የደኅንነት ቀበቶ በሕዝብ ማመላለሻ ተሳፋሪዎች ላይ እንዲተገበር ተወሰነ

0
306

ከመጪው ታኅሳስ ወር ጀምሮ እስከ 150 ኪ.ሜ የሚጓዙ ሚኒባሶች፣ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከ5 እስከ 8 መቀመጫ ያላቸው ተሽከርካሪዎችና በአገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የደኅንነት ቀበቶ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ መመሪያ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

በአገራችን መመሪያው አሁን እየተተገበረ ያለው በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የትራፊክ አደጋ ይህንን መመሪያ ተግባራዊ ለማድርግ መገደዱን የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታውቋል።

መመሪያው አዲስ አለመሆኑን የገለፁት የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዮሐንስ ለማ፣ ከዚህ ቀደም በ208/2003 እንዲሁም 395/2009 የትራፊክ መመሪያ ደንቦች ላይ ወጥቶ ወደ ተግባር አለመግባቱን ገልፀዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም እንደተናገሩት የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከስት ዋነኛ ምክንያቶች ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ፍጥነት፣ የደኅንነት ቀበቶን አለማሰር ናቸው በአገራችን ከ 2005-2010 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ውስጥ 40 በመቶ የሞት እንዲሁም ቀላል ጉደት 60 በመቶ በላይ የደረሰው ተሳፋሪዎች ላይ እንደነበር ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው፣ የደኅንነት ቀበቶ የሚያደርጉ በፊተኛው የተሽከርካሪ ክፍል ውስጥ የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች ከ45-50 በመቶ እንዲሁም ከኋላ የሚቀመጡ ከ25 እስከ 30 በመቶ ከሞት አደጋ እንደሚተርፉ ያሳያል።

አዲሱ መመሪያ ሁሉንም ተሽከርካሪዎች እንደማይመለከት የተገለፀ ሲሆን፣ በተለይም በ አጭር ርቀት ማለትም የከተማ ታክሲዎችን፤ የከተማ አውቶብሶችን እንዲሁም ባለ ኹለት እግር ተሽከርካሪዎች የሚተገበረው የትራፊክ መመሪያ ደንብ እንደማይመለከታችው ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here