ልማት ባንክ በሩብ ዓመቱ ኹለት ቢሊዮን ብር ብድር ፈቀደ

0
535

በኪሳራ ውስጥ የቆየው ልማት ባንክ በ2012 የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለተለያዩ ዘርፎች ኹለት ቢሊዮን አንድ መቶ ሚሊዮን ብር እንደፈቀደ አስታወቀ። ባንኩ በሦስት ወር ውስጥ አዳዲስ ካጸደቃቸው ብድሮች ውጪ ከዚህ ቀደም የተፈቀዱ ኹለት ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆኑ የተለያዩ ብድሮችን መክፈሉንም አስታውቋል።

ባንኩን ለኪሳራ ዳርጓል በተባለው ዝናብን ጠብቆ የሚከናወን የሰፋፊ እርሻ የሚሰጡ ብድሮችን ሙሉ ለሙሉ ያቆመ ሲሆን፣ 99 ሚሊዮን ብር የሚሆን ለእርሻ መስጠቱንም የባንኩ የእቅድ እና ስትራቴጂ ክፍል ኀላፊ ናትናኤል ተናግረዋል። ይህም የአበባ እና የወተት ልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርበው ውል ተፈጽሟል።

በሩብ ዓመቱ የተፈቀደው ብድር አልሚዎች የራሳቸውን ሃብት ፈሰስ አድርገው ከጨረሱ እስከ ኹለት ዓመት ባለው ጊዜ በተለያዩ ደረጃዎች ይከፈላሉ ብለዋል።
‹‹ባንኩ የልማት ባንክ እስከሆነ እና የአገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መሠረትም ግብርና እስከሆነ ለግብርናው የምንሰጠውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን፣ ነገር ግን ዝናብ ላይ ለተመሰረት የግብርና ሥራ የምናበደረውን ብድር በመተው ወደ መስኖ ለማተኮር አዲስ ስትራቴጂ ቀርጸናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የግብርና ኢንቨስትመንት እንደ ሌላው ወዲያው ብድርን ለመመለስ የሚያስችል ባለመሆኑ ብድሩ ለተወሰነ ጊዜ በአጠራጣሪ ብድር ሰንጠረዥ ውስጥ ሊቆይ ይችላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እስከ አሁንም በዝናብ ላይ ለተመሠረት ግብርና ባንኩ አበድሮት መመለሱ አጠራጣሪ ደረጃ ላይ ያለው የገንዘብ መጠን ስድስት ቢሊዮን ብር እንደሆነም ኀላፊው ተናግረዋል። የሕዝብ ገንዘብ ያለ አግበብ መባከን አይገበውም ያሉት ናትናኤል፣ ነገር ግን አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገው የግብርናውን ዘርፍ በገንዘብ አቅም ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።

አጠራጣሪ ብድር ውስጥ ከገቡት ብድሮች መካከል በተለይም የአበባ እርሻ፣ የጨርቃጨርቅ በቶሎ ብድር መክፈል ባይጀምሩም አሁን ግን መሻሻሎች መኖራቸውን ኀላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከመሠረቱም አሰጣጣቸው ላይ የውል ችግር ያለባቸው ብድሮች ሙሉ በሙሉ የተበላሹ ቢሆንም አጠራጣሪዎቹ ላይ በተደረገው ማሻሻያ ግን መመለስ መጀመሩን አክለው ገልፀዋል። ባንኩ በዓመት የማይሰበስበውን ያክል ብድር በሦስት ወር ለመሰብሰብ መቻሉን አጠራጣሪ ብድሮች ላይ ያለውን መሻሻል ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት የተሰጠው ብድር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ 55 በመቶ መቀነሱ የሚጠበቅ ነው ሲሉ የባንክ ኢንዱስትሪ ተንታኙ አብዱል መናን መሐመድ ይናገራሉ። ልማት ባንክ ለሚሰጠው ብድር ጠንካራ መስፈርቶችን መከተል መጀመሩ ብዙ የብድር ውሎችን እንዳያፀድቅ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለው እንደሚያምኑም ገልፀዋል።

የባንኩ አቅም ቀላል በማይባል አጠራጣሪ እና የተበላሸ ብድር በመመታቱ ምክንያት ጫናው ቀላል አይሆንም፣ እንደ አብዱል መናን ገለጻ። በዝናብ ላይ ለተመሠረተ ግብርና ከዚህ ቀደም የተሰጡ ብድሮችም አክሳሪ በመሆናቸው እና አሁንም የኪሳራ አደጋ ሊያጋጥም ስለሚችል ባንኩ በዝናብ ላይ ለተመሠረተ ግብርና ብድር ያለማቅረቡ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉም ብለዋል።

‹‹ከዚህ በኋላም በዝናብ ላይ ለተመሠረተ ግብርና ብድር ለማቅረብ ግልጽ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ይጠይቃል›› ያሉት አብዱልመናን፣ ባንኩ የሰበሰበው ብድር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ማደጉን ይናገራሉ። ‹‹ልማት ባንክ ብድሮቹን ለመሰብሰብ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ያሳያል። የሚሰበሰበው ብድር መጠን ማደጉ ባንኩ በመጪው ሩብ ዓመት የሚለቀውን እና የሚፈቅደውን ብድር እንዲጨምር ያደርገዋል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here