በፖለቲካ ቀውስ ለተጎዱ አልሚዎች ብድር ተዘጋጀ

0
559

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን በኢንቨስትመንት ተቋማት ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ማገገሚያ የሚሆን ብድር ለማመቻቸት የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን አሰማራ።

ከልማት ባንክ እና ከመድህን ድርጅቶች የተውጣጡ አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉትን የኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጥናት በማድረግ የጉዳት መጠናቸውን በመለየት ለኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያቀርቡ ሲሆን በዚህ መሰረትም የጉዳት መጠናቸው ታይቶ ብድሩ እንደሚመቻች ታውቋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ወራት በተከሰተው አለመረጋጋት በቋሚ ንብረት እና ማሽኖች ላይ ጉዳት ደርሷል ያለው የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ፣ መንግሥት በ2008 እና በ2009 በኢንቨስትመት ላይ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አድርጓል። በተጨማሪም በተለያዩ ማሽኖች ላይ በደረሰው ጉዳት ባለሀብቶች ከውጭ ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስገቡ መደረጉ ተገልጿል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም በነበረው አለመረጋጋት በኢንዱስትሪ፣ በአበባ እና በፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰማሩ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ላይ በነበረው ጉዳት ጥቂት በማይባል የንብረት ውድመት ደርሷል ያሉት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መኮንን ኃይሉ፣ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ዜጎችም ሥራ አጥ ሆነዋል ብለዋል።

መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት ላጋጠሙ ጉዳቶች ካሳ ለመክፈል አቅም የለኝም በማለቱ ምክንያት የብድር አማራጭ መወሰዱን መኮንን ተናግረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የፖለቲካ ቀውሶች የተለያዩ የልማት አውታሮችን እና የኢንቨስተመንት ሥራዎችን ዒላማ ማድረጋቸው ለአልሚዎች ከባስ,ድ የኪሳራ ምክንያት መሆኑ ሲነሳ ይሰማል።

ኮሚሽኑ በ2012 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ የሩብ ዓመት አንድ ቢሊዮን ብር የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው መሳካቱን ገልጿል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲፃፀር የ13 በመቶ እድገት ያሳየ ነው።

የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ጌታቸው ተክለ ማሪያም እንደሚሉት፣ መንግሥት ከዚህ በፊት ሲከፍል የቆየውን ካሳ መክፈል ማቆሙ አግባብነት የለውም። የአገርን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ሥራ ነው፤ አልሚዎች መንግሥትን አምነው ሃብታቸውን ያፈስሳሉ፣ መንግሥትም ይህንን እምነት መጠበቅ መቻል አለበት የሚሉት ጌታቸው፣ ይህንን ማድረግ ባልቻለ ጊዜ ግን ካሳ መክፈል እንጂ ብድር ማቅረብ ማለት አግባብነት የሌለው ውሳኔ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መንግሥት የፋይናንስ አቅሜ አይፈቅድም በማለት የሚያስቀምጠውን መሟገቻ የማይስማሙበት ጌታቸው፣ መንግሥት ይሄንን ለማሳካትም የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ እምነቱን ማስጠበቅ ይገባዋል ብለዋል።

‹‹ይህ ውሳኔ መንግሥት ያለበትን ጥልቅ የፋይናንስ ችግር ያመላክታል›› ያሉት ባለሞያው፣ ይህ ግን ውስብስብ የሆነ ችግሮችን ይዞ በመምጣት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይጎዳዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ደኅንነት ችግር ወደ ዋስትና ማጣት የሚያሸጋግሩ ውሳኔዎች አልሚዎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ኹለቴ እንዲያስቡ ያደርጋል።›› ሲሉ አክለዋል።

በጥቅምት ወር በኦሮሚያ፣ በሀረሪ እና በድሬዳዋ ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ መሠረተ ልማቶች፣ የግለሰብ ንብረቶች እንዲሁም ፋብሪካዎች ወድመዋል። ከሰው ሕይወት መጥፋት በተጨማሪ የወደሙት እንደ ምሥራቅ አፍሪካ የዱቄት ፋብሪካ ዓይነት ተቋማትም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረቶቹን እንዳጣ የድርጅቱ ኀላፊዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን መግለፃቸው የሚታወስ ሲሆን በአዲስ አበባም ዲ ኤች ገዳ የብርድ ልብስ ማምረቻን ጨምሮ አንዳንድ ፋብሪካዎች የከፋ ጉዳት ባይደርስባቸውም የጥቃት ሙከራዎች እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here