በቡራዩ ተነስቶ በነበረው ግጭት ተሳታፊ በተባሉ ሰዎች ላይ ብይን ተሰጠ

0
938

ከመስከረም 2/2011 እስከ መስከረም ስድስት 2011 ባሉት ቀናት ወደ አዲሰ አበባ ይመለሳሉ በተባሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ሥነ ስርዓት ላይ የእርስ በእርስ ግጭት አስነስተዋል የተባሉ 17 ተከሳሾች እንዲከላከሉ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ።

በልደታ ምድብ ችሎት ኅዳር 24/2012 በዋለው ችሎት በ እነ ታፈሰ ተሰማ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው ከነበሩ 33 ተከሳሾችን ጉዳይ ሲሰማ የቆየው ፍርድ ቤቱ፣ በ23ቱ ላይ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ ካዳመጠ በኋላ በ17ቱ ላይ የቀረበው ክስ በማስረጃ የተረጋገጠ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ተከሳሾችም ይከላከሉ ሲል ወስኗል።

ክስ ከቀረበባቸው ግለሰቦችም ዐስሩን ተከሳሾች በሌሉበት ክስ ተመስርቶ ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ክሱ እንዲቋረጥ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። ከተከሳሾቹ መካከልም ጠበቃ ማቆም ለማይችሉት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆም የተደረገ ሲሆን፣ አቃቤ ሕግ በስድስት ተከሳሾች ላይ ያቀረበው ማስረጃ በቂ ስላልሆነ በነጻ አሰናብቷቸዋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ኹከትና ብጥብጥ በሰዎች ሞት፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ተጠረጥረው ክስ የተመሠረተባቸውን ሰዎች መዝገብ ለአንድ ዓመት ያህል ሲመለከት ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራውን ሲያከናውን ቆይቶ ከጥቅምት 20/2011 ጀምሮ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፣ በታኅሳስ 109 ተከሳሾቸ ላይ ክስ መሥርቷል። በወቅቱም 81 ተከሳሾች በማረሚያ የነበሩ ሲሆን 28ቱን ለመያዝ እቅድ እንደነበረው ፖሊስ አስታውቆ ነበር።

በተመሳሳይ ወቅት በአዲስ አበባ በተፈጠረው ግጭት ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጎራ በመሆን አምባጓሮ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት 17 ግለሰቦች መካከል ዘጠኙ እንዲከላከሉ ብይን መሰጠቱ ይታወሳል።

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ‹‹የእርስ በእርስ ግጭት ላይ በመሳተፍ›› ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ያቀረበውን ክስ ወደ ‹‹አምባጓሮ›› የቀየረው ፍርድ ቤቱ፣ ክስ እና ምስክር ሰምቶ ካገባደደ በኋላ አንድ ተከሳሽ በቸልተኝነት ሰው በመግደል ወንጀል ራሱን እንዲከላከል በይኖ ስድስት ተከሳሾች በከባድ አንባጓሮ የቀረባቸውን ክስ ፍርድ ቤቱ በአምባጓሮ እንዲከላከሉ ማለቱም ይታወሳል። ኹለት ተከሳሾችም በተመሳሳይ በከባድ ውንብድና ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በውንብድና እንዲከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል። ክስ ከተመሰረተባቸው 17 ግለሰቦች ስድስቱ ባለመቅረባቸው ምክንያት ክሳቸው የተቋረጥ ሲሆን የተፈጠረውን ግጭት ሽፋን በማድረግ የስርቆት ወንጀል በመፈጸም የተከሰሱትን ግለሰብ በነፃ አሰናብቷል።

በአጠቃላይም ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ እና በቡራዩ በተከሰተው ግጭት በተደራጀው መዝገብ ከተከሰሱ 109 ግለሰቦች መካከል 26ቱ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ጉዳያቸው እየታየ ሲሆን ቀሪዎቹ ያልተገኙ እና የተወሰኑት በነጻ ተሰናብተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here