በሰባት ዓመት ውስጥ ከፍተኛው የምግብ የዋጋ ጭማሪ በኅዳር ወር ተመዘገበ

0
672

በአገሪቷ በሰባት ዓመት ተኩል ውስጥ ትልቁ የዋጋ ግሽበት በኅዳር 2012 መመዝገቡን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ይፋ የሆነው የማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ አመላከተ። በዚህም መሠረት መስከረም 2005 ተመዝግቦ ከነበረው 21.3 በመቶ የምግብ ዋጋ ግሽበት በኋላ በኅዳር ወር የታየው የምግብ ዋጋ ጭማሪ ከፍተኛው ሲሆን 24 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የኤጀንሲው መረጃ ያመላክታል።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ኅዳር ከነበረው የምግብ ዕቃዎች አማካይ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በተገባደደው ኅዳር ወር የነበረው ዋጋ ላይ አንድ አራተኛ ገደማ ጭማሪ መኖሩን ያሳያል። በኅዳር ወር 2ዐ12 የተመዘገበው አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም የኤጀንሲው ሪፖርት ያሳያል። ይህ ከመስከረም 2005 አንስቶ ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል። በተመሳሳይም አጠቃላይ ምግብ-ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በ 16 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በተለይ ለምግብ ዋጋ መጨመር በኅዳር ወር የእህል ዓይነቶች በተለይም ጤፍ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ የተጋገረ እንጀራ እና የበሬ ስጋ የተጋነነ ባይሆንም የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸው እንደ ምክንያት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ስንዴ ዳቦ፣ ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጎመን፣ ካሮት፣ ምስር፣ ቅቤ፣ የምግብ ዘይት እና ወተት አይብና ዕንቁላል ቅናሽ አሳይተዋል ሲል ኤጀንሲው አስታውቋል።

በኹለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከስምንት በመቶ እንዳያልፍ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከነሐሴ 2009 ጀምሮ እስከ አሁን ባለኹለት አሃዝ እድገት እያሳየ ይገኛል። ይህም የአገሪቷ ማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ላይ ችግር ከመፍጠሩ ባሻገር በድህነት አረንቋ ውስጥ ያሉ ዜጎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው። በተለይም በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ አንድ ሦስተኛ ዜጎች በድህነት ውስጥ መኖራቸው ከፍተኛ የሚባል የኑሮ ቀውስ እያሳደረ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎቹ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ ትልቁ ዘላቂ መፍትሄ አቅርቦትን መጨመር እና የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማሳጠር ነው ይላሉ። በተጨማሪም መንግሥት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊስን በመከተል የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ እንደሚችል አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ‹‹በአገሪቱ በቅርቡ እየባሰ የመጣው የዋጋ ግሽበት የፖለቲካውን አለመረጋጋት ተከትሎ የተፈጠረ ክስተት ነው›› ያሉት አብዱልመናን ‹‹በዚህ የተነሳ በተፈጠረ ጥርጣሬ ምክንያት የዋጋ ግሽበቱ ተባብሶ ቀጥሏል›› ይላሉ። ‹‹ፖለቲካውን ማረጋጋት ከተቻለ ገበያው ላይ እየታየ ያለውን ጥርጣሬ ተገማች ማድረግ የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ሙያዊ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here