ ዳግም ከሁለት ዓመታት በኋላ በዚህ ዓመት ባለፈው ወር መጋቢት 16 ቀን 2016 ከመኖሪያ ቤቷ ጠርተው ጥቃት አድርሰውባት እንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢ የሚገኝ ጫካ ውስጥ ጥለዋት መሰወራቸውንም ተናግራለች። 

የሳሮን ወላጅ እናት ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት በሃዘን የተሞላ ቆይታ “በወቅቱ የነበረው ሁኔታ እና ስሜቱ በቃላት መግለጽ የሚቻል አይደለም። ልጄ እስካሁን ምንም ደህና አይደለችም፤ ጸበል ነው ያለችው” በማለት ይገልጻሉ። “ልጃችን ደህና እንድትሆን እና ፍትህ እንድታገኝ እንፈልጋለን” የሚሉት እናት አሁን የተለያዩ የሕግ አካላት ጉዳዩን እንደያዙት ነግረውናል። 

ወጣቷ በበኩሏ “በመጀመሪያው ጥቃት ፖሊስ ጥፋተኞቹን ይዞ እርምጃ ወስዶ ቢሆን ኖሮ ሁለተኛ ጥቃት አይፈጸምብኝም ነበር” በማለት ሕጉ ከለላ እንዳልሆናት ገልጻለች።

የፆታ እና ወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎች ባህሪያቸው እና በፍርድ ቤት የሚታዩበት መንገድ በመላው ዓለም “የተንሸዋረረ” ቢሆንም በኢትዮጵያ እና መሰል ታዳጊ አገራት ችግሩ የከፋ ነው። የጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ባህሪያቸው ተመልካች በሌለበት ድብቅ ቦታና ሁኔታ መፈፀማቸው፣ ተጠቂዎች እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ቦታና ሁኔታ መሆኑ፣ በስፋት ጥቃት አድራሾች የስጋ ዝምድና አልያም ሌላ ትውውቅ መኖር እንዲሁም ማህበረሰቡ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ማስረጃ ለመስጠት ቁርጠኛ አለመሆን ይጠቀሳሉ። ለአብነት ደግሞ በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ የ5 ዓመት ህፃን ልጅ ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል በመፈጸም ጥፋተኛ የተባለዉ ግለሰብ በ6 ወር እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ማስታወስ ይቻላል። 

እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከሆነ በጾታዊ ጥቃት ላይ የሚደረጉ የወንጀል ፍትህ ሂደቶች ላይ የማስረጃ እጦት እና እጥረት፣ የምስክር መካድ፣ ተጠቂዎችን ያላማከለ የፍትህ ሂደት፣ በፍትህ ሂደቱ ተጠቂዎችን መልሶ መጉዳት፣ ተጠርጣሪዎች የማምለጥ፣ ጥፋተኛዎች ተገቢ ቅጣት ያለማግኘት ችግሮች ይታዩባቸዋል። 

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሕግ ባለሞያዎች ሕብረተሰቡ ውስጥ ካለው የግንዛቤ ክፍተት ጀምሮ የፍትህ አካላት እንዲሁም ሕጎች ራሳቸው በጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች ላይ ተጨማሪ ጫና የሚያሳድሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከጊዜ ወደጊዜ እጅግ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን አጽንዖት ሰጥተውበታል።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና በጾታዊ ጥቃቶች ላይ ትኩረት ያደረጉት ባለሞያ አበባየሁ ጌታ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የአገሪቱ የወንጀል ሕግ ሰፊ ክፍተት አለበት። “ለአብነትም በተባበሩት መንግሥታት መግለጫ መሠረት በትዳር ጓደኛ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር እንደ ጾታዊ ጥቃት ሲወሰድ በወንጀል ሕጉ ግን እንደ ወንጀል እንዳይቆጠር ተደርጓል። ጾታዊ ጥቃት የሚለው ቃል ወይም ሃሳብ በየትኛውም የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ ተጠቅሶ፣ ተጠቃሎ፣ ተተርጉሞና ተብራርቶ አይገኝም” ሲሉ የሕግ ባለሞያው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

