ንግድ ባንክ ለሰራተኞቹ የሚሰጠው ብድር ላይ ቅናሽ አደረገ

0
724

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት በተገበረው አዲስ አሰራር ተዘዋዋሪ ብድር፣ ከአንድ ግዜ በላይ የሚሰጥ የቤት ብድር እንዲሁም በደሞዝ እርከን ጭማሪ መሰረት የሚሠጡ የብድር ማሻሻያዎችን ጨምሮ ለሰራተኞቹ የሚያቀርበው የብድር አይነቶችን ቀነሰ።

የሰራተኞቹን የስድስት ወር ደመወዝ የሚያበድረው ባንኩ አንድ ሰራተኛ የተበደረውን የስድስት ወር ደመወዝ ከፍሎ ሲጨርስ ድጋሚ የሚበደረው የነበረ ሲሆን በተያዘው የበጀት አመት የተደረገውን የደመወዝ ማስተካከያ ተከትሎ ግን ይህ ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲቆም መደረጉን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የባንኩ ሰራተኞች ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ተዘዋዋሪ ብድሩ ሲከፈል ከሚቀመጥበት የብድር መመለሻ ቋት ውስጥ አውጥቶ መጠቀም ያሚቻል የነበረ ሲሆን አሁን ግን ይህ በመከልከሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በየወሩ የሚቆረጥባቸው ስራተኞችን የጎዳ መሆኑንም ሰራተኞቹ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም ከዚህ ቀደም ለቤት መስሪያ ብድር የወሰደ ሰው ብድሩን ክፍሎ ባይጨርስም በየአመቱ ባለው የደመወዝ ጭማሪ ለተጨማሪ ግንባታ ብድር ቢፈልግ ባደገው ደመወዙ ልክ የብድር ውሉ ተስተካክሎ ሚያገኘው ተጨማሪ ብድርም እንዲቆም ተደርጓል።

ከዚህ ቀደም አንድ ቤት ገዝተው ሙሉ ለሙሉ ገንዘቡን ከመለሱ በኋላ በድጋሚ የሚሰጥ ብድር እንዲቆም መደረጉን የተናገሩት ሰራተኞቹ፣ ውሳኔው ከዚህ ቀደም ያላቸውን ቤት ሸጠው አዲስ ለመግዛት ሂደት ላይ የነበሩ ሰራተኞችን የጎዳ ነው ብለውታል፡፡

ቤቶች ከመገዛታቸው በፊት የሚደረግ ግምት ላይም በተገነባበት ዋጋ እንዲሆን መሃንዲሶች ላይ ጫና አለ የተባለ ሲሆን ይህም በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መንግስት በገነባበት ዋጋ እንደሚገመት እና የገበያ ዋጋውን ግማሽ እኳን የማይሆን ገንዘብ ብቻ እንዲፈቀድ መደረጉን ሰራተኞቹ ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here