በምን እንግባባ?

0
380

‹‹አንድ ሰው ‹እንቢ!› ካለ አልፈልግም፤ ‹እሺ› ካለ እስማማለሁ ማለቱ ነው›› የሚል መሠረታዊ ትምህርት ይሰጥ ይሆን? በምን እንግባባ? ሴቶች በተለያየ አጋጣሚ ከወንድ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የተሰማቸውን መልስ ቢሰጡም ወንዶቹ (ብዙውን ጊዜ) የሚገባቸው በአንጻሩ/በተቃራኒው ነው።

የተፈጥሮ ጉዳይ ከሆነ የሚያስረዳኝ ሰው እፈልጋለሁ። ግን አንዲት ሴት በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለቀረበላት ጥያቄ መልሷ እንቢ ከሆነ አልፈልግም ማለቷ ነው፤ አበቃ! በሞቴ እያሉ እያግደረደሩ እንደሚያቀርቡት ምግብ ወይም እንደሚያቀብሉት ጉርሻ፣ አግደርድረው እንደሚከፍሉት የታክሲ ሒሳብ አይደለም፤ የሕይወትና የሰውነት ክብር ጉዳይ ሲሆን እንቢ ማለት እንቢ፤ አልፈልግም ማለት አልፈልግም ነው።

ከሰሞኑ የ16 ቀን ንቅናቄ አንዱ ጉዳይ ይህ የወንዶች መልስን በራስ መንገድ እየተረጎሙ የመረዳት ጉዳይ ነው። ይህ በመንገድ ላይ፣ በየትራንስፖርቱ፣ በየቤቱና በየትዳሩ ይስተዋላል። የሚገርመው እንቢ ማለትን ማስረዳት ብቻ ሳይሆን እሺታንም ማብራራት ከባድ ነው። አንዲት ሴት ከወንድ ለሚቀርብላት የትኛውም ዓይነት ጥያቄ መልሷ ‹እሺ› ከሆነ፤ በቀላል የተገኘች፣ በቀላል እሺ የምትል ተሸናፊ ተደርጋ ትቆጠራል።

በምን እንግባባ! ትርጉም አሰጣጡ ለየቅል ነው። እንቢ ስትል እንቢታዋን የ‹ሴትነት ተፈጥሮ› አድርገው የሚቆጥሩና ለጥፋት የሚጋበዙትን ስናይ፣ የጥቃቱ ነገር ብቻ አይደለም የሚነሳው፤ የቋንቋና መግባባት አለመቻል ጉዳይም ነው።

በእርግጥ በቅርበት በማኅበራዊ ኑረታችንም የማንግባባበት ሁኔታ ብዙ ነው። ቅርቧ ለሆነ ወንድሟ ‹ሴቶች ጥቅም ፈላጊ አይደለንም፤ የተወሰኑ እንደዛ ዓይነት ሴቶች ይኖራሉ፤ ጥቅም ፈላጊ ወንዶች እንዳሉት ሁሉ። ፊልም ላይ የምታየው ሁሉ እውነት አይደለም› ብላ በመናገር ልታሳምነው የምትዳክር ሴት አውቃለሁ። ተግባብተው ግን አያውቁም፤ ‹እህቴ አንቺ ጥቅም ፈላጊ ላትሆኚ ትችያለች፤ ሴቶቹ ግን እንደዛ ናቸው› ይላታል መልሶ።
እንዲህ ያለው ነገር በተለያየ መንገድ የሚያጋጥመን ሴቶች ጥቂት አይደለንም። የሚያስቡትን እንጂ የምንናገረውን የማይሰሙ ብዙ ወንዶች አሉ።

በምን እንግባባ? በደል የፈጸመ በኩራት ሲንቀሳቀስ በደል ተቀባይ ሴት አንገቷን ደፍታ፣ በሯን ቆልፋ እንድትማቅቅ የሚያደርገው ደግሞ አንድም ማኅበረሰቡ ራሱ ነው። ምን ተከፍሎት፣ ምን አይቶና ምን ሰምቶ እንደሆነ ባይታወቅም ሁሉም የወንድ ጠበቃ ነው የሚመስለው። ‹መቀመጫዬን መታኝ!› ብትል፤ ማን እንዲህ ለብሰሽ ውጪ አለሽ፤ ‹ተደፈርኩ› ብትል ማን በጨለማ ብቻሽን ሒጂ አለሽ፣ ‹ደበደበኝ› ብትል ማን ተናገሪው አለሽ ነው መልሳቸው።

እንዴት ነው መግባባት የምንችለው? ማን ነው ጆሮው ሳያደላ ሰምቶ የሚዳምጥ? ማን ነው ‹‹በደል ደረሰብኝ›› የምትልን ሴት፤ ‹‹ማን ተጠጊው አለሽ?›› ማለትን ትቶ ከፍትኅና እውነት ጎን የሚቆመው? እንዴት ነው ተግባብተን የምንቀጥለው ወይስ መግባባቱን ትተነው በዚሁ እርሷ ቻይ፣ እርሷ ታጋሽ፣ እርሷ ዝምተኛ፣ እርሷ በደል ተሸካሚ፣ እርሷ ገመና ሸፋኝ፣ እርሷ አንገት ደፊ ሆና ትቀጥል።

ይሄ በሴቶች ላይ የሚፈጸም በደል ድርብርብ ነው። አንድ ቋንቋ እያወሩ መግባባት አለመቻል በተለያየ ዓለም እንደመኖር ነው። በተመሳሳይ አውድ ላይ ለእርሷ ‹አልፈልግም› ማለት ለእርሱ ‹እሺ› ማለት ከሆነ ወይም ከመግደርደር ከተቆጠረ፤ እንግዲህ ከዚህ በላይ አለመግባባት ወዴት አለ?

እርዱን አይደለም፣ አግዙን፣ ተሸከሙን አባብሉን ያለ የለም፤ ቢያንስ ተረዱን ነው ጉዳዩ። ቢያንስ እንግባባ ነው። የምንናገረውን እንጂ የምታስቡትን አታዳምጡ ነው። እውነት ለመናገር ሴቶች በትውልድ መካከል እንዲሁም በዓለም ሁሉ ላይ ያሉት ቻይ እንዲሁም ታጋሽ ባይሆኑ፤ ይህ አለመግባባት የዓለምን ጦርነት በቀሰቀሰ፤ ከጦርነት የባሰም በሆነ ነበር። ኧረ እንግባባ!
በሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here