የጾታ ተኮር ጥቃት ወንጀሎች በተለያዩ የወንጀል ሕጉ አንቀፆች ቢደነገጉም እነዚህን ወንጀሎች በአንድ ላይ አሰባሰቦ፣ አጠቃሎና ትርጉም ሰጥቶ የተቀመጠ የወንጀል ሕግ የለም። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጾታዊ ጥቃት በሚል የሚገልጻቸው ከፈቃድ ውጪ አካላዊ ንክኪ፣ በቤት ውስጥ በሴት ሕጻናት ላይ የሚፈፀም የወሲብ ጥቃት፣ ከጠለፋ ጋር የተያያዙ የኃይል ተግባራት፣ በትዳር ጓደኛ የሚፈጸም ተገዶ መደፈር፣ የሴቶች ግርዛትንና ሴቶችን የሚጎዱ ሌሎች ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ከትዳር ጓደኛ ውጪ የሚፈጸሙ የኃይል ተግባራትና ከብዝበዛ ጋር የተያያዙ የኃይል ተግባራት፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸም አካላዊ፣ ወሲባዊ እና ሥነ ልቦናዊ የኃይል ተግባራት፣ የወሲብ ትንኮሣ፣ የወሲብ ጥቃት፣ በሴቶች መነገድንና ተገዶ ሴተኛ አዳሪ መሆን፣ በጠቅላላው በሕብረተሰብ ውስጥ የሚፈጸሙ አካላዊ፣ ወሲባዊ እና ሥነ ልቦናዊ የኃይል ተግባራት፤ በየትኛውም ቦታ በመንግሥት የሚፈጸሙ ወይም ችላ ተብለው የሚታለፉ አካላዊ፣ ወሲባዊና ሥነ ልቦናዊ የኃይል ተግባራት ጾታዊ ጥቃት ናቸው ሲል ያስቀምጣል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለአዲስ ማለዳ ሃሳባቸውን የገለጹት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የሕግ ባለሞያ ፆታን መሰረት ያደረጉ የወንጀል ፍትህ ሂደቶች ላይ የዳኞች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል። 

“ዳኞች ገና በማስረጃ ባልተረጋገጠ ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ፤ ተጠቂ ሴትን በሚወነጅል መንገድ ጥያቄ ማቅረብ፣ ክብር አለመጠበቅ፣ የሕፃናትን ስነ ልቦና አለመረዳት፤ የጾታዊ ጥቃት ወንጀሎችን በልዩ ሁኔታ አለመረዳትና ተጎጂዎችን ማመናጨቅ (ለምሳሌ መረጃ የማግኘት አስቸጋሪነትንና አንዳንድ ተጠቂዎች ጥቃቱ የተፈፀመበትን ቀንና ሰዓት መለየት ሊያዳግታቸው እንደሚችል አለመረዳት)፤ ሕፃናትና ሴቶች ችሎቶች ምደባ ልዩ ስልጠና አለመጠየቁና በአብዛኛው በልምድ መሰራቱ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ” ሲሉ ባለሞያው ተናግረዋል። 

ጥቂት ወራት ወደኋላ መለስ ስንል በጅግጅጋ ከተማ የ11 ዓመቷ ታዳጊ ፋጡማ ኡጋስ በቡድን ከተደፈርች በኋላ በገመድ ታንቃ ተገድላ መገኘቷን እናስታውሳለን። ወላጅ አባቷም “ስለ እኔ ልጅ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በዚህ መንገድ ሕይወታቸው ለጠፋ ሁሉ ፍትሕ እንዲሰፍን እጠይቃለው” ማለታቸው ከሰሞነኛ መነጋገሪያነት አላለፈም። 

ተመጣጣኝ ቅጣትን በተመለከተ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሞያው ካሳሁን ሙላቱ የአገሪቱ ሕግ ወንጀል ብሎ ለሚደነግጋቸው ተግባሮች “ተመጣጣኝ የሚለውን” ቅጣት ማስቀመጡን ገልጸው፤ ከችሎት ችሎት አልያም ዳኞች ነገሩን የተረዱበት መንገድ እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር ችግር አንጻር የአተረጓጎም ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ነገር ግን “በአጠቃላይ ለወንጀል ድርጊቶች የሚሰጡ ውሳኔዎች አነስተኛ ናቸው” ማለት ባይቻልም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከፍተኛ ቅጣትን የሚጥል እንደሆነ ካሳሁን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እንዲያውም ሕጉ “ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ለማስተማር አይሞክርም፤ በቅጣት ያምናል” ሲሉ የሕግ ባለሞያው ገልጸዋል።

