ንግድ ባንክ የአሊያንስ አውቶቢሶችን ለሀራጅ አቀረበ

0
938

በግሉ ዘርፍ ብቸኛ የብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ የሆነው አሊያንስ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ንብረት የሆኑና በብድር ዕዳ ከተያዙ 100 አውቶቡሶች መካከል 33 የሚሆኑትን ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ መነሻ ዋጋ ንግድ ባንክ ለጨረታ አቀረባቸው።

በ2009 አጋማሽ ከንግድ ባንክ በተገኘ 70 በመቶ ብድር 100 አውቶቢሶችን ያስገባ ሲሆን ድርጅቱ በውሉ መሠረት እዳውን ባለመክፋሉ ንግድ ባንክ አውቶቡሶቹ አገልግሎት እንዳይሰጡ እና እንዳይንቀሳቀሱ እግድ አውጥቶባቸው ነበር።

በንግድ ባንኩ እንዳይንቀሳቀሱ ከታገዱ 100 አውቶቢሶች መካከልም በተሻለ ይዞታ ላይ ያሉት ተመርጠው ለሃራጅ የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት መልኩ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአሊያንስ ሥራ አስኪያጅ አብዱል ፈታ ሑሴን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በ2 ሺሕ 500 ባለ አክሲዮኖች የተመሠረተው አሊያንስ ትራንስፖርት ለምን ውጤት ማምጣት እንዳልቻለ የሚያብራሩት አብዱልፈታ ‹‹ድጋፎቹ ቢቀሩ እንኳን ስምሪት ሲሰጠን በኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች በመሆኑ ምክንያት በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መሥራት የምንችለውን ያክል ተንቀሳቅሰን መሥራት አልቻልንም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ግልጸዋል። ወደ ሥራ ከመግባታችን በፊት ማቆሚያ ቦታ እንደሚመቻችልን በታሪፍ ላይ ድጋፍ እንደሚደረግልን ቃል ተገብቶልን ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

ጉዳዩን ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ድረስ መፍትሔ ለማፈላለግ አንኳኩተናል ሲሉ ገልፀዋል። ድርጅቱ ብድሩን በሥራ ላይ ሆኖ ለመክፈል ለንግድ ባንክ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱንም ለኪሳራው ምክንያት ነው ተብሏል።

አውቶቢሶቹ ሥራ ሳይጀምሩ ለብድሩ የተሰጠው የእፎይታ ጊዜ አልቆ ባንኩ ገንዘቡን መክፈል ባለመቻሉ ከመደበኛ ስምሪት ውጪ በመሆን 100 አውቶቢሶች ያለሥራ ቆመው ለብልሽት መዳረጋቸውንም ጠቅሰዋል። ወደ አገር ውስጥ በገቡበት ወቅት ለማቆሚያ ቦታ ተፈቅዶልን የነበረው መስቀል አደባባይ አካባቢ ነበር። ሆኖም በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ቦታው መከልከሉን የገለጹ ሲሆን፣ አውቶቢሶቹ ገና ሥራ ሳይጀምሩ በአስመጪው የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ከስድስት ወራት በላይ ቆመው፤ በዚህ መኻል ባንኩ የሰጠው የእፎይታ ጊዜ እንደተጠናቅቀ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በደርጅቱ ተቀጥረው የነበሩ ከ400 በላይ ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ጉዳዩን ለሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በማሳወቅ ከሥራ ተሰናብተዋል።
‹‹በእኛ ላይ የደረሰውን ኪሳራ ያየ ማንኛውም ድርጅት አውቶቢሶቹን ገዝቶ ወደ ሥራ ይገባል የሚል ግምት የለኝም›› ሲሉም ተናግረዋል። አክለውም ከፍተኛ የአገር ሃብት የወጣባቸው ንብረቶች ለከፍተኛ ብልሽት እየተዳረጉ በመሆኑ ለእኛ እንኳን ባይሰጠን ሌሎች ድርጅቶች ሊጠቀሙባቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ከሰኔ 2011 ጀምሮ በአውቶቢሶቹ ላይ ጨረታ እየወጣ መሆኑን ገልፀው፣ አክሲዮን ማኅበሩ በጉዳዩ ላይ ተስፋ ባለመቁረጡ በንቃት እየተከታተለው ነው ብለዋል። ለሀራጅ ጨረታ ከቀረቡት አውቶቢሶች ውስጥ ከፍተኛው መነሻ ዋጋ 964 ሺሕ ብር ነው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የንግድ ባንክ የሥራ ኀላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጧት ለሦሰት ቀናት ያደረገቸው ጥረት አልተሳካም።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here