ዐስሩ ፓርቲዎች ያደረጉት ስምምነት እስከ ውህደት ሊደርስ ይችላል ተባለ

0
421

አርብ ኅዳር 26/2012 ዐስር የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን ከ 10 ቀናት በኋላ በሚጀመረው የመዋቅር ጥናት መሠረት ቢያንስ ትብብር እንደሚሆን እና ከተቻለ ግን ወደ ግንባር ወይም ወደ ውህደት ሊመጣ እንደሚችል አስታወቁ።

በኢሊሊ ሆቴል ለትብብሩ ቅድመ ሁኔታ ወይም የፍላጎት መግለጫ ይሆን ዘንድ በተፈረመው ሰነድ ላይ በመመርኮዝ ሦስት ኮሚቴዎች ከሁሉም ፓርቲዎች ተመርጠው መዋቀሩን የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር(ኦነግ) ቃል አቀባይ ቀጄላ መርዳሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የመጀመሪያው ኮሚቴ የትብብሩን መዋቅር የሚያጠና ሲሆን ኹለተኛው ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት፣ ሦስተኛው ኮሚቴ ደግሞ ስለ መጪው ምርጫ የሚያጠና ይሆናል።

ከኦነግ በተጨማሪም የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የአፋር ሕዝቦች ነፃነት ፓርቲ፣ የሲዳማ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአገው አገር አቀፍ ሸንጎ፣ የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ትብብሩን መሥረተዋል።

ትብብሩን ለመመሥረት ዋነኛ መስማሚያ ነጥቦች ናቸው የተባሉትም በኅብረ ብሔራዊ ስርዓቱ ላይ የሚደረጉ ተቃራኒ ድርጊቶችን ለመመከት፣ ለይስሙላ የተቀመጠውን የፌዴራል ስርዓት በሥራ ላይ እንዲውል ለማስቻል፣ የአገረ መንግሥት ግንባታውን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ሁሉም ጥያቄ የሆነውን ሰላም ለማስፈን መሆኑን ቀጄላ ተናግረዋል። ስድስት ወር የፈጀ ድርድር እና ውይይት መደረጉን ገልጸው ሐሳቡ ከአንድ ፓርቲ የመነጨ ሳይሆን ሁሉም በየፊናው በሚገናኝበት ጊዜ የመጣ ሐሳብ ነው። በተለያዩ መድረኮች በምንገናኝበት ጊዜ የተነጋገርንበት ሐሳብ ቢሆንም ሁሌም ምርጫ በመጣ ጊዜ ተሰባስቦ መነጋገር የተለመደ ነው።

ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ‹‹ትብብር ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ›› በሚል ኅብረት ነበረ ያሉት ቶሌራ፣ እንዲህ ዓይነት ጥምረቶች አዲስ አይደሉም ብለዋል። አክለውም ከተለያዩ ፓርቲዎች የሚመጡ ብዙ ጥያቄዎች ስላሉ የአባላት ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል።

‹‹የተለያዩ ጥያቄዎች ይመጡልናል ነገር ግን በቡድን እንዲሁም እያንዳንዱ ፓርቲ የኹለትዮሽ ውይይት ካደረገ በኋላ የፓርቲዎች የኋላ ታሪክ ተጠንቶ የሚፈቀድ ነው›› ብለው ‹‹ሕወሓት በትብብር ውስጥ ለመግባት ጥያቄ አቅርቧል የተባለው ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ነገር ግን ፓርቲው በተለያዩ መድረኮች ላይ እንድንሳተፍ ጥሪ ያቀርባል እኛ ግን ለመሳተፍ ፍለጎት የለንም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ላለፈው 27 የመጣንበት መንገድ እንዲህ ዝም ብሎ የሚታለፍ ሳይሆን የተዛባውን ግንኙነት ወደ ኋላ ዞር ብሎ መመለከት የሚጠይቅ ነው። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚሆን ነገር አይደለም ጊዜ ይፈልጋል›› ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ተፎካካሪ በመሆኑ እንዲህ ያድርግ እያልን ምክር አንሰጥም ያሉት የኦነግ አመራር ቀጄላ፣ ፕሮግራሙን በዝርዝር ተመልክተን ምርጫ ሲደርስ የተሻለ አማራጭ ይዘን የምንሞግተው ነው ብለዋል።

ከትብብሩ መዋቅር በተጨማሪም መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጀቶ ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ የመጨረሻ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል የተባለ ሲሆን፣ አርብ በተደረገው ጉባኤም የሦስቱ ኮሚቴዎች ውጪ የተመረጠ የአመራር መዋቅር ያለመኖሩን ተናግረዋል።
እስከቀጣዩ ምርጫም የትብብሩ ቅርጽ እና አስፈላጊ ሥራዎች እንደሚገባደዱ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here