የወንጀል ሕግ በባህሪው በየጊዜው የሚቀያየር ባለመሆኑ አንድ ሕግ ሲወጣ በማመዛዘን ለመጪው ጊዜ ታሳቢ መደረግ ይገባዋል የሚሉት ሌላኛው የሕግ ባለሞያ አበባየሁ ጌታ፤ የወንጀል ሕጉ አስተማሪና ተመጣጣኝ ቅጣት የለውም ማለት አይቻልም በሚለው አስተያየት ከካሳሁን ጋር ይስማማሉ። 

ነገር ግን ሕጉ አስተማሪ እርምጃዎችን እየወሰደ የማይቀጥል ከሆነ መሰል ጥቃቶች እየተበራከቱ እንደሚቀጥሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት አበባየሁ ጌታ፤ አስተማሪ እና ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት እንዴት ይተላለፋል የሚለው ክሱ ላይ የሚንተራስ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የተሰራው ወንጀል ምንድነው፣ ጥቅም ላይ የዋሉ ሌሎች ነገሮች አሉ ወይ፣ ወንጀሉ የተፈጸመበት ሁኔታ እና በምርመራው የሚገኘው ውጤት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።

“ከጊዜ ወደ ጊዜ ሴቶች ላይ እየደረሰ የመጣው ጥቃት አስከፊም አሳሳቢም ነው” የሚሉት የሕግ ባለሞያ እና አማካሪ ካሳሁን ሙላቱ አጥፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ የማያገኙ እና ተሸሽገው የሚኖሩ ከሆነ ወንጀሉ እንዲስፋፋ በር የሚከፍት መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። 

እንደ ኢትዮጵያ ባላደጉ አገራት ደገሞ የሕግ ግንዛቤው አነስተኛ መሆን እና የሕግ የበላይነት ብዙም ያልተፈተነበት በመሆኑ እና ሕግን እንዲያስፈጽሙ የተቋቋሙ አካላት የማስፈጸም አቅም ውስን በመሆኑ ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት ምቹ እድል እንደሚፈጠርላቸው የሕግ ባለሞያዎቹ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሳስበዋል።

በሐዋሳ ከተማ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ሳጅን የኋላመብራቴ ወልደማርያም በተባለ ግለሰብ የጠለፋ ወንጀል ሰለባ የሆነችው ጸጋ በላቸውን ለቀናት ሰውሮ ካቆየ በኋላ በሕግ ቁጥጥር ስር እንደዋለ አይዘነጋም። የሐዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ታህሳስ 18 ቀን 2016 በዋለው የሴቶችና ህጻናት ችሎት የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ሁኔታዎችን መርምሮ በተከሳሹ ላይ የ16 ዓመት ጽኑ እስራት ወስኗል። 

በክስ ሂደቱ ላይ ፍርድ ቤቱ የቀረበለት የሃኪም ማስረጃ የአእምሮ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል አስገድዶ መድፈር መድረሱን ቢያመለከትም “የጉዳት መጠን አያሳይም” በሚል ማስረጃው ውድቅ እንዲሆን መደረጉን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። የሕግ ባለሞያው አበባየሁ ጌታ እንደሚሉት የአእምሮ ጉዳት ያደረሰ ከፍትኛ ቅጣት እስከ ዕድሜ ልክ ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቱ በቂ ማስረጃ የለም በሚል ‘በመደበኛ የአስገድዶ መድፈር’ እንዲታይ ማድረጉ ቅጣቱን ከእድሜ ልክ ወደ ሀያ ዓመት ጽኑ እስራት ዝቅ እንዳደረገው አስረድተዋል።

ነገሩን በእንቅርት ላይ የሚያስብለው ደግሞ ተበዳይ ጸጋ በላቸው የ16 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደበት ተከሳሽ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከእስር ቤት ወጥቷል ስትል በማህበራዊ ሚድያ መግለጿ ነበር። ግለሰቡ በዋስትና ወጣ እንዳይባል እንኳን በኢትዮጵያ ሕግ አስር ዓመትና ከዚያ በላይ እስር የተፈረደባቸው ወንጀሎች የዋስትና መብትን የሚያስነፍጉ እንደሆኑ የሕግ ባለሞያዎች ያስረዳሉ። 

የዋስትና መብት የሚመለከታቸው መርማሪ ፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ እና ፍርድ ቤትን ሲሆን፤ በዋስትና ወረቀት የተመለከቱትን ግዴታዎች አመልካቹ የሚፈፅም የማይመስል ከሆነ (የዋስትና ግዴታዎቹ ተጠቂንና ተጠቂና ምስክሮችን መጠበቅ ሊሆን ይችላል)፣ ዋስትና ቢፈቀድለት ተከሳሽ ግዴታውን ሊፈጽም አይችልም ተብሎ ሲታመን ዋስትና ሊከለከል እንደሚችል ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሕግ ባለሞያዎች ተናግረዋል። 

እንዲሁም ተጠርጣሪው ወይንም ተከሳሹ ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈጽም ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን እና ምስክሮችን በመደለል፣ በማባበል ወይም አስረጂ የሚሆኑበትን ሊያጠፋ ይችላል ተብሎ ከታሰበም የአንድ ሰው የዋስትና መብት እንደሚከለከል ይጠበቃል።

ነገር ግን ዳኞች በዘፈቀደ እንዳይወስኑ ደረጃ የወጣላቸው እና ያልወጣላቸው በሚል ተከፋፍለው የሚገኙ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መኖሩንም ገልጸው “ዳኞች በዚሁ መሰረት የመወሰን ግዴታ አለባቸው፤ አንድም ለህሊና አንድም ለሕጉ የሚገዙ ከሆነ አስተማሪ ቅጣት ያስተላልፋሉ” ሲሉ አበባየሁ ጌታ ገልጸዋል። ይኹን እንጂ አንዳንድ ለፍርድ ቤት የተሰጡ ስልጣኖች በመኖራቸው “ይኼን ስልጣን አለአግባብ የሚጠቀሙ ዳኞች አሉ። በዚህም ቅጣትን አለአግባብ የሚቀንሱበት ሂደት አለ” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

በመተከል ዞን የ5 ዓመት ህጻን ላይ አስገድዶ መድፈር የፈጸመውና በስድስት ወራት እስር ይቀጣ የተባለውን ግለሰብ በተመለከተ ሃሳባቸውን የሰጡት አበባየሁ፤ ቅጣቱ “ሌላውን የሚያበረታታ፤ ባደርገውስ የሚል አስተሳሰብን” የሚፈጥር መሆኑን ተችተዋል። 

ፖሊስ በግልጽ ምርመራ ሂደቱን ማድረግ፣ አቃቤ ሕግም በየትኛው አንቀጽ ክስ እንደሚመሰርት እና ከዛም አልፎ ፍርድ ቤቱ የልጁን ዕድሜ ከተመለከተ በኋላ ግዴታው ባይሆንም ማጣራት እና ክሱ እንዲሻሻል ማድረግ እንደነበረበት መክረዋል። ይህ ክስ የተመሰረተበት አንቀጽ ትክክል ባለመሆኑ ዳኛው እና አቃቤ ሕጉ የዲሲፕሊን ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን እና ከስራ መታገዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

አስገድዶ መድፈር በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑን ያነሱት የሕግ ባለሞያው አበባየሁ ጌታ የወንጀል ሕጉ ጾታዊ ጥቃቶችን ከከፍተኛው የአሲድ ጥቃት እስከ ለከፋ እና ትንኮሳ ያሉትን በግልጽ አላሰፈራቸውም ይላሉ። 

ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በባሌበቷ እና የሁለት ልጆቿ አባት የሆነው አሪፍ አልዪ በባለቤቱ አያንቱ ሙስጠፋ ላይ የሰልፈሪክ አሲድ ጥቃት ፈጽሞ ፊቷን፣ ጭንቅላቷን፣ ጀርባዋን፣ አንገቷን፣ ደረቷ እና እጇ አካባቢ መቃጠሏ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በደረሰባት ጥቃትም “ለልጆቼ ሞታለች ብላቹ ንገሯቸው” ማለቷ የማይታየውን ስነ ልቦናዊ ጫና አግዝፎ ያሳየ ነበር። ለፖሊስ ጥቆማ ከተሰጠ ወራት ቢያልፉም እስካሁን ድረስ ወንጀለኛው አልተያዘም።  

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የሕግ ባለሞያ “አንዳንድ ወንጀሎች በወንጀል ሕጉ ውስጥ የሚገባቸውን ያህል ክብደት አልተሰጣቸውም ይሆናል” በማለት ፍርድ ቤቶች በሕጉ ከተቀመጠው የቅጣት መጠን በልጠው የመወሰን ስልጣን እንደሌላቸው አስረድተዋል። ለዚህም ሰበር ሰሚ ችሎት በሚሰጠው አስገዳጅ ሕግ ትርጉም ጥፋተኝነት የተወሰነበት አካል ከሕግ ድንጋጌው ውጪ የሚሰጥ የቅጣት ውሳኔ የሕግ መሰረት አይኖረውም። 

በአሁኑ ሰዓት ፍርድ ቤቶች እየሰሩ የሚገኙት የአሲድ ጥቃትን “በከባድ አካል ጉዳት በማድረስ ወይንም የመግደል ሙከራ በማድረግ” በሚል የሕግ ክፍል በመዳኘት ሲሆን “የወንጀል ሕጉ በግልጽ የአሲድ ጥቃትን የሚከለከል፣ እንዲሁም ከፍ ያለ እስከ ሞት ድረስ ያሉ ቅጣቶችን በማስቀመጥ መሰል ጥቃቶች በተደጋጋሚ እንዳይፈጸም ማድረግ ይቻላል” ሲሉ የሕግ ባለሞያው አበባየሁ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

መንግስት ሕግ የሚያስከብረው ባለው አቅም፣ አደረጃጀት የሰው ኃይል እና ቁጥብ ሃብትና ገንዘብ ነው የሚሉ የሕግ ባለሞያዎች የተወሰነ ክፍተት መኖሩን ይገልጻሉ። አበባየሁ ጌታ እንደሚገልጹት ደግሞ ጾታዊ ጥቃቶች በመንግስት ትኩረት አልተሰጣቸውም።   

የፍትሕ ሂደቱ እና የሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዴት ይቀየር?

የሃይማኖት ተቋማት ምዕመናኖቻቸው በስነ ምግባር እንዲታነጹ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ተቀዳሚ መፍትሄ እንደሚሆን የሕግ ባለሞያዎቹ ገልጸዋል።  

በሕብረተሰቡ ዘንድ ለተጠቂዎች የሚሰጠው የተዛባ አመለከላከት ፆታዊ ጥቃት ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ ከማድረጉ ባሻገር የፆታዊ ጥቃት ወንጀሎችን መከታተልና መቅጣት ትዳር እንደማፍረስ፣ ቤተሰብ እንደመበተን ሳይቆጠር ሁሉንም ለሕግ አሳልፎ መስጠት እንደሚገባም ተጠቁሟል። 

ፖሊስ ጉዳዩ ቢሮው ድረስ እስኪመጣለት ድረስ ከመጠበቅ በራስ ተነሳሽነት የማጣራትና ምርመራዎችን የማድረግ ተነሳሽነት መኖር፣ የሕግ አካላትም ሕጉን በአግባቡ መተርጎም እንደሚገባ የሕግ ባለሞያዎች አሳስበዋል። የሕግ አካላት ወንጀል መከላከል ላይ በስፋት መስራት እና ለወንጀል ድርጊት የሚያጋልጥ ሁኔታን አስቀድሞ መከታተል ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተመላክቷል።

የሕግ ባለሞያዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ይህ ሲሆን ሕብረተሰቡ በሕግ የበላይነት በማመን ወንጀል ፈጻሚዎችን ወደ ሕግ እንዲያቀርቡ እና “ምን ዋጋ አለው ይለቀቃሉ? ተመጣጣኝ ቅጣት አይሰጣቸውም፤ ተመልሰው ያጠቁናል” ብለው እንዳይሰጉ ማድረግ ይቻላል።

ፍርድ ቤቶችም የሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው አውቀው ጥፋተኛዎች ላይ ተገቢውን ቅጣት መስጠት፣ ተጎጂዎች ላይ ዳግም ጥቃት እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም ክብርን የጠበቀ የችሎት ሂደት ማከናወን ይገባቸዋል። 

አዲስ ማለዳ በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሞያዎች ማሕበርን ምላሽ እና ሀሳብ ለማካተት